በሕወሓት/ኢህአዴግ ባለስልጣናት የተዘረፈ በርካታ የኢትዮጵያውያን ሃብት በዩናይትድ አረብ ኤመሬትስ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል:: ባለፈው ሳምንት ከዓለም አቀፉ ፖሊስ ተቋም ኢንተርፖል ጋር የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽመው የትም ሃገር የተደበቁ ወንጀለኞችን ይዞ ለማምጣት የተስማማው የዶ/ር አብይ አህመድ አስተዳደር ዛሬ ደግሞ ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ድንበር ዘለል የፋይናንስ ወንጀሎችን ለመከላከል መስማማታቸውን ይፋ አድርጓል::
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተከበሩ ሼክ አብዱላ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር አቡዳቢ ውስጥ ዛሬ ባደረጉት ውይይት የሁለቱ አገሮቹን ግንኙነት የደረሰበትን አጥጋቢ ደረጃ አንስተው የተነጋገሩ ሲሆን ይህንኑ ወዳጅነት የበለጠ በማጠናከር አገሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ መስማማታቸው ተሰምቷል::
በአገር ውስጥ የተጀመረውን የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ጥረት ለመደገፍ ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኢኮኖሚ ላይ የሚፈፀምን ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከልና ሲፈፀሙም ተቀናጅቶ ለመመርመር በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በተሳተፉበት በዚህ ውይይት በኢንቨስትመንት፣ በግዥ እና ሌሎች ተዛማጅ ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል እና ለመዋጋት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ከመግባባት ደርሰዋል፡፡
በቀጣይ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን መከላከል የሚካሄድ ጠንከራ ጥረትን በህግ መዕቀፍ ለማስደገፍ አብረው እንደሚሰሩም ገልጸዋል::
በተለይ በአቡዳቢና በዱባይ የሕወሓት/ኢህአዴግ ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ የሰረቁትን ሃብት በማሸሽ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ መሰማራታቸው; በየባንኮቹም በርካታ ብሮችን እንዳስቀመጡ በተደጋጋሚ ሲነገር ነበር:: ከሜቴክ የተዘረፈ በርካታ ገንዘብብ እንዲሁም ሕወሓት የሚያካሂደው የጥቁር ገበያ ንግድ ዋና መናኸሪያም የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ መሆኑ ይታወቃል::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ወንጀለኞችን የክልል ወሰን ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ወሰን ሳያግደን ይዘን ለፍርድ እናቀርባለን ማለታቸው ይታወሳል::
https://www.youtube.com/watch?v=3DhpJfLazkE&t=397s