የታምራት ገለታ አዲስ ጨዋታ

December 2, 2018

ዶ/ር አብይ አህመድ ሰሞኑን “ጥፍር ሲነቅል ሕዝብን ያላማከረ፤ ጥፍር መንቀል ሕጋዊ አይደለም ስንለው ብሔሩ ውስጥ ለመደበቅ ይሞክራል” በማለት ወንጀለኞች ከተጠያቂነት ለማምለጥ ብሔራቸውን መደበቂያ እንደሚያደርጉ በአጭር ቃላት ገልጸውልን ነበር:: ይህ አባበል መቀሌ ላይ ለተደበቁት የሕወሓት ወንጀለኞች ብቻ ሳይሆን ዛሬ ለጠንቋዩ ታምራት ገለታም ሰርቷል::
https://www.youtube.com/watch?v=a-vz39roM74
ከሁለት ወር በፊት በምህረት የተፈታው ጠንቋዩ ታምራት ገለታ (እያንጓለለ) ዛሬ ሰላሌ ከተማ ውስጥ ለጀዋር መሐመድ በተደረገ ስነስርዓት ላይ ባደረገው ንግግር ‘1000 ጠንቋይ ባለበት ሀገር ከፍተኛ ስቃይ, ስም ማጥፋት፣ እስርና እንግልት የተፈፀመብኝ ኦሮሞ ስለሆንኩ ነበር” በማለት መናገሩ በሰፊው እየተናፈሰ መነጋጋሪያም እየሆነ ነው::

ባለአውሊያ” እና ”ባለከራማ” ነኝ በማለት ከአሥር ዓመት በላይ በጥንቆላ ሥራ ላይ ተሰማርቶ የነበረው ታምራት ገለታ በስድስት ክሶች ፍርድ ቤት ቀርቦ ተመስክሮበት ወንጀለኛ ተብሎ የተፈረደበት ሰው ነው:: የኦሮሞ ሕዝብ አይሰማውም እንጂ ዛሬ በብሄሩ ውስጥ ለመደበቅ መሞከሩ ታምራት ተከሶባቸው ወንጀለኛ የተባለባቸውን ወንጀሎች ዝርዝር ከፋይላችን አውጥተን ለሕዝቡ ለማሳየት አስገድዶናል:: አብረን እንቆይ::

ረቡዕ ነሐሴ 6 ቀን 2001 ዓ.ም. የዋለው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ”ባለአውሊያ” እና ”ባለከራማ” ነኝ በማለት ከአሥር ዓመት በላይ በጥንቆላ ሥራ ላይ ተሰማርቶ የነበረው አቶ ታምራት ገለታን ጥፋተኛ ያለበት; ንብረቶቹም ተወርሰው ለመንግሥት ገቢ እንዲሆኑ የወሰነበት; ዓቃቤ ሕግ በሞት ይቀጣልኝ ሲል የጠየቀበት ዕለት ነበር::

“ጠንቋይ” ታምራት ገለታ ከስድስት ግብረአበሮቹ ጋር ተከስሰው የነበሩባቸው ስድስት የተለያዩ ክሶች በዘጠኝ ሰዎች ሕይወት ማጥፋትና የመግደል ሙከራ በማድረግ፣ የሰው ገንዘብና ንብረት በማታለልና በማጭበርበር፣ ሴቶችን በመድፈር በሚሉ ሲሆን በነዚህ ክሶች በሙሉ በዚሁ ዕለት ከነ ግብረ አብሮቹ ጥፋተኛ ተብሏል::

በዕለቱ የጥፋተኝነት ውሳኔውን ፍርድ ቤቱ ካሰማ በኋላ ከሳሽና ተከሳሽ የቅጣት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ አቶ ታምራት በተደራራቢ ወንጀሎች የጥፋተኝነት ውሳኔ መሰጠቱን ገልጾ፤ ተከሳሹ በሞት ፍርድ እንዲቀጣለት ጠየቀ:: የተከሳሽ የአቶ ታምራት ገለታ ጠበቃ ደግሞ ደንበኛቸው ከዚህ ቀደም ወንጀል ሠርቶ የማያውቅ መሆኑንና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑን በመግለጽ ቅጣቱ እንዲቀልለት ጠይቋል።

