ሰሞኑን በመንገድ ዳር የተገነቡ ና ከመንገድ ዳር ከፕላን ውጪ የተገነቡ የንግድ ቤቶችን የማፍረስ ዘመቻ በአዳማ አንዳንድ ቀበሌዎች እየተካሄደ ነው ። የማፍረስ ዘመቻውንም እያከናወነ ያለው የከተማው አሥተዳደር ፤ ይሁን እንጂ ማዘጋጃ ቤቱ ይሁን ፣ የአሥተዳደር አካሉ የትኛው የማፍረስ ሥራውን እንደሚያከናውን ፣ ባለ ንግድ ቤቶቹ አያውቁም ። አብዛኛዎቹም ከግለሰብ ተከራይተው ሥለሚሰሩ ፣ ግርግሩ ግራ አግባቷቸዋል ። በግልፅ የሚያውቁት ጉዳይም የለም ። አፍራሽ ግብረ ኃይሎችም ፣ ለፀጥታና መረጋጋት ይበጃሉ ተብለው ከየጎጡ የተመለመሉ እጅግ የበዙ ሥራ አጥ ዜጎች ናቸው ። ( አንዳንዶቹም የቀበሌ ቤት እናገኛለን ብለው ፣ የቀን ሥራቸውን ትተው ከቀበሌ የብልፅግና ካቢኒዎች ጋር ዘወትር የሚባትሉ ናቸው ።
በእርግጥ ከአፍራሾቹ ውሥጥ አንዳንድ የመሥተዳድሩ አካላትም በብልፅግና ሥም ራሳቸውን የሚያበለፅጉ ቀምቶ በሎች እንጂ ሠርቶ በሎች እንዳልሆኑ ስለሚታወቅ በዚህ ተግባር ላይ መሠማራታቸው ፈፅሞ አያሥገርምም ።
እናም እላለሁ ፣ “ ይኽ የማፍረስ ዘመቻ የሥራ ፈቶች ዘመቻ በመሆኑ አንድ ታታሪ ሰው ፣ ምን ያህል እንደሚለፋ እና ለኑሮዎ መቃናት እንደሚደክም ያልተገነዘበ በመሆኑ በአሥቸኳይ መቆም አለበት ። በማፍረስ እና መልሶ ጉቦ ተቀብሎ ማሰራት ፣ እንደ ወያኔ ዘመን ልማድ ዜጎችን ማሥከፋት ነው ይገፀስ ። ይኼ ፣ ትላንት ያሥተዋልነው ፤ ውሃ ቅዳ ፣ ውሃ መልስ ተግባር ነው ። ይኽ የማፍረስ ዘመቻ በሥራ ለምናምን ብዙዎቻችን አሥከፊና ግማሽ ልጩ ና ገማሽ ጎፈሬ የሆነ ድህነትን አሥፋፊ ዘመቻ በመሆኑ በአሥቸኳይ ይታረም ። “ እላለሁ ።
ይኽ ድህነትን የሚያበረታታ ፣ የማፍረስ ዘመቻ ፤ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ያለው ፣ በየመንገዱ ዳርና ዳር ፣ ከተከራዩበት ቤት ውጪ ፣ ጊዚያዊ ጥላ ሰርተው ፣ ቤት ገንብተው ፣ የፀሐይ መጠለያ ሰርተው ሸቀጦቻቸውን ዘርግተው ፣ እየሸጡ ባሉ ግለሰቦች እና እነሱን ከለላ አድርገው ፣ ሲኒ ደርድረው ቡና በመሸጥ ላይ የነበሩትን በእጅጉ የሚጎዳ ና ወደ ድህነት አዘቅት የሚጨምር ነው ና መወገዝም አለበት ።
በዋና መንገድ ላይ ወንበር ደርድረው ፣ ይኽንን ደሃ ህዝብ ሥጋ እየበሉ ና ውስኪ እየጠጡ የሚያሥጎመጁትን ፣ “ ወደ ንግድ ቤታችሁ ግቡና ያሻችሁን ፈፅሙ ። ይኽ ነፃ ቦታ የእናንተ በረንዳ አይደለም ና በህዝብ መተላለፊያ ላይ ተቀምጣችው ፣ ህዝብን አታሳቁት ፤ አታሰቅቁት ፣ … ።” በማለት የወሰዳችሁት እርምጃ ተገቢና ትክክል ቢሆንም ፣ ሁሉንም ቀበሌዎች በነካ እጃችሁ መዳሰሱን አትዘንጉም ። ይላል ህዝቡ ።
ለውበት አሳማሪ _ ሊስትሮዎችና ለመንገድ ላይ ቡና አፍይዎች የተዋበ መጠለያ በጎዳና ላይ ወይም ጥገ አላይም በፓርክ ውሥጥ ቦታ ሰጥቶ ሥራ አጥነትን ፣ ሥራ በመፍጠር ፣ ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ የማይጥር ፤ የከተማ አሥተዳደር ፣ ለብልፅግና ቆሜያለሁ ማለት አይችልምና ይኽ የማፍረስ ፣ ህዝብና መንግሥትን የሚያቀያይም ተግባር በነማን ውጥን እና ምክር እንደተከናወነ ይጣራ ?
