Health: ራስ ምታት! ዓይነቶቹ፤ ምልክቶቹና ህክምናው

May 21, 2013

ራስምታትን የማያውቀው ሰው የለም ለማለት ያስደፍራል፡፡ በህክምና ከጭንቅላት የሚነሳ ማንኛውም ህመም (የአይንና ጆሮ ህመምን ሳይጨምር) እንዲሁም ከኋላ በኩል ካለው የአንገት ክፍል መነሻ የሚነሳ ህመም፣ የራስምታት ይባላል፡፡ የራስምታት በራሱ በሽታ ሊሆን ይችላል፡፡ የበርካታ በሽታዎች ምልክት ሆኖም ይከሰታል፡፡ አንዳንዴ የራስ ምታት የገዳይ በሽታዎች ምልክት የሚሆንበት አጋጣሚዎች አሉ፡፡ የራስምታት በራሱ በሽታ ሲሆን፣ ሶስት አይነት መልክ ይኖረዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በህብረተሰባችን በብዛት የሚታወቀው ሚግሬይን የሚባለው የራስምታት ነው፡፡ ሌሎቹ (tension headache) እና (Cluster headache) ይባላሉ፡፡
ከሶስቱ የራስምታት ዓይነቶች (tension headache) ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ በብዛት ይታያል፡፡
ሚግሬይን የራስምታት (migraine headache) ከ (tension headache) በመቀጠል ከፍተኛ ስርጭት አለው፡፡ ይህኛው የራስምታት አይነት ህፃናትንና አዋቂዎችን ሊያጠቃ ይችላል፡፡ ከጉርምስና ወቅት በፊት ሁለቱም ፆታዎች እኩል በዚህ ህመም እንደሚጠቁ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከዚህ ዕድሜ በኋላ ግን በአብዛኛው ሲጠቁ የሚታዩት ሴቶች ናቸው፡፡ ከጠቅላላው ህብረተሰብ፣ ከወንዶች 16 በመቶ፣ ከሴቶች ደግሞ 18 በመቶ የሚሆኑት ይህ አይነት የራስምታት ይታያባቸዋል፡፡
ክላስተር የራስምታት (cluster headache) የሚባለው ስርጭቱ በጣም አነስተኛ (0.1 በመቶ) ሲሆን፣ 85 በመቶ የችግሩ ተጠቂዎች ወንዶች ናቸው፡፡
ሚግሬይን፣ ስር ሰደድ የሆነ የራስምታት አይነት ሲሆን በዘር የሚተላለፍበት እድልም አለ፡፡ የራስምታቱ የሚያናጋ እና የመውቀጥ አይነት ከፍተኛ የህመም ስሜት ይፈጥራል፡፡ ይህ አይነቱ የራስምታት በአብዛኛው በአንድ የጭንቅላት ክፍል ላይ ይበረታል፡፡ አንዳንዴ በግንባር አካባቢ፣ ሌላ ጊዜ በአይን ዙሪያ እንዲሁም በአንገት ጀርባ አካባቢ የህመም ስሜቱ ይፈጠራል፡፡ በአብዛኛው ሕመሙ የጭንቅላትን ቀኝ ወይም ግራ ክፍል የሚያጠቃ ሲሆን፣ ሁለቱንም የጭንቅላት ክፍል የሚያጠቃበት እድል አነስተኛ (ከጠቅላላው 1/3ኛው) ነው፡፡ ህመሙ አንዴ በቀኝ ቆይቶ በግራ የጭንቅላት ክፍል መፈራረቁ በተለይ የሚለይበት ፀባይ ሲሆን፣ በአንድ በኩል ብቻ ከቆየ (ከተደጋገመ) ከሚግሬይን የራስምታት ውጪ የሆኑ በሽታዎች (ለምሳሌ የጭንቅላት ዕጢ) መጠርጠር ይበጃል፡፡ የሚግሬይን የራስምታት የአካል እንቅስቃሴ ሲኖር (ለምሳሌ ደረጃ መውጣት) የሚቀሰቀስ አይነት ነው፡፡ ከየራስምታቱ ጋር ማቅለሽለሽና ማስመለስ፣ ተቅማጥ፣ የፊት አመድ መምሰል (መንጣት)፣ የእጅ እግር መቀዝቀዝ እንዲሁም በብርሃንና በድምፅ በቀላሉ የመረበሽ ምልክቶች ይታያሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ሚግሬይን የራስምታት ያለባቸው ሰዎች ብርሃንና ድምፅ ሽሽት በጨለማና ረጭ ባለ ቦታ መሆንን ተጠቂዎችና ቤተሰቦቻቸው ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምልክቶቹ ሲታዩ፣ የራስምታቱ ሊጀምር እንደሆነ በሚገባ ያውቃሉ፡፡
ሃያ በመቶ በሚሆኑ የበሽታው ተጠቂዎች ደግሞ ከራስምታቱ ትንሽ አስቀድሞ የሚከሰት እንዲሁም አንዳንዴ ከራስምታቱ ጋር አብሮ የሚቀጥል (aura) የሚባል ምልክት ያሳያሉ፡፡ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ላይ ደግሞ ምልክቶቹ (aura) ከራስምታቱ ውