ትግላችን የኢትዮጵያን ህዝብ ማዕከል ያደረገ በኢትዮጵያ ህዝብ የታጀበና በኢትዮጵያውያን ላይ የሚተማመን ሊሆን ይገባል

October 3, 2013

መስከረም 22 ቀን 2006 ዓ.ም.

Oct 2,  2013

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሽንጎ በመሠረታዊ ሰነዶቹ ላይ በግልጥ እንዳሰፈረው ለምሥረታው ዋና ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ በዋናነት ሀገራችን ኢትዮጵያ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተገፈፉባት፣ ዜጎች በእኩል የማይታዩባት፣ በዘርና በጎሳ እንዲከፋፈሉ የተደረገባትና አንድነቷን አደጋ ላይ የሚጥል አምባገነን ሥርዓት የተንሰራፋባት መሆኗን በማጤን፣ ይህንን አፋኝና አምባገነናዊ ሥርዓት አስወግዶ በህገ-መንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመተካት የተባበረ ትግል እንደሚያስፈልግ በማመን ነው።

የሸንጎው ዋና መሰባሰቢያውና ትልቁ ትኩረት ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ የአባል ድርጅቶችንና ግለሰቦችን በኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት፤ የሕዝቡ የሥልጣን ባለቤትነትና ሉዓላዊነት ጽኑ ዕምነት ማረጋገጥ ነው::

በሀገራችን ውስጥ ለመሠረታዊ መብቶች መጣስ፤ ለአንድነታች መናጋትና የማያባራ የአመጽ አዙሪት ውስጥ ለመውደቃችን በዋናነት ተጠያቂው የገዥው ህወሓት/ኢህአዴግ ፖሊሲና ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የተዘረጋው አፋኝ ሥርዓት ነው። የሀገራችንን አንድነትም ከእለት ወደ እለት አሳሳቢ ወደሆነ አደጋ እየገፋው የሚገኘው በዋናነት ይኅው ገዥው ህወሓት/ኢህአዴግ ነው።

ይህ አደጋ እንዲቆም፤ አዙሪቱም እንዲሰበርና እንዳይቀጥል ለማድረግ ደግሞ  የሥርዓት ለውጥ ማምጣትን የግድ ይላል።

የሥርዓት ለውጥ ማምጣት ስንል ትግላችን የህወሓት/ኢህአዴግን የግፍ አገዛዝ ማሰወገድ ብቻ ሳይሆን የሀገራችንን አንድነት በምንም መልኩ ለድርድር በማያቀርብ ሁኔታ የህዝባችን መብት ሙሉ ለሙሉ ማስከበር፣ ፍትህ የሰፈነበት ሥርዓትን መመሥረትና መገንባትን ይመለከታል። ይህ ብቻ ሳይሆን በህወሓት/ኢህአዴግ ፀረ-አንድነት ፖሊሲ አንድነቷን ያጣችውን፣ ዳር ድንበሯ የተሸራረፈውን ኢትዮጵያን በአካባቢውም ሆነ በአፍሪካ ተገቢና ታሪካዊ ቦታዋን እንድትይዝ የሚያስችል መሠረትን መጣል ነው።

ይህንን ሁሉ ተግባራዊ ለማድረግ የአንድነትና የዴሞክራሲ ሀይሎች አካሄድ ምን መሆን ይገባዋል? የሚለውን ጥያቄ ደግመን ደጋግመን ልንመክርበትና ልንመረምረው የሚገባን ጉዳይ ነው።

ህወሓት/ኢህአዴግ በህዘባችን ላይ የሚያካሂደው ግፍ ሞልቶ በመፍሰሱ የተነሳ ህወሓት/ኢህአዴግ ይወገድልን እንጂ የፈለገው ይምጣ የሚል አመለካከት አልፎ አልፎ ሲንጸባረቅ ይታያል። የዚህ ዓይነቱ አመለካክት በሥርዓቱ የመማረር ውጤት እንደሆነ ግልጽ ቢሆንም፣ ወደምንፈልገው ዘላቂ ሰላም፣ ብሄራዊ ጥቅምና የህዝብ መብት መከበር ሊያደርስ መቻሉ ግን እጅግ አጠራጣሪ ነው።

የአንድነትና የዴሞክራሲ ሀይሎች የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት በሚያካሂዱት ትግል ተገቢ የሚመስላቸውን የትግል ስልት የመምረጥና አስፈላጊውን ትብብር የመፍጠር መብታቸውን ሸንጎ ይገነዘባል።

