ዛሬ ከብዙ ጊዜ በኋላ ለመጻፍ ያስገደደኝ ጉዳይ ቢኖር የአገር ደህንነት ሚስጢራት ብክነትን በማየቴ ነው፡፡ የመከላከያው አወቃቀርና የሚስጢር አያያዝ እጅግ ያሳዝነኛል አስደንግጦኛልም፡፡ በትላንትናው እለት እንኳን አንድ እኔን አጅግ ያስደነገጠ አሳዛኝ ክስተት አይቻለሁ፡፡ የኢትዮጵያን አየር ኃይል ማዘዣ ጣቢያ ጉብኝት በሚል በፊልም ቀርጸው በዩቲዩብ የለቀቁትን ሳይ እጅግ ነው ያዘንኩት፡፡ ሲጀምር እንዲህ ያለን ጥብቅ የአገር መከላከያ የደህንነት ቦታ አንኳንስ በቪዲዮ ካሜራ መቅረጽ ይቅርና መጎብኘትስ እንዴት ሊታሰብ ቻለ? እነዚህ በጎብኚ ሥም የታደሙት በምን አግባብ እንዲህ ያለ ቦታ ገብተው እንዲጉበኙ ተፈቀደላቸው? ምን የሚሉት ዓላማ ይሆን? ሌላ ቀርቶ እንዲህ ያለ ቦታ ለራሱ ለመከላከያ ተቋሙ ባልደረቦች እንኳን ከተፈቀደላቸው በቀር መግባት ይችላሉ? ምን እየሆነ ነው ያለው? ይሄን ቪዲዮ ለአጭረስ ሰዓት በዩቲዩብ ከለቀቁት በኋላ ወዲያውኑ አነስተውታል፡፡ ከታየው ቢዲዮስ ውጭ ምን ምን ሚስጢራትን አነዚህ ጎብኝ የተባሉት ማየት አንደቻሉ የምናውቀው የለም፡፡ ነገ ለአገር ጠላት ለሆኑ ሸጠው ሊከብሩበት የሚችል ሚስጢር ወስደውስ ከሆነ፡፡ ነገ ለእነ ግብጽና ሌሎች የኢትዮጵያ ጠላቶች አሳልፈው ሊሸጡት አንደሚችሉ አለማስተዋል ትልቅ ስህተት ነው፡፡ እንግዲህ የመከላከያው መዋቅር የሚስጢር አያያዝ ሁሉም ቦታ እንዲህ ከሆነ መከላከያው አንዴት ውጤታማ ይሆናል? በተቃራኒው የመከላከያው የዕዝ ሰንሰለትና መረጃ ልወውጥ አጠያያቂ ነው፡፡ የዛሬ ዓመት መከላከያው ሳይዘጋጅ፣ በእቅልፍ ላይ እያለ ጦርነት ተከፈትንበት ከተባልንበት ጊዜ አንስቶ የመከላከያው የመረጃ ልውውጥና ሚስጢራዊነት አስደንግጦኛል፡፡ አንድ የመከላከያ ተቋም በየትኛውም አግባብ በተነገረን አይነት የመጠቃት አደጋ ሊገጥመው አይችል ብዬ አምናለሁ፡፡ በተቃራኒው በዛን ወቅት ወያኔ አዲስ አበባ ያሉ አባላቶቻቸውን ሳይቀር በደንብ በመረጃ አጠናክረዋቸውና አንዳንዶችም መቀሌ ሰላም ሆና አዲስ አበባ የጦር ሜዳ ትሆናለች በሚል ስላቀዱት ወደመቀሌ ሄደው ነበር፡፡ አንግዲህ ይሄ በወያኔ ደጋፊዎቿ ጋር ያለ የእዝና መረጃ ልውውጥ ሰንሰለትን የአገሪቱ የትኛውም የደህንነት ተቋም አላወቀውም ወይም ሆን ትብሎ ተትቷል፡፡ መከላከያን የሚያህል ተቋም ግን ባላሰበበት ጊዜ ተጠቃ በሚል ሊደልሉን ሞክረዋል፡፡ እንዴት ብሎ የጠየቀ የለም፡፡ የሆነ ሆኖ የመከላከያው የመረጃ አያያዝና ልውውጥ አገርን ለአደጋ እየዳረገ አንደሆነ ይታሰብበት፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአገር መከላከያ ባለስልጣን ጀነራሎች በተደጋጋሚ በሚዲያ እየወጡ ቃለመጠይቅ ሲደረግላቸው ተመልክቻለሁ፡፡ ይሄም ትልቅ ስህተት ነው፡፡ የአንድን