በምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጀርሳ ለፎ ወረዳ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የስምንት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ። የኤጀርሳ ለፎ ወረዳ ትራፊክ ፖሊስ ተቆጣጣሪ ዋና ሳጂን ፍቃዱ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ትላንት ማምሻውን በወረዳው ለገ ሁሉቆ በተባለ አካባቢ ነው።
ከአዲስ አበባ ወደ ጊንጪ ሲጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3– 30485 ኦሮ የሆነ የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ከአምቦ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ ከነበረ ኮድ 3 –52989 ኦሮ የህዝብ ማመላለሻ ቅጥቅጥ አይሱዙ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ አደጋው መድረሱን ተናግረዋል።
በአደጋው የሚኒባሱ አሽከርካሪን ጨምሮ ሚኒባሱ ውስጥ የነበሩ የ8 ሰዎች ህይወት ወዲያው ማለፉንም ተናግረዋል።
በሚኒባሱ እና በአይሱዙ ተሸከርካሪ ውስጥ የነበሩት ጉዳት የደረሰባቸው ስድስት ሰዎች በጳውሎስ ሆሲፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በአደጋው ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች አስከሬን ለየቤተሰቦቻቸው መሰጠቱን የገለጹት ዋና ሳጂን ፍቃዱ የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ኢዜአ