በዕለቱ አቶ ታምራት ከጥንቆላ ውጪ ገቢ ያገኝበት የነበረ ሥራ እንዳልነበረው የገለጸው ፍርድ ቤቱ፤ በጥንቆላ ሥራ ያፈራቸው ንብረቶች ሙሉ ለሙሉ ውርስ ሆነው ለመንግሥት ገቢ እንዲሆኑ ችሎቱ ወስኗል። እንዲወረሱ የተወሰነባቸው 153 ሺህ 351 ብር በአቢሲኒያ ባንክ ዑራኤል ቅርንጫፍ፣ ሁለት መኪኖች፣ በፍቼ ከተማ የሚገኝ ሆቴልና መሬት፣ ወርቅና ልዩ ልዩ በፖሊስ ኤግዚቢትነት የተያዙ በርካታ ንብረቶች ነበሩ::

የከሳሽና የተከሳሽን የቅጣት ሃሳብ ፍርድ ቤቱ ካደመጠ በኋላ፤ ነሐሴ 12 ቀን 2001 ዓ.ም. ወንጀለኛ ተብሎ ተፈርዶበታል::

አቶ ታምራት ገለታና ግብረአበሮቹ የተከሰሱባቸው 6 ክሶች የሚከተሉት ናቸው::

1ኛ. ዓቃቤ ሕግ አቶ ታምራትን ጨምሮ በስድስት ግለሰቦች ላይ መሠረታቸው ክሶች ውስጥ በአንደኛው ክስ በአንደኝነት ዋናውን ተከሳሽ አቶ ታምራት ገለታን አስቀምጦ የነበረ ሲሆን፣ አቶ ደረጀ ስሜ፣ አቶ አዲሱ ሡልጣን እና ወ/ት ፍሬገነት ማርዬ ጨምሮ ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በወንጀሉ ዝርዝር ላይም “ተከሳሾቹ ሆን ብለው በግብረአበርነት ከ1992 ዓ.ም. እስከ 1999 ዓ.ም. ባለው ግዜ ውስጥ በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 22 ልዩ ስሙ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፊት ለፊት ሄለን ሕንጻ ጀርባ፣ አዳማ ከተማ ልዩ ቦታው ኬላ በተባለ አካባቢ፣ በኦሮሚያ ክልል ልዩ ቦታው ፊቼ ግራር ጃርሶ በተባለ ቦታ በሚገኙና ለጥንቆላ መሥሪያ በተዘጋጁ ቤቶች ውስጥ፤ ከተባባሪዎቹ ጋር በጋራ በመሆን አቶ ታምራት ማንኛውንም በሽታ እንደሚያድን፣ ለሰዎች ሀብት እንዲያገኙ እንደሚያደርግ፣ ዕድሜ እንደሚያስረዝም እና የእግዚአብሔርና የአላህ መልዕክተኛ እንደሆነ በመግለጽ ኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ የሥነ-ልቦና ተጽዕኖ በማሳዳር የተለያዩ ግለሰቦች በእምነቱ ስር እንዲወድቁ በማድረግ የግለሰቦቹን ገንዘብና ንብረት ለመውሰድ እንዲመቻቸው፤ ከተቀቀለ ጫት፣ ከአመድ፣ ከሰልፈር፣ ከሽቶ እና ሌሎች ምንነታቸው ያልታወቁ ነገሮች የተቀመመ እና ሃውዛ የሚሉትን ውኅድ ከብሽታቸው ለመዳን የመጡ ግለሰቦች እንዲጠጡ በማድረግና ወደ ሌላ ሕክምና ከሄዱ እንደሚሞቱ በመግለጽ እና በማስፈራራት ተከሳሾች ተግባራቸው ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት እያወቁና እየተረዱ የሆነው ይሁን ብለው የሰው ሕይወት እንዲጠፋ አድርገዋል” ሲል ከሷቸዋል።