መከላከያ አዛዥ ማንም እንዲህ ባለ ሁኔታ ማገኘትና ቃለመጠይቅ ማረግ ከቻለ እንግዲህ የተቋሙ ሚስጢራዊነት አደጋ ላይ ሊሆን እንሚችል መታሰብ አለበት፡፡ በኢትዮጵያ መከላከያ ጀነራል ነን በሚሉት እየተደረገ ያለው አደጋ እንዳለው አስተውሉ፡፡ የታማጆር ሹሙን ጨምሮ ሌሎችም እንደልባቸው የትም ቃለ መጠይቅ ሲያደርጉ ኧረ ተው የሚል የለም፡፡ ከእንደነዚህ ያሉ ቃለ መጠይቆች ጠላት ምን ያህል መረጃ እነደሚያገኝ ግልጽ ነው፡፡ ይታሰብበት፡፡
በዚሁ ሰሞኑን እየሆነ ያለውን ለማስተዋል ቢረዳ እስኪ ትንሽ ልበል፡፡ ዛሬ እየሆነ ያለውን ቀደም ብለን አንዳንዶቻችን ሊሆን እንዳለው አስተውለን ደጋግመን ማስጠንቀቂያ ብንሰጥም በሆያሆዬ የጠፋው ማስተዋል ወሳኝ ጉዳዮች እንደዋዛ አሳልፈናል፡፡ አሁን ምንም ማለት አልችልም፡፡ አስተያየትም ላለመስጠት አስቤ ነበር፡፡ ለብዙ ጊዜም ዝምታን መርጬ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ መደናግጥና ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም፡፡ እየሆነ ያለው መሆን ያለበት ነው፡፡ እንዲህ ካልሆነ ሊገባን አልቻለምና፡፡ ሆኖም ነገሮች እንደሚቀየሩም አያለሁ፡፡ ግን የመጣንባቸውን ሂደቶችና ስህተቶቻችንን እናስተውል፣ እናርም፡፡ እርም የሆነውን ነገር ከመካከላችን እናውጣ፡፡ ለእውነት እንቁም፡፡
ወያኔ 27 ዓመት የሄደችበትንና ሕዝብ ክፉኛ የተጎዳበትን አካሄደ ምርጫው አድርጎ የዛሬ ሶሰት ተኩል ዓመት የጀመረው ወያኔ በጋተችው የአማራ ጥላቻ የለከፈው የኦሮሞ ተረኛና ዘረኛ ኢትዮጵያን ዛሬ ለደረሰችበት እነዳደረጋት እናያለን፡፡ እነ ለማ በጀመሩት ቢቀጥል ዛሬ እውነትም ኢትዮጵያ ትንሳኤዋን ማየት በጀመርን ነበር፡፡ እንግዲህ ከመጥን የላፈው ጥላቻ ዘረኝነትና ስግብግብነት አሁን ሁሉንም መልሳ ልትበላ እንደሆነ አስተውሉ፡፡ እንዳይደራጅና እንዳይታጠቅ መሪዎቹን ጭምር በመግደል ሲያሴሩበት የነበረው አማራ ከዚህ በኋላ ከሌላው የተለየ አደጋ እንደሌለበት ሁሉም ይረዳ፡፡ አሁን ጉዳዩ ወያኔ በመገባቸው የጥላቻና ዘረኝነት ባርነት ወድቀው በተረኝነት የሚያረጉትን ያሳጣቸውን ጨምሮ አደጋው አፍጦ መጥቷል፡፡
ለማ መገርሳ የወያኔን መንገድ አንደግምም በሚል የራሱን አቋም ይዞ እንደነበር እንታዘብ ነበር፡፡ ይህ የለማ አቋም በስግብግብነትና በዘረኝነትና ጥላቻ እንደወረደ ከወያኔ የተጋቱትን ስጋት ስለሆነባቸው መጀመሪያ ከኦሮሚያ ከዛም ከሁሉም ቦታ አስወጡት፡፡ ቀጥሎም ያለባህሪው የጸረ ኢትዮጵያዊነት ታርጋ ለጥፈውለት ኢነሱ በቅቤ ምላሳቸው ለኢትዮጵያ የታመኑ ሆነው ሰውን ሁሉ አዚም አረጉበት፡፡ የሆነውን እንድታስተውሉ ነው፡፡