ከነዚህ ድርጅታዊ መብቶች ጎን ለጎን መታየት የሚገባው ትልቁ ነገር ደግሞ የትግል ስልቱም ይሁን የትብብር ስምምነቶች ህዝብና ሀገርን የሚመለከቱ ሲሆን የአንድ ድርጅት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የወል እንደምታ ስለሚኖረው በጊዜያዊነትም ይሁን ለዘለቄታው በህዝባችንና በሀገራችን ላይ በቀጥታም ይሁን በተዛዘዋዋሪ የሚኖረውን ጠቀሜታና ጉዳት መመርመር የግድ ነው።

በዚህ አንፃር በአሁኑ ሰዓት በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው የህወሓት/ኢህአዴግ ዋነኛ አጋር የነበረው ሻኣቢያንና መሪውን ኢሳያስ አፈወርቂን የተመለከተ ነው።

ታሪክ እንደሚያሳየን ኢሳያስም ሆነ እሱ የሚመራው ድርጅቱ ሻኣቢያ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን እንደ ጠላት በመመልከት የተዳከመችና የፈራረሰች ኢትዮጵያ እንድትሆን ምኞታቸው ብቻ ሳይሆን ሳያሰልሱ ሠርተዋል። ከዚህም በመነሳት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚጻረር ተግባሮች ያራምዳሉ፤ ያስፋፋሉ፤ ይደግፋሉ። ከተቻላቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የነሱን አሻንጉሊት መንግሥት ለማንገስ ይጥራሉ። የማይሳካ ሲመሰላቸው ደግሞ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ መንግሥት እንዳይኖር በሁሉም መልክ ይጥራሉ። ይህን ከአርባ  ላላነስ ተከታታይ ዓመታት የተካሄደን እውነታ መዘርዘር ባያስፈልግም ለአብነት ያክል ግን ላለፉት 22 ዓመታት ካካሄዷቸው ፀረ-ኢትዮጵያ ተግባሮች ውስጥ የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል።

  • በደርግ የሥልጣን መጨረሻ ወቅት ወደ አዲስ አባባ በተደረገው ጉዞ ህወሓት/ኢህአዴግን በከፍተኛ ወታደራዊ ኃይል አዲስ አባባ እንዲደርስ ድጋፍ የሰጠው ሻኣቢያ ነበር።
  • የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በተወሰነበት የ1983 የለንደኑ ኮንፍርንስ ኢትዮጵያዊ ህብረ-ብሄር ድርጅቶች እንዳይሳተፉ እነሱ ከተሳተፉ “እኛ ከውይይቱ እንወጣለን “በማለት በሀገራቸው ጉዳይ ድምጻቸው እንዳይሰማ ያደረጉት ህወሓትና ሻዕቢያ በጣምራ ነበሩ።
  • በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ከኤርትራ ምድር የጥርስ ወርቃቸው ሳይቀር እያወለቀ ንብረታቸውን ዘርፎ የገደለውን ገድሎ በባዶ እግራቸው  እንዲባረሩ ያደረገው ሻዕቢያ ነበር፡
  • ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር በማበር ህጋዊነት በሌለውና የኢትዮጵያ ጥቅም በምንም መልኩ ግንዛቤ ውስጥ ባላስገባ ሁኔታ ኤርትራን ገንጥሎ ህዝቧን የለያዩ ኢትዮጵያንም የባህር በር አልባ ያደረጓት ህወሓት/ኢህአዴግና ሻኣቢያ በጥምረት ናቸው፡
  • ጦርነት እስከገጠሙበት እስከ 1990 ድረስ የሀገሪቱን ሀብት ዓይን ባወጣ ሁኔታ ይቀራመቱት የነበሩት ያው ህወሐትና ሻኣቢያ ነበሩ፡
  • በ1990 ጦርነትን በማንሳት በወራት ውስጥ ከ70ሽህ ህዝብ በላይ ለእልቂት የዳረጉት ያው ሻኣቢያና ህወሓት/ኢህአዴግ ናቸው፡
  • በዚሁ ጦርነት ጊዜ የህጻናትን ትምህርት ቤት በአውሮፕላን በመደብደብ የኢትዮጵያውያን ህጻናትን ደም ያፈሰሰው ሻዕቢያ ነው፡
  • ከዚያ ወዲህም ኢትዮጵያን ማዳከም ወይም መገንጠል ዓላማችን ብለው የተነሱትን ሁሉ አቅፎ ደግፎ የሚያሰማራው በዋናነት ሻዕቢያ ነው።