2. የአቶ ታምራት ጥንቆላ እምነት ተከታይ የነበሩና በተለያየ ግዜ ከበሽታቸው ለመዳን ወደ ስፍራው በመሄድ ሕይወታቸውን አጥተዋል ያላቸውን ሟቾች ዓቃቤ ሕግ ሲዘረዝር፤ ተስፉ ተሾመ፣ ኢብራሂም ባርጌቾ፣ ፈጠነ፣ መሐመድ አረጋ፣ ተስፋዬ ታዬ እና መካ አብዱላሂ ይባሉ የነበሩ ስድስት ግለሰቦች ወደ ሕክምና እንዳይሄዱ በመከልከል ውኅዱን አጠጥተው ለመሞት ዳርገው ንብረታቸውን ወርሰዋል ሲል፤ በዚህ ድርጊታቸው በ1949 ዓ.ም. የወጣውን የወ/መ/ሕ/ቁ32/1/ሀ/ለ፣ 58/1/፣ 522/1/ሀ/ሐ የተመለከተውን ተላልፈዋል ሲል አንቀጽ ጠቅሶባቸዋል።

ሁለተኛው ክስ፦ በአንደኛው ክስ የተከሰሱት አራቱም ተከሳሾች የተከሰሱ ሲሆን፤ ወሰኔ ፈረደ ትባል የነበረችውን የጥንቆላ እምነቱ ተከታይ የምትሠራው የመጠጥ ግሮሰሪ ሥራ እንደማይሳካላትና መድኃኒት እንደተደረገባት በማሳመን የግሮሰሪዋን ቁልፍ በ80 ሺህ ብር ሸጣ ወደ ቤቱ እንድትገባ ካደረገና ገንዘቡን ላስቀምጥልሽ በሚል ዘዴ ተቀብሎ ወደ ሐኪም ቤት እንዳትሄድ በማሳመን ውኅዱን በተደጋጋሚ እንድትጠጣ ካደረጉ በኋላ ሕመሙ ሲጸናባት አዳማ ወስደው ቤት ተከራይተው እንድትቀመጠጥና እዛው እንድትሞት በማድረጋቸው በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ፣ 58/1/ለ እና 539/1/ሀ/ሐ የተመለከተውን በመተላለፋቸው በዚህ አንቀጽ ስር ጥፋተኛ ተብለው እንዲቀጡለት ጠይቆ ነበር። በዚህ አንቀጽ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ደግሞ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት እንደሚቀጡ ተደንግጓል።

ሦስተኛው ክስ፦ በ1995 ዓ.ም. አራቱ ተከሳሾች ሄለን ሕንጻ ጀርባ እና አዳማ በሚገኙ የጥንቆላ ቤቶች ውስጥ የኤች.ኤይ.ቪ. ሕመምተኛ የሆነች አንዲት ግለሰብ የምትወስደውን መድኃኒት አቋርጣ ከሱ ጋር ጫት በመቃም ወደ ጥንቆላው ቤት ብትመላለስ እንደሚያድናት በማሳመን በአቶ ታምራት ትዕዛዝ በወ/ት ፍሬገነት ቀማሚነት ተበጥብጦ የተሰጣትን ውኅድ በመጠጣቷ ሕመሟ ተባብሶ ሰውነቷ ሽባ ሆኖ ልትሞት ስትል በቤተሰቦቿ ጥረት ውጭ ሀገር ሄዳ ብትታከምም ልትሞት ችላለች ያለው ዓቃቤ ሕግ ለዚህ ከባድ የሰው አገዳደል የወንጀል ሙከራ በ1949 ዓ.ም. የወጣውን የወ/መ/ሕ/ቁ32/1/ሀ/ለ፣ 58/1/፣ 522/1/ሀ/ሐ የተመለከተውን ተላልፈዋል ሲል፤ ዕድሜ ልካቸውን በጽኑ እስራት ወይም በሞት የሚያስቀጣቸውን አንቀጽ ጠቅሶባቸዋል።