በወያኔ የጥላቻ፣ ዘረኝነትና አረመኔነት የተጠመቀ ኦሮሞ የታላላቅ አባቶቹን ክብርና ታሪክ ክዶ በመረጠው ባርነት በመውደቁ ዛሬ በተረኝነት የወያኔን ቦታ ይዞ አገር እየመራ ባለበት ወያኔ አሁን ያገኘችውን እድል ባታገኝ ነበር የሚገርመው፡፡ ታላላቅ የሚባሉ መንግስታዊ መዋቅሮች መከላከያውን ጨምሮ ከወያኔ በከፋ ያለ ሀፍረት በወያኔ ጡት ባደጉት የሀገር ስሜት በሌላቸው ይልቁንም በከሀዲነትና በአገር ጠልነት በተበከሉ ኦነጋውያን ተወሮ ከወያኔ ጋር በሚደረግ ውጊያ ድልን መጠበቅ አይታሰብም፡፡ አዝናለሁ፡፡
ኢትዮጵያ በኢትዮጵያዊነታችን ለእኛ ለሁላችንም እጅግ ሰፊና ሀብታም አገር ነበረች፡፡ ሆኖም ግን እርግማን ሆኖብን ይሄው አሁን ያለንበትን እየኖርን ነው፡፡ ብዙ ተስፋ የተደረጉ ነገሮች በፍጥነት ጠፍተዋል፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር ተስፋ የሚሆን ነገር ሲሰጠን ሥሙን አመስግነን የተሰጠንን ተስፋ በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ በፈንጠዝያና በትቢት የሆነብንን ሁሉ ረስተን የሆነልንን ሁሉ ሳናስተውል ተመልሰን እዛው ነን፡፡ የኖህ ዘመን ሰዎችን አስተውሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን አሁንም መደናገጥ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ በውሸትና በማስመሰል ዛሬም በአገራችን ላይ እየቆመሩ ያሉ ሁሉም ይጠፉ ዘንድ እየሆነ ያለው እየሆነ ነው፡፡ በወያኔ አስተሳሰብ፣ በወያኔ ሕግና ስርዓት፣ በወያኔ አወቃቀር በወያኔ ሰንደቅ አገር በተረኝነት እየመሩ አይናችን እያየ በወያኔ አድገው በወያኔ ሥሪትና ሴራ እየቆመሩወያኔ ላይ እንዴት ያለ አቋም ሊኖራቸው ይችላል ተብሎ ነበር፡፡
የሚከተሉትን ነጥቦች ሕዝብም አገር ወዳድ የሆናችሁ በስልጣን ላይ ያላችሁም ሁሉ እንድታስተውሉት ይሁን
ኢትዮጵያውያን ሁሉ፡- መጀመሪያ እርም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ አውጡ፡፡ ከምንምና ከምን በፊት የወያኔ የሆኑ ሥርዓቶች፣ አሰራሮችና ምልክቶች ሁሉ ከኢትዮጵያ ምድር ይጠፉ ዝንድ እናስብ፡፡ በአፈ ቅቤዎች ተስፋ መከራችንን አናስረዝም፡፡ ወያኔ አስጠንቁላ ኮከብ የደረተችበትን ሰንደቅ ይዘህ፣ ወያኔ በጋተችህ የዘር መንፈስ ተለክፈህ፣ በወያኔ ሕግና ሥርዓቶች እየተመራህ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብትል ራስህን ታዘብ
