በቡድናችን ድል ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ከወጡት መካከል መኪና ተገልብጦ ሁለት ሰዎች ሞቱ

June 17, 2013

በባህርዳር ከተማ በብሄራዊ ቡድናችን ድል ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ከወጡት መካከል በአንድ መኪና ላይ ደስታቸውን ሆነው ሲገልጹ ከነበሩ ወገኖቻችን መካከል 2ቱ ሕይወታቸው ሊያልፍ መቻሉ ተዘገበ። በሌላ በኩልም – ኢትዮጵያ ትናንት ደቡብ አፍሪካን ማሸነፉዋን ተከትሎ ምሽት ላይ በነቂስ ወደ አደባባይ ወጥተው ድጋፍ ካደረጉት የባህር ዳር ነዋሪዎች መካከል በዛ ያለ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች “የኮከብ ዓርማ የሌለውን ሰንደቅ ዓላማ በመልበሳቸው፣ እንዲሁም ‹‹ሰማያዊ ፤ሰማያዊ ደገመው ዋልያዊ››፣ “ኢትዮጵያዊው ለሰንደቅ አላማው ፤ለሰማያዊው ” እያሉ ደስታቸውን በመግለጻቸው፣ ከፌደራል ፖሊሶች ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተው ማምሸታቸውን የኢሳት ቲቪ በዛሬ ምሽት የዜና እወጃው ዘገቧል።
ፖሊሶች ሰንደቅ ዓላማውን ለመንጠቅ ባደረጉት ሙከራ አንዳንድ ወጣቶችን መደብደባቸውን የዘገበው ኢሳት ወጣቶችም “ለባንዴራችን እንሞታለን” እያሉ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ አራት ወጣቶች ክፉኛ መደብደባቸውን የገለጸው የባህርዳሩ ወኪላችን፣ ‹‹ ፌደራል የፓርቲ ቅጥረኛ ገዳይ ነው፤ ፤የወንድሞቻችን ደም ፈሶ አይቀርም” በማለት አስፓልት ላይ ቆመው ሲናገሩ ተደምጠዋል ሲል ዘጋቢዎቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
በግርግሩ መሀል አንድ ሚኒባስ በመገልበጡ ሁለት ወጣቶች ሲሞቱ 4 ደግሞ መቁሰላቸውን የገለጸው ቲቪው የባህርዳር ከተማ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት ኢንስፔክተር ኢሳ ሁለት ወጣቶች መሞታቸውን ቢያምኑም ከሰንደቃላማ ጋር በተያያዘ ከፖሊስ ጋር ተፈጠረ የተባለውን ግጭት ግን አስተባብለዋል ብሏል።

Previous Story

Sport: የኢትዮጵያን ደስታ የፊፋ ዜና አቀዘቀዘው

Next Story

Hiber Radio: ዩ.ኤን.ኤች. ሲ.አር ግብጻውያን በአገራቸው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን እንዲጠብቁ ጠየቀ

Go toTop