በአራተኛው ክስ፦ አራቱ ተከሳሾችና በመሞቱ ምክንያት ክሱ የተቋረጠው አምስተኛው ተከሳሽ በጋራ ሆነው በካንሰር በሽታ የተያዘች እህቱን ለማዳን ገብቶ የነበረን አቶ መንግሥቱ የተባለ ግለሰብ በጥንቆላው እምነት ስር እንዲወድቅ ካደረጉት በኋላ፤ ከደምወዙ አስር ከመቶ ለስምንት ዓመት እንዲከፍል፣ ለአቶ ታምራት ልደት በየዓመቱ የሁለት ሺህ ብር ኬክ እንዲያቀርብ፣ ለመንታ ልጆቹ ልደት በየዓመቱ አንድ ሺህ ብር ለአራት ዓመት እንዲሰጥ፣ በየዓመቱ ለድግስ 200 ብር እንዲያስገባ እና 50 ሺህ ብር ላስቀምጥልህ በሚል ወስደውበት ለአባቱ ቀብር ሄዶ ሲመጣ እንዳይገባ ተከልክሎ መባረሩን ክሱ ይዘረዝራል።

አቶ አረጋ ይማምና ወ/ሮ ራህማ ሰይድ የተባሉ ግለሰቦች፤ ልጃቸውን ሟች መሐመድ አረጋን ለማዳን እንደገቡ በዛው እንዲቀሩ ተደርገው ሴት ልጃቸውን ውጪ ለመላክና ቤታቸው መድኃኒት ስለተደረገበት እንዲሸጡት በማሳመን እና ከሽያጩ ላይ አስራት እንዲከፍሉ በማሳመን 55 ሺህ ብር ለልጃቸው መላኪያ 13 ሺህ ብር ወስዶ በሀብታቸው ላይ ጉዳት እንዲደርስባቸው በማድረጋቸው፤

ከአንድ ግለሰብ 20 ሺህ ብር፣ ከሌላኛው 400 ሺህ ብር፣ ንግድ ውስጥ እንገባለን በሚል ከሦስተኛው ሰው 150 ሺህ ብር፣ አንዱን ውጭ እልከዋለሁ በሚል 35 ሺህ ብርና ከሆድ ሕመም እፈውሰዋለሁ ያለውን ሌላኛውን 60 ሺህ ብር፤ በድምሩ 95 ሺህ ብር በመውሰዳቸው በቀላል እስራት ወይም እንደነገሩ ከባድነት እስከ አምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና መቀጮ የሚያስቀጡለት ዓቃቤ ሕግ አንቀጽ ተጠቅሶባቸዋል።

አምስተኛ ክስ፦ አቶ ታምራትና ወ/ሮ አልሳቤጥ ሆነው አንዲት ግለሰብን አታለው በማስፈረም የሰው ቤት የራሳቸው በማድረጋቸው በከባድ አታላይነት ተከሰዋል። በዚህ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከአስራ አምስት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና እስከ ብር 50 ሺ በማይበልጥ መቀጮ የሚያስቀጣቸው አንቀጽ ተቅሶባቸዋል።

በስድስተኛው ክስ፦ በዚህ ክስ አቶ ታምራት ብቻ የተከሰሰ ሲሆን፤ ከሕመማቸው ለመዳን የመጡ ሦስት ሴቶችን አስገድዶ ደፍሯል የሚል ክስ ቀርቦበታል። በዚህም እስከ አስር ዓመት ሊያስቀጣ የሚችል አንቀጽ ተጠቅሶበታል።

Previous Story

እነገዱ አንዳርጋቸው አሜሪካ ሲገቡ የተደረገላቸው አቀባበል – Video

Next Story

የሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር የተጠረጠሩባቸው ሕገወጥ ግዥዎች ይፋ ተደረጉ

Go toTop