ለአማራ፡- ከሁሉ በከፋ ወያኔ ከጅምሩ ጀምሮ በአማራ ጠል እምነቷ የተነሳችበትንና ይሄንኑ የጥላቻ መርዝ ወደሌሎች ያሰራጨችበትንና ኢትዮጵያዊነትን የሰለበችበትን ሂደት አስተውል፡፡ በመካከልህ እስከዛሬም መሪ ነን የሚሉ ሎሌዎቿ ያደረጉብህንም አስተውል፡፡ ለበቀለኝነት ሳይሆን ዛሬም እንዳይመርዙህ በሚል ነው፡፡ ዛሬም ድረስ በምድርህ እየሆነ ያለውን አስተውል፡፡ በዓዴን የተባለ አዴፓ ዛሬም ከወያኔ የተሰጠውን ዓርማ ሊተው አልፈለገም፡፡ ዛሬ አማራ በተባለው ምድር የበዓዴን የተባለው የእርግማን ባንዲራ ሲያውለበልብ የተገኘ ጠላትህ እንደሆነ አስተውል፡፡ ይህ የዕርግማን ምልክት ነውና፡፡ ባለኮከብ የሚባለው የወያኔን ባንዲራም እንዲሁ፡፡ ይሄን ስትጥልና በምድርህ ላይ እንዳይታይ ስታደርግ የሚከተልህን ኃይልና በረከት ታየዋለህ፡፡ ይሄ ለሌሎችም ማስተማሪያ ነው፡፡ አንተን ተከትለው የአባቶቻቸውን ቃል ኪዳን ይመልሱ ዘንድ፡፡ ይሄን ጉዳይ እንደተራ ነገር እንዳታየው እመክራለሁ፡፡
ሌላው የምትሰራውንና የምታስበውን በሚስጢር ያዝ፡፡ ለወሬና ጉራ አደባባይ እየወጡ መደንፋት ሳይሆን ጠላቶችህ እስከሚጨንቃቸው ዝም በል፡፡ ሥራህን ግን ሥራ፡፡ ዛሬ በክተትም ሆነ በሌሎች አዋጅ መሰል ዘመቻ አሰላለፍህን በገሀድ እየነገሩልህ እየማገዱህ ያሉትን መሪ ተብዬዎችን እየቆመሩ ያሉበትን ሁኔታ አስተውል፡፡ በጅምላና በመግበስበስ ሳይሆን በሁሉም ቦታ በጥንቃቄና በተሰላ ሁኔታ ተሰለፍ፡፡ ከመካከለህ ያሉ ጠላቶችህን ለይ፡፡
ለኦሮሞ፡-ኦሮሞ ከኢትዮጵያውያን ሁሉ የወያኔ ዋና የቁማር መድረክ እንደሆነ ብዙ ጊዜ ተናግሬአለሁ፡፡ አዝናለሁ፡፡ ኦሮሞን ከአባቶቹ ታሪክን ልዕልና አውጥተው ዛሬ ላይ የሚጋልቡት ፈረስ አድርገውት እናያለን፡፡ ወያኔ ለ27ዓመት እድል ያገኘውም በርካታ ኦሮሞን በተለይ ኦነግ በሚባል መሳሪያው ለአስተሳሰብ ባርነት ውስጥ መክተት መቻሉ ነው፡፡ ለጥቂት ጊዜ በተለይ ለማ መገርሳ በመራው የኦሮሞና አማራ ጥምረት አንድነት ምክነያት ምን ያህል ጉልበት እደነበርና በባዱ እጁ ጠላትን እንዴት እንዳስደነገጠና ከዛም በላይ እንዳስወገደ ማስተዋል በቂ ነበር፡፡ ኦሮሞን የአባቶቹን ታሪክ ማስካድና ከማንነቱ አውጥቶ መጠቀሚያ መሳሪያ ያደረገችውን ወያኔን ትልቅ ጉልበት የሆናት ሚስጢርም ይሄው ነው፡፡ እንጂማ ወያኔ ከሌላው ባልተናነሰ በኦሮሞም ብዙ ግፍ ፈጽማ ነበር፡፡ ዛሬ የኦነግ ሰራዊት መሪ ነኝ የሚለው ጃልመሮ ከእነጭርሱም ኦሮሞ ያልሆነ ኦሮምኛ የሚናገር ትግሬ እንደሆነ ስታዘብ አዝናለሁ፡፡ እንግዲህ በቅርቡ ጋላቢና ተጋላቢ በሚል በወጣው ዘገባ የምንሰማው ትግርኛ ተናጋሪ የኦነግ መሪ በትክክልም ኦሮሞ ነው የተባለው ጃል መሮ ከሆነ በዚህን ያህል ኦሮሞን ወያኔ መቆመሪያ በማድረጓ አዝናለሁ፡፡ የሰማሁት ጃል መሮ የተባለ ትግርኛ ተናጋሪ አፍ መፍቻ ቋንቋው ትግሪኛ እንደሆነ እናስተውላለን፡፡ የአማራው አንዱና ዋነኛ ችግሩ ሁሉም አማርኛ ስለሚናገር መለየት ስለሚያስቸግር ነው፡፡ በኦሮሞ ውስጥ የትግሪኛ ተናጋሪ (አክሰንት የሌለው) መሪ ነኝ ብሎ ያለበትን ሳሰብ ገና ብዙ ሌሎችም በኦሮሞ ሥም ያሉ ትግሬ ወያኔዎች እንደሆነ እገምታለሁ፡፡
ከኦሮሞ በኢትዮጵያዊነታቸው ጠንከር ያለ አቋም ያላቸው የቱንም ያህል የኦሮሞነት ስሜት ቢኖራቸውም እንዴት እየተለቀሙ እንደሆነ ሐጫሉ ሁንዴሳ ማሳያችን ነው፡፡ አሁንም እላለሁ ኦሮሞ ወደ አባቶችህ ተመለስ፡፡ ሰኚ ጎበና ዳጬ እያልክ ስትሰድብ የኖረከው ዛሬ ራስህን ላለህበት ዳርጎሀል፡፡ ዛሬ በተረኝነት ሥልጣን ለኦሮሞ ሆኗል ብለህ አስበህ ከሆነ ተሳስተሀል፡፡ ይሄው ምን እየሆነ እንደሆነ ታስተውላለህ፡፡
ለሱማሌና አፋር፡- ወያኔ የከፋ ግፍ ከፈጸመችባቸው እንደሕዝብ አንዱ ሱማሌ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ አሁን ያለው የሱማሌ አስተዳደርና የተቃዋሚ ድርጅቶችን ሳይቀር በወያኔ ላይ በያዙት አቋም አደንቃለሁ፡፡ እባብ ሞኝን ሁለቴ ነደፈው የሚለው ለሱማሌ አይሰራም፡፡ ለኦሮሞና አማራ ግን በተደጋጋሚ ነደፈው የሚለውም ይሰራል፡፡ አፋር ዝም ብሎ ሥራውን እየሰራ ይመስላል፡፡ አፋር ከድሮውም በኢትዮጵያዊነት መንፈስ መሪዎቹ ስላኖሩት ወያኔ የወሰደችበት አይመስልም፡፡ በቅርብ በሱማሌና አፋር ግጭት ተነሳ ሲባል አዝኜ ነበር፡፡ ለሱማሌና አፋርም ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም በድንበር ምክነያት ግጭት እንዳይኖር የወያኔን ምልክቶችና አሰራሮችን ማስወገድ ወሳኝ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊና ሀብታም አገር ነች፡፡ ለሁላችንም የሚበቃ ሀብት አለ ተረጋግተን መጠቀም ከቻልን፡፡ የአፋርና ሱማሌ ሕዝብና መሪዎች አስቡበት ለሌሎችም አርዓያ የሚሆን የሁለቱን ሕዝብ መስተጋብርን ፍጠሩ፡፡ ይሄን የምለው ትልልቅ ነን ከሚሉት አማራና ኦሮሞ በተሻለ የአመራር ብስለቶች በእነዚህ ሁለት ክልሎች ያስተዋልኩ ስለመሰለኝ ነው፡፡
ሌሎች፡- ምርጫችንን እንወቅ፡፡ ኢትዮጵያዊነቱና አንድነቱ ለራሳችን ስንል እንጂ ለሌሎች ብለን አይደለም፡፡ ይሄው በወያኔ ሕግ መሠረት ክልሎች መፈብረክ ቀጥለዋል፡፡ የወያኔን ሥርዓት አስወግጃለሁ እያለ በተግባር ከወያኔም በላይ እየሰራ ያለው ዛሬ ያለውን ተረኛ አስተውሉት፡፡ ክልል መሆን ለምን አንደተፈለገ አይገባኝም፡፡ ሁላችሁም ወዴት እየሄድን እንደሆነ አስቡበት፡፡ መሆን የነበረበት ይልቁንም ዛሬ ወያኔ በዘር የሸነሸነችውን አወቃቀር ሙሉ በሙሉ አፍረሶ የሕዝብን መስተጋብርና አስተዳደራዊ ምቾትን በሚፈጥር አወቃቀር መገንባት ነው፡፡
ደግሜ እላለሁ አሁን እየሆነ ያለው መሆን ስላለበት ነው፡፡ እንዲህ ካልሆንም ሊገባን አልቻልምና፡፡ እርም የሆነውን ነገር ከመካከላችን እናውጣ፡፡
ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
አሜን
ሰርፀ ደስታ