ህዝብ የሚለው ፣ “ የከተማው መሥተዳድር ፣ ነገ ከተማው ሲለማ ፣ ፎቅ እየተሰራ ቅርፅ በሚይዘው ከተማ ፣ ምንም ዓይነት እግረኛ የማይጎዝበትን ፣ በጭርንቁስ ቤት የተሞላን የጎዳና ዳርና ዳር ፣ ዳስና በረንዳ ማፍረሱ ተገቢ ና ፍትሃዊ አይደለም ። “ ነው ። ለዚህ ድህነትን የማሥፋፋት ፣ ድርጊትም የምንጃር ጎዳናንን በዋቢነት ያቀርባል ። “ በተለይም 08 እና 07 ቀበሌ ውሥጥ የሞሉት ጭርንቁስ ቤቶች በጊዚያቸው በልማት የተነሳ መፍረስ ላይቀርላቸው ለምን ዛሬ ብዙ ሺ ሥራ አጦችን በውሥጣቸው አካተው ሣለ በዘመቻ መልክ የማፍረስ ተግባር ሊከናወንባቸው ቻለ ? “ በማለትም ይጠይቃል ።
እነዚህ ሁለት ፣ ቀበሌዎች ያለሙና እጅግ የበዛ ህገወጥ ግንባታ ያለባቸው ናቸው ። 08 ሙሉ ለሙሉ የህገወጥ ገብያ መናህሪያ ነው ። ሙሉ ለሙሉ ” ጉልት ነው ።” ማለት ይቻላል ። ዜሮ ሰባትም ከ08 የማይሻል የምንዱባኖች የዕለት እንጀራ ማግኛ ቀበሌ ነው ።
እነዚህ ሁለቱ ቀበሌዎች ፣ የሚለወጡት ፣ በአገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ሰፍኖ ፣መንግሥትና ህዝብ ወደልማት ፊቱን ሲመልስ እንደሆነ ይታወቃል ።በወቅቱ በልማት ፣ ሥለልማት ከተባለ ደግሞ ፣ ለጉልት ቸርቻሪዎች ፣ ሌላ ህገዊ ሆነው የሚሰሩበት ፣ እራሳቸውን ጠቅመው አገሪቱንም በግብር ክፍያ የሚጠቅሙበትን ፣ መንገድ በማመቻመች ቸርቻሪዎቹን ወደ ሌላ የገብያ ማዕከል መጠለያ ( ሼድ ) ሰርቶ ማዛወር እንጂ ፤ ብት ፈልጉ ዲንጋይ ብሉ ብሎ ፣ ከየጉልቱ ጠራርጎ ማንሳት የሚፈጥረው የራሱ የማይቀለበስ ችግር እንደሚወልድ የታወቀ ነው ። እናም ተለዋጭ ሥፍራ ሳያዘጋጁ መነካካት አላሥፈላጊ አይመሥለኝም ። ለራሱ ሰው ኑሮ ጭቅላቱን አዙሮታል ። ተጨማሪ ትንኮሳ ፣ ሆድ ለባሰው ጩቤ ማዋስ እንደሆነም መንግሥት አያውቅም ማለት አይቻልም ።
“ትላንት ፣ በአማራና አፋር የደረሰውን መፈናቀል እኛም እንደግመዋለን ! ” ነው እንዴ ነገሩ ? … ።በበኩሌ ፣ “ ይኽ የማፈናቀል ዘመቻ ፣ ህዘብን ለማስቀየም እና የብልፅግና መንግሥትን የድህነት መንግሥት አድርጎ ለመሣል የተወጠነ ነው ። ሌበነት ፣ ለማኝነት ፣ ጎዳና ተዳዳሪነትን ለማበራከት እና እንደገና በሁከትና በብጥብጥ መንግሥት እንዲተረማመስ ና ሀገር እንዲፈርስ ለማድረግም በህግ ማሥከበር ሥም የተተኮሰ የመጀመሪያው ሠላም አደፍራሽ ጥይት ነው ። “ ብዬ ለማመን እገደደለሁ ። ይኽ ድርጊት መወገዝ ያለበትና በአስቸኳይ መቆም ያለበት ውጉዝ ተግባር እንደሆነም አሰምርበታለሁ ።
ይኽ ውጉዝ ተግባር ፣ በእግረኛ መንገድ ማፅዳት ሥም ፣ በመሐል ከተማ በጎርፍ መውረጃዎች ውሥጥ የተከማቸውን ግማት ፣ ማዘጋጃ ቤቱ ሳያፀዳ ፤ በሥራ ፈትነት አልያም ለሥውር ጥቅም ፣ አልያም ለሥውር ሤራ የገባባት የማፍረስ ተግባር ከሆነ ደግሞ እጅግ አሣፋሪ ነው ።