እነዚህና ሌሎችም ጉዳዮች ሁሉ የሚያመለክቱት ህወሓት/ኢህአዴግን ስንታገል ጎን ለጎን ከሌሎች በኩል የሚጠብቁንን አደጋዎች በጥንቃቄ ካላመዛዘን የህዝባችን መብትና የነጻነት ፍላጎት እንዲሁም የሀገራችንም ህልውና ለሌላ ዙር አደጋ እንደሚጋለጥ ነው።

በመሆኑም ሸንጎው ይህን ሁሉ ሴራ ተሽክሞ የሚጓዘውን ሻዕቢያን እና መሪውን ኢሳያስን ለሀገራችን ነጻነት ተቆርቋሪና ለልዕልናዋ መከበር የትግል አጋር አድርጎ አይመለከተውም፤ አይቀበለውም፤ አያስበውምም።

ይህን እውነታ በትክክል አለመረዳት ወይንም አጣጥሎና ዝቅ አድርጎ ማየት ወይንም የሻዕቢያን ድለላ እንደ እውነተኛ ቃል መውሰድና የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲቀበለው መሞከር በሀገራችን ሉዓላዊነትና አንድነት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በትክክል አለመገንዘብ ወይንም አደጋውን ሆነ ብሎ ዝቅ አድርጎ ከመረዳት የሚዘል ሊሆን አይችልም።

ኤርትራንና ሻዕቢያን በተመለከተ የኢትዮጵያ ህዝብ ገና ብዙ ያልተዘጉ አጀንዳዎች፤ ያልተቋጩ ጉዳዮች አሉት። ይህ ጉዳይ በመሠረቱ ነፃ መንግሥት መሥርተን የኢትዮጵያን ድንበርና ጥቅም አስጠብቀን ከመጓዝ ጋር እጅግ የተሳሰረ ነው። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅት ይህንን ታላቅ ሀገራዊ አጀንዳ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንዲዳፈንና እንዲደበዝዝ ከሚያደርጉ እርምጃዎች ራሱን መቆጠብ አለበት እናላለን። አደጋው ሲታይ ደግሞ የማስጠንቀቂያ ደወል ማሰማት ሀላፊነት ከሚሰማው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚጠበቅ ነው።

የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው የሚለው ብሂል ከሁኔታዎች ጋር ተገናዝቦ የሚታይ ጉዳይ ነው። በዚህ አንጻር ምንም እንኳን ሻዕቢያ ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር ጊዜያዊ ግጭት ቢኖረውም ሻዕቢያና መሪው ኢሳያስ አንድነቷ የተከበረ ጠንካራ ኢትዮጵያን ማየት የማይፈልጉ በመሆናቸው የኢትዮጵያ ወዳጅ ሆነውም አያውቁም፤ ሊሆኑም አይችሉም። በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነቷ የተረጋገጠባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እታገላለሁ የሚል ኢትዮጵያዊ ድርጅት ሁሉ ይህንን እውነታ ሳያመነታ በድፍረት መናገር ይጠበቅበታል።

ይህ የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ መሆኑን እያስረገጠ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ላይ የማይደራደር መሆኑንም ሊያረጋግጥ ይወዳል።

በኛ በኩል ኢትዮጵያችን ዳግም እጇን የማታነሳ ደካማ ሀገር እንድትሆንና እንድትበታተንም ያጭርና የረጅም ጊዜ እስትራተጂ አውጥተው ሌት ከቀን ከሚደክሙት ጋር መሠረታዊ ራዕያችን በፍጹም የማይገናኝ ነውና አንተባበርም።

የህወሓት/ኢህአዴግን አስከፊ የዘረኛነትና የጭቆና ሥርዓትን አስወግዶ አዲስ ሥርዓት የመገንባት ትግላችን የኢትዮጵያን ህዝብ ማዕከል ያደረገ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ የታጀበና በኢትዮጵያውያን ላይ የሚተማመን ሊሆን ይገባዋል። ትግሉ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ምሽጋችንም ደጀኑም የኢትዮጵያ ህዝብ ነው።

የሀገራችን አንድነትና ሉዓላዊነት በቆራጥ ልጆቿ ትግል ይከበራል!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

Previous Story

አወጋን በወልቃይት ጎሮ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የአማራ ልጆች እንዳይማሩ መከልከላቸውን ገለጸ

Next Story

ሕዝባዊ ጥያቄዎችን በማፈንና አደባባይ በመከልከል መገደብ በህግም በታሪክም ያስጠይቃል!! ሲሉ አንድነትና በ33ቱ ፓርቲዎች በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ

Go toTop