ኣባ ይፍቱኝ(በዉቀቱ ስዩም)

April 28, 2015

ኣባ ይፍቱኝ !
ሲኦል ኣለ ሲሉኝ፤ የለም ብየ ክጀ
የባልቴት ተረት ነው፤ በማለት ቀልጀ
ኣውቄ በድፍረት፤ በድያለሁና
ያንጹኝ በንስሃ፤ ያንሱኝ በቀኖና
ሲኦል ከነጭፍራው፤ በጉም ተሸፍኖ
እንዴት ሳላየው ኖርኩ፤ ካጠገቤ ሆኖ?
ኣባ ይፍቱኝ
ሰይጣን ብሎ ነገር፤ የተጭበረበረ
ዋዛ ነው ቧልት ነው፤ ብየ ኣስብ ነበረ
ይሄው እውነት ሆኖ፤ ዋዛና ተረቱ
ባይኔ በብረቱ
ዲያብሎስን ኣየሁት፤ በሸሚዝ ዘንጦ
እልፍ ግዳይ ጥሎ፤ ቸብቸቦ ጨብጦ፡፡
ኣባ
ልክ እንደ ብርሌ ፤ኣጥንት ሲከሰከስ
ኣባይን ኣዋሽን፤ የሚያስንቅ ደም ሲፈስ
ለምለም ፍጥረት ሁላ፤ ወደ ኣመድ ሲመለስ
ልክ እንደ ጧፍ ሃውልት፤ ምስኪኖች ሲጋዩ
ምድጃው ዳር ሆነው፤ ይሄንን እያዩ
ገሃነም ከላይ ነው፤ ብለው መሳትዎ
እስዎ እንደፈቱኝ ፤ እግዚሃር ይፍታዎ

Previous Story

Hiber Radio: በአሸባሪው አይኤስ የመን መግባት ኢትዮጵያውያን ስጋት ገብተዋል… ከ28 በላይ ኢትዮጵያውያንን በሊቢያ ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለው አይሲስ ላይ ከፍተኛ የአየርና የእግረኛ ጥቃት ተፈፀመበት… በደቡብ ምዕራብ ጋምቤላ የስደተኛ መጠለያ የሚገኝ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጥረት መንገሱ ተሰማ…. እና ሌሎችም

Next Story

የብአዴን አባላት በአማራው ሕዝብ ምላሽ የተነሳ ጭንቅ ውስጥ መውደቃቸው ተዘገበ

Go toTop