( እኔ የለሁበትም የየቀበሌው ካድሬዎችና አጫፈሪዎቻቻቸው ናቸው ካለ ደግሞ ፤ በማዘጋጃ ቤቱ አንፈርድም ። )
እንዴ ! ሆን ብሎ ሠርቶ የሚበላውን ህዝብ ፣ የመሥሪያ ሥፍራውን እያፈራረሱ ፣ መሥለቀሥ ምን የሚሉት ህግና ደንብ ማሥከበር ነው ? ለሚሰራ ሰው ቀድሞ ቦታ ሳያመቻምቹ እነሱን ተገን አድርገው የዕለት እንጀራቸውን የሚያገኙትን የመንገድ ላይ ቡና አፍይ እህቶቻችንን እንጀራ መሣጣትሥ የሚጨበጨብለት ተግባር ነውን ? ¡¡ ከምናፈናቅላቸው በፊት ለሠራተኛ ዜጎች ተገቢ መፍትሄ ማሥቀመጥ የአሥተዳደር ነኝ ባዩ ፤ የመንግሥት ሹም ኃላፊነት ነበር ። ይኽ አሥተዳደር የመንግሥት የታችኛው አካል መሆኑንም መዘንጋት አልነበረበትም ።
ዜጎች ይህ የታችኛው የመንግሥት አካል ፣ ፖሊሥን እና ሥራ ፈት የጎጥና የቀበሌ ጭፍራዎቹን ይዞ ” ኃይ በለው ” በማለት በዘፈቀደ ፣ ከጎዳና ላይ ዜጎችን “ቢፈልጉ አፈር ይብሉ ። ምን አገባኝ ። አሥጨንቄ ኋላ ትርፍ አገኛለሁ ። …”በማለት መንቀሳቀሱን ያውቃሉና ፣ ቅሬታቸው አገርን በመምራት ላይ ባለው መንግሥት ላይ መሆኑንን ከፍተኛው የመንግሥት አካል ማወቅ አለበት ። ብዙ መልካም አማራጮችን እና ገቢዎችን ማግኛ መንገድ እያለ ፣ በደቀቀ ኢኮኖማ ፣ ዜጎችን በሥራ አጥነት ማድቀቅም ነውረኝነት ነው ። መሥተዳድሩ ድብቅ ሤራ ባይኖረው ፣ ወይም የዕውቀት ደሃ ባይሆን ኖሮ ፣ ዜጎች ፣ ባልተገነነ ኪራይ ፣ ሰርተው የሚለወጡበትን ፣ የመንገድ ጥግ ፣ ቡና ማፍያ ፣ በአማረ መልኩ ሠርቶ በማከራየት ፣ ማዘጋጃቤቱ ገቢ ማግኘት ይችል ነበረ እኮ ! !
ለምሳሌ ፣ ለጫማ ውበት ጠባቂዎች ፣ መንገዱን የሚያሥውብ የፀሐይ መከላከያ ና መቀመጫ ፣ በየመንገዱ በመሥታወቂያ አገልግሎት ፣ በየመቶ ሜትሩ በማሠራት ፣ ለማዘጋጃ አገልግሎት ፣ በየወሩ በባንክ እንዲከፍሉ በማድረግ ገቢውን ማሳደግ ይችል ነበር ። ህዝብን ዝቅ ብለው በማገልገል ፣ የዕለት እንጀራቸውን በማግኘት ላይ ያሉትን ፣ አገርን ጠቃሚ ማድረግ ሲገባ ፣ ማሳደድ ተገቢ ና ትክክል አይደለም ። በዚኽኛው ዳር መንገድ ላይ ቁጭ ብሎ ሲሰራ ” የእኔ ወገን ነው ። ” ብሎ መተው ፣ በወዲያ በኩል ተመሣሣይ ሥራ የሚሰራውን በነጋ በጠባ ” መጣሁብህ ! ንብረትህን እወርሳለሁ !! ” ብሎ ማሥፈራራት የሰው ተግባር አይደለም ና ሊወገዝና ባሥቸኳይ እንዲቆም ቀጭን ትዕዛዝ በሚመለከተው ባለሥልጣን ሊሠጥበትም ይገባል ። …
( በአዳማ ከተማ ፣ በዋናው ንግድ ባንክ ፊት ለፊት ፣ በፓርኩ መሐል ፤ በኮብል እስቶን መንገዱ ጥጉን ይዘው የሚሰሩትን ሊስትሮዎች ፣ እንዳይሰሩ መከልከል በበኩሌ ፣ ዘርፋችሁ ፣ ሠርቃችሁ ፣ ለምናችሁ ወዘተ ። ብሉ እንጂ ሠርታችሁ አትብሎ ማለት ነው ።
