የደቡብ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር አቶ ተስፋዬ ታፈሰ በክልሉ 42 ሚሊዮን 284 ሺ 908 ብር ጉድለት መታየቱን ተናገሩ
አቶ ተስፋዬ ከመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት ከተካሄደባቸው መሥሪያ ቤቶች የገንዘብ አስተዳደር ሥርዓት ሕጉን የተከተሉ መሆኑን ለማረጋገጥ በተደረገው ኦዲት ስምንት መሥሪያ ቤቶች የገንዘብ አያያዛቸው ላይ ጉድለት መኖሩ መታወቁን ጠቁመው ‹‹በእነዚህ መሥሪያ ቤቶች 275 ሺ 49 ብር የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ተገኝቷል፡፡ የክልሉ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ድርጅት 155 ሺ 316 ብር፤ የክልሉ የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት 67 ሺ 87 ብር በማጉደል ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡›› ብለዋል፡፡
ጨምረውም ‹‹በክልሉ የፋይናንስ አስተዳደር ሕግ መሰረት በተቋማት ያለው የገንዘብ መጠን በየወቅቱ ይቆጠራል፡፡ በቆጠራ ሪፖርትና በሂሳብ መግለጫዎች ላይ የሚሰፍረው አሃዝ እኩል መሆን አለበት፡፡ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ በሂሳብ መግለጫ ሪፖርት የተደረገውና በቆጠራ በተገኘው ገንዘብ መካከል በ59 መሥሪያ ቤቶች 42 ሚሊዮን 284 ሺ 908 ብር በማነስ ታይቷል፡፡›› ብለዋል፡፡ በ133 መሥሪያ ቤቶች ላይ በወቅቱ መወራረድ ሲገባው ያልተወራረደ 629 ሚሊዮን 982 ሺ ብር እንዳገኙ ያስረዱት ዋና ኦዲተሩ ሥራ ያልተሠራበትም ካለ ተለይቶ ወደ መንግሥት ካዝና መመለስ የነበረበትና ሥራ ተሠርቶም ከሆነ መረጃዎች ቀርበው መወራረድ የነበረባቸው ቢሆንም ምንም ሰነድ እንዳልተገኘ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ኦዲት በምናደርግበት ጊዜ በ137 መሥሪያ ቤቶች 128 ሚሊዮን ብር ማስረጃ ሳይቀርብ፣ የተሟላ ማስረጃ ሳይኖርና ህጋዊ ባልሆነ ማስረጃ ተወራርዶ እንዲሁም ተመዝግቦ ተገኝቷል፡፡›› ያሉት አቶ ተስፋዬ ይህ በመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መሰረት ያልተፈፀመ በመሆኑ ሕጋዊ ያልሆነ ሥራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ወደ 13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር፣ ፖሊስ ኮሚሽን 9 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር፣ የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የሲዳማ ዞን ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ማስረጃ ሳይቀርብ፣ የተሟላ ማስረጃ ሳይኖርና ህጋዊ ባልሆነ ማስረጃ የወጪ ሂሳብ አወራርደው ከተገኙት መሥሪያ ቤቶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ኦዲተሩ ተናግረው በመጨረሻም ‹‹በሕጉ መሰረት ያልተሟላ ማስረጃ ሳይኖር ሂሳብ አወራርዶ መገኘት ያስጠይቃል፡፡ እኛም በላክነው ሪፖርት ይህን የፈፀሙ አካላት በሕግ መጠየቅ እንዳለባቸው አሳውቀናል፡፡›› ብለዋል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=cKOwRaexXZ4&t=4s