ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ “አዲሱ አበባ ቆራጭ” ሆኑ

October 7, 2013

ከእንግዳ መቀበልና መሸኘት፣ ከአበባ መትከልና ከአበባ መቆረጥ ያለፈ ስልጣን የሌለው እየተባለ በሚተችበት የፕሬዚዳንትነት ሥፍራ ላይ ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ መሾማቸው ታወቀ።

ኢሕአዴግ በተቆጣጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2006 ዓ.ም. ባደረጉት የጋራ ስብሰባ በቱርክ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ ያሉትን ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን በአዲስ አበባ ቆራጭነት ሾመዋል።

በኢሕአዴግ ዘመን ኢትዮጵያን በሽግግሩ ወቅት አቶ መለስ፣ ዶ/ር ነጋሶ፣ መቶ አለቃ ግርማ የመሩ ሲሆን ዶ/ር ሙላቱ የኢሕአዴግ ዘመን 4ኛው፣ ከሽግግሩ በኋላ ደግሞ 3ኛው ፕሬዚዳንት ሆነዋል።

በርከት ያሉ የፖለቲካ አስተያየት ሰጪዎች ለዘ-ሐበሻ እንደገለጹት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ከኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ተመረጠ ለሚል የፖለቲካ ጥቅም እንጂ ስልጣኑን ከያዙ በኋላ ምንም ሊፈይዱበት የማይችሉበት መሆኑን ይናገራሉ። በተለይ እንደ ሕዝብ ብዛት ምንም ስልጣን የሌለው ፕሬዚዳንትነት ሳይሆን የጠ/ሚ/ርነት ስልጣን ነው ለኦሮሞ ተወላጅ የሚገባው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች አቶ ሙላቱ ለጠ/ሚ/ር ወይም ለውጭ ጉዳይ ሚ/ር የሚያበቃ እውቀት ያላቸው ቢሆንም የኢሕ አዴግ ዘመን አበባ ቆራጭ ከመሆን ያለፈ ምንም ሥራ ሊሰሩ ይችላሉ በሚል እንደማይጠብቁ ይናገራሉ።

የዶ/ር ሙላቱ ፋክት ፋይል
(ከመንግስታዊ ሚዲያዎች የተገኘ)

– ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ውርቱ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ አርጆ ወረዳ በ1949 ዓ.ም ተወለዱ።
– የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአርጆ እና በአዲስ አበባ ተከታትለዋል።
– በ1974 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ፍልስፍና እንዲሁም በአለም አቀፍ ግንኙነት ከዚያም በፍልሰፍና የዶክቶሬት ድግሪያቸውን።
– ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን በተለያዩ መስኮች ያከናወኑ እና በመምህርነትም ያገለገሉ ሲሆን ፥ አማርኛ ፣ ኦሮምኛ ፣ እንግሊዘኛ ፣ ቻይንኛ እንዲሁም ፈረንሳይኛ ቋንቋን መናገር እና መጻፍ ይችላሉ።
– ከ1993-1994 ዓ.ም የኢፌዴሪ የግብርና ሚኒስትር ፣ ከጥቅምት 1994 እስከ 1998 ዓ.ም በፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤነት እንዲሁም ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በቱርክ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።
– ዶክተር ሙላቱ በትዳር ህይወታቸው የአንድ ወንድ ልጅ አባት ናቸው።

Previous Story

Hiber Radio: የተስፋዬ ገ/አብ ምስጢሮችን ይፋ ያደረገው አክቲቪስት ይናገራል

Next Story

ታማኝ እና ቴዲ ትላንት ምሽት (ከክንፉ አሰፋ) ጋዜጠኛ

Go toTop