ሥለ ህገ ወጥ አሠራር መወገድ ከተነሳ ፣ ከወያኔ አገዛዝ ጀምሮ ህግን መጣሥ የተለመደ እና የሚበረታታ ሆኖ መገኘቱ እየታወቀ ። በዋነኝነት ይህን የህገ ወጥ መድረክም የከፈቱትና ለመላው ከተማ ኗዋሪ ያሥተማሩት እነሱ መሆናቸው እየታወቀ ፣ ዛሬ ደርሶ ይህንን ውሥብሥብ ህገ ወጥ ድርጊት ፣ ህጋዊ ና ሁሉንም ያካተተ ባልሆነ የጉልበት መንገድ ፣ ቦታ እየለዩ ማፍረስ ህገ ወጥ አሠራር ነው ። በቅድሚያ ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ፣ ለእነዚህ ህገ ወጥ ድርጊቶች ፣ ምን ዓይነት ህጋዊ መፍትሄ በናቅድና ፣ይህንን እቅድ ለመተግበር የሚያሥችል ሀብት ከነማን እናገኛለን ብሎ ማሰብ ሊቀድም ይገባል ። ለሁሉም ነገር ፣ ለከተማ ፅዳቱም ቢሆን በቆሻሻ ለተሞላው አርጂን ዘላቂ መፍትሄ ለመሥጠት ፣ በችግሩና በችግሩ አፈታት ዙሪያ የሚመለከታቸውን ምሁራንን ያካተተ ውይይትና እቅድ እጅግ አሥፈላጊ ነው ።
የከተማ ውበትና ፅዳት የሚመለከታቸው ና የሚቆረቁራቸው ፣ የበኩላቸውን ለማዋጣት ዝግጁ የሆኑ ምሁራን ከተማዋ አላጣችም ። ደግሞም መታወቅ ያለበት ፣ መላ አዳማ ፣ በአራቱም አቅጣጫ ፣ በጨረቃ ቪላ ቤቶችና ደሳሳ ጎጆዎች የተሞላች ፣ እና የአካባቢውም ውበት ፣ በእጅጉ የቆሸሸበት ሥፍራ መኖሩ እንግዳ አይደለም ። እናም ህገ ወጦች ባለ ጨረቃ ቤቱች ፣ ቢያንስ ግብር የሚገብሩበትን መንገድ መመቻቸት ወይም ወደ ህጋዊ መንገድ ማምጣት እንዲቻል የመፍትሄ አቅጣጫ ሊያሥቀምጡ የሚችሉት እነዚህ ምሁራን እንደሆኑ መገንዘብ ያሥፈልጋል ። ቆሻሻ በሚከማችበት የጎርፍ መውረጃም ከአካባቢው ባለሀብት ጋር በመነጋገር ፣ የጎርፍ መውረጃው ፣ ቆሻሻ በማይደፋበት መልኩ ፣ በወጉ የማገነባበትን መንገድ ሊቀይሱ የሚችሉት እነዚህ ምሁራን ናቸው ።
ይኽን የከተማዋን ገፅታ ያበላሸ ፣ ማሀል ከተማ ውሥጥ የሚታይ አሥጠሊታ ቆሻሻ ለማሶገድ ፣ መላው የከተማን ህዝብ አሥተባብሮ ወደ መፍትሄ መግባትን ተቀዳሚ ሥራው ከማድረግ ይልቅ ነገ በልማት አሥገዳጅነት የሚሥተካከሉትን እና ከሥራቸው ጋር የብዙ ሺ ሠርቶ በሌዎችን ጉሮሮ የሚያረጥቡ ፣ የሥራ መድረኮችን መዝጋት በአሁኑ ሰዓት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነውና የብልፅግና መንግሥት ድህነትን ከማሥፋፋት ና በፀሐይና በቁር አቦራ ለብሰው ጎንበስ ብለው ጫማችንን በማሣመር የሚተዳደሩትን ሊስትሮዎች እና ትኩስ ቡና ለደሃው አዘጋጅተው በርካሽ ዋጋ ጀባ የሚሉንን ወደ ድህነት አረንቋ ተመለሠው እንዲገቡ ከመጫን እንዲቆጠብ በፅኑ እንመክራለን ።