የሚኒሶታ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ለ18ኛ ያዘጋጀው የባህል ምሽት የፊታችን ቅዳሜ ይደረጋል

April 16, 2013

(ዘ-ሐበሻ) በሚኒሶታ የሚገኘው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ለ18ኛ ጊዜ ያዘጋጀው የባህል ምሽት ዘንድሮም የፊታችን ቅዳሜ ኤፕሪል 20 ቀን 2013 እንደሚደረግ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወጣት አብርሃም ደስታ ለዘ-ሐበሻ ገለጸ።
ከተመሰረተ 19ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር በሚኒሶታ በየዓመቱ የባህል፣ የፋሽን፣ የራት፣ የስነጽሁፍ፣ የውዝዋዜና የተለያዩ ዝግጅቶችን በየዓመቱ በሚያቀርብበት በዚህ ዝግጅት ላይ ለ4ኛ ጊዜ በዶ/ር ሲራክ ኃይሉ የሚሰጠው የስኮላርሺፕ አሸናፊዎችም በዚሁ ዕለት ይታወቃሉ ያለው ፕሬዚዳንቱ ወጣት አብርሃም 10 ተማሪዎች የዘንድሮውን ስኮላርሺፕ ለማሸነፍ በከፍተኛ ውድድር ላይ ናቸው ብሏል።
አምና “ተረት ተረት”በሚል ርዕስ የተከበረው ይኸው የሚኒሶታ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ዓመታዊ በዓል ዘንድሮ ደግሞ “የሃገር ኩራት” በሚል እንደሚከበር ወጣት አብርሃም ለዘ-ሐበሻ አስረድቷል። እንደ አብርሃም ገለጻ “እዚህ አሜሪካን ሃገር እየኖሩ፣ ተወልደውም ሆነ እዚህ ያደጉ ወገኖቻን በኢትዮጵያዊነታቸው እንዳይሸማቀቁ፤ ይልቁንም በኢትዮጵያዊነታቸው እንዲኮሩ በማሰብ ነው የዘንድሮው የባዕሉ ርዕስ የሃገር ኩራት በሚል ር ዕስ እንዲከበር የታሰበው”። በዚህ ዓመታዊ በዓል ላይ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን የሚያሳዩ አኩሪ ሥራዎች እንደሚቀርቡም ፕሬዚዳንቱ ለዘ-ሐበሻ ገልጿል።
ኤፕሪል 20 ቀን 2013 በሚደረገው በዚሁ ዓመታዊ በዓል ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የካንሰር ሆስፒታል ለመሥራት ቅድመ ዝግጅታቸውን ያጠናቀቁት ክብርት ወሰኒ ባወር ከካሊፎርኒያ ተጋብዘው በክብር እንድግድነት እንደሚገኙ የገለጸው የተማሪዎቹ ፕሬዚዳንት “ይህን ዝግጅት ለማድረግ 3 ወራት ፈጅቶብናል። ከቤተሰብ ጋር የሚታይ የባህል እና የራት ምሽት ነው ያዘጋጀነው። አምና በተደረገው ተመሳሳይ በዓል ላይ ከምንገምተው በላይ ህዝብ በመምጣት አዳራሹ ሞልቶ ነበር። ዘንድሮም የሚኒሶታ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ የተማሪዎቹን ሥራ እንዲመለከት፤ ኢትዮጵያን በጋራ እንዲያነግስ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ብሏል።
ይህ ዓመታዊ የባህል ዝግጅት የሚደረግበት አድራሻ 2017 Buford Ave Ste 42, Saint Paul, MN 55108 ሲሆን ለበለጠ መረጃ 7634390351 መደወል ይቻላል።S


Previous Story

‹ልጅ ያቦካው —- › እንዲሉ! (ልጅ ተክሌ ‘የኢሳት 3ኛ አመት ክብረ-በዓል የሙስሊሞች ብቻ ነው እንዴ?’ በሚል ላቀረበው ጽሁፍ የተሰጠ ምላሽ)

Next Story

የመለስ ሌጋሲ አስፈጻሚዎች ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙን በእስር ቤት ቢያሰቃዩም ዩኔስኮ ጋዜጠኛዋን ሸለመ

Go toTop