የ100 ቢልየን ብር ሃብት የ100+ ሚልየን ህዝብ ጉዳይ ነው፤ – ነብዩ ስሁል

September 29, 2021

በአሸባሪው ህወሓት ክህደታዊ ትንኮሳ ምክንያት የተገባው ህግ የማስከበር ተልእኮና ጦርነት ተከትሎ የተቋቋሞው የትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር በአደረጃጀትና በአፈጻጸም ሂደት የነበሩት በጎና ደካማ ጎኖች ሲመረመሩ ምን ያመስላሉ የሚል ጥያቄ የአብዛኛው ዜጋ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

ግዜያዊ አስተዳደሩ መጀመርያ ሲቋቋም ከነበረው አጣዳፊ ሁኔታ አንጻር በሚገባ ታስቦበትና ተቀናጅቶ የተጀመረ መዋቅር ባይሆንም የትግራይ ህዝብ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር በፌዴራል መንግስት ዘንድ የነበረው ፍላጎት ግን እጅግ ከፍተኛ እንደነበር ይታወሳል፤ በተለይ የግዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የለውጥ ኃይሎች እንዲሰባሰቡበት መደረጉ የትግራይ ህዝብ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳደር የነበረው ፍላጎት ጎላ አድርጎ ከማሳየቱ በተጨማሪም የተሻለ የዴሞክራሲ ልምምድ ለመፍጠር ተሞክሮበታል፡፡ ይህንን ተከትሎም አሸባሪው የህወሓት ቡዱን ያለአግባብ አግበስብሶ ይዞት ከቆየው መንበረ ስልጣኑ ተነቅሎ በህዝብ የተመረጡ የአዲስ ትውልድ አመራሮች ክልላቸው፣ ዞኖቻቸው፣ ከተሞቻቸው፣ ወረዳዎቻቸውና ቀበሌዎቻቸው የማስተዳደር እድል እዉን በማድረግ በክልልና በአገር ደረጃ አዲስ የአስተዳደር ታሪክ ለመስራት ተችሏዋል፡፡

ይህ ፍላጎትና አንጻራዊ እምርታ እንደተጠበቀ ሆኖ በግዜያዊ አስተዳደሩ ቀድሞ የነበረው የአመሰራረት፣ የስትራቴጂክና የቅንጅትና ክፍተት ላይ የከፍተኛ አመራር ድክመትና ኢህዝባዊ ፍላጎቶችና ተግባራት ተጨምሮዉበት አስተዳደሩ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት እጅጉን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡

በስትራቴጂክ ክፍተቱ ረገድ ሲታይ የተቀመጡት 5 የትኩረት አቅጣጫዎች የፖለቲካ ይዘትና ግብ ያልነበራቸውና በትግራይ የነበረው ሁኔታ በደንብ ያልተረዱ ጎዶሎ አቅጣጫዎች ከመሆናቸው በተጨማሪ ግዜያዊ አስተዳደሩ ከፖለቲካና ከለውጥ ኃይልነት ይልቅ አነስተኛ የበጎ አድራጎት ተቋም መስሎ ለመንቀሳቀስ በመሞከሩ የህዝብና የለውጥ ፈላጊው ማህበረሰብ ቀልብ ለመግዛት ሳይችል ቀርቷል፡፡ በመቀጥልም ግዜያዊ አስተዳደሩ የትግራይ ህዝብና የለውጥ ኃይሉ በጉጉት ይጠብቃቸው የነበሩ የፖለቲካ፣ የፕሮፖጋንዳ፣ የሚድያና የህዝብ ግንኙነት የመሳሰሉ እጅግ ወሳኝ የስራና የርብርብ ዘርፎች ሳይሰሩ በመቅረታቸው በአገርና ህዝብ ላይ ትልቅ ኪሳራ አድርሶ አልፏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአመራር ጥራትና ህዝባዊነት ላይ ከፍተኛ ክፍተት ነበረ፤ በተለይ ከፍተኛ አመራሩ (ከፊትም ከመጋረጃ ጀርባም የነበረው) እጅግ ብቃት ያነሰውና የግል ምቾት፣ ክብርና ጥቅም ያሉ ኢህዝባዊ ተግባራት ላይ የተዘፈቀ ነበረ፡፡ በዚህ ምክንያትም ከፍተኛ አመራሩ ምንም እንኳን ከባድ መስዋእት እየከፈሉ ህዝባቸው የሚያገለግሉ የታችኛው እርከን አመራሮች መኖራቸው ቢስተዋልም በአጠቃላይ ግን ግዜያዊ አስተዳደሩ በህዝብ ተስፋ እንዲቆረጥበት፣ እንዲናቅ፣ እንዲጠላ ቀጥሎም የሽብር ቡዱኑ እንዲያንሰራራ ምክንያት ሆኗል፡፡

ከዚህ በባሰ ሁኔታ ከፍተኛ አመራሩ የተጣለበት እጅግ ትልቅ ህዝባዊና መንግስታዊ ኃላፊነት ዘንግቶ ጥቃቅንና ግዜያዊ የስልጣን ኔትዎርኮች በመፍጠር የሌብነትና የሙስና ተግባራት ላይ በሰፊው ሲሰማራ ታይቷል፡፡ ይህ እዉን ለማድረግም በየደረጃው የነበሩ የተሻለ የትግል መሰረት፣ ህዝባዊ ተቀባይነትና አላማ እንዲሁም የላቀ የመሪነት ብቃት የነበራቸው አመራሮች በተለያዩ ሴራዎችና የጨረባክሶች እንዲዋከቡና ከኃላፊነት እንዲርቁ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ይህ ሁሉ ድክመትና የውስጥ ሴራ የሽብር ቡዱኑ ለማስወገድ ወይም ለህግ ለማቅረብ እንዲሁም የትግራይ ህዝብ የአገራዊ ለዉጡ ተቋዳሽ ለማድረግና ወደ አዲስ የዴሞክራሲና የልማት ምዕራፍ ለማሸጋገር በእጃችን የገባው ወርቃማ እድል እንዲባክን በር ከፍቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አገራችንና መላ ህዝባችን አሁንም የጦርነት አዙሪት ውስጥ እንዲዳክሩና የፌዴራል መንግስትና የአገር መከላከያ ሰራዊታችን ፖለቲካዊ፣ ፋይናንሳዊና ታሪካዊ ኪሳራ እንዲደርስባቸው ምክንያት ሆኗል፡፡

በፋይናንስ ረገድ ብቻ ሲታይ 100 ቢልየን ብር የግዜያዊ አስተዳደሩ እንዲሰራቸው ለታሰቡት ስራዎች ወጪ መደረጉ ይታወቃል፤ ይህ የዘንድሮ ጠቅላላ አገራዊ ባጀት 20% የሆነው ወይም የታላቁ የህዳሴ ግድብ አሁናዊ ወጪ ግማሽ የሚያክል ከፍተኛ የህዝብና የመንግስት ሃብት በትክክል ለታለመለት አላማ ስለመዋሉ እስካሁን ማረጋገጫ አልቀረበበትም፤ የትግራይ ህዝብም በዚህ መጠንና ደረጃ የታገዘበት ሁኔታ በማንኛውም ግዜ አልታየም፡፡

እንደብዙዎች ግምትና መረጃ ከሆነ ይህን ያክል ግዙፍ ሃብት የግዜያዊ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች (ከፊትም ከመጋረጃ ጀርባም የነበሩት) እንዳባከኑት፣ ልግላቸው ጥቅም እንዳዋሉትና ሆን ተብሎ በታቀደና በተዝረከረከ ሁኔታ ለአሸባሪው ቡዱን እንዲደርሰው መደረጉ ያምናሉ፡፡ ይህ ማለት አሸባሪው ቡዱን ዳግም እንዲያሰራራና እንዲደራጅ የግዜያዊ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ትልቅ ሚና በመጫወት በትግራይ አዲስ ትውልድና በትግራይ ህዝብ ተስፋ፣ በመከላከያ ሰራዊት ክቡር መስዋእትነት፣ በፌዴራል መንግስት ቀና ፍላጎትና በመላ የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት ላይ ከፍተኛ ደባ ተፈጽሟል፡፡

ስለሆነም በገንዘብ ረገድ ብቻ ይህንን ያክል ግዙፍ የመንግስትና ህዝብ ሃብት ባባከኑ አካላት ላይ እየተካሄደ ያለው ምርመራ ተፋጥኖና ተገባድዶ በአስቸኳይ በህግ ፊት መቅረብ አለባቸው፡፡ ለዚህም እያንዳንዱ ዜጋ የ100 ቢልየን ብር ሃብት የ100+ ሚልየን ህዝብ ጉዳይ ነው በማለት ፍትህ መጠየቅ አለበት፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

‹‹ሸኔ አሸባሪው ህወሓትን ወደ ስልጣን የመመለስ እንጂ ወደ ጫካ የሚወስድ የኦሮሞ ጥያቄ የለውም››

Next Story

የትህነግ ስትራቴጂ -መፅሐፍ- ቅኝት {መስፍን ማሞ ተሰማ – ሲድኒ አውስትራሊያ}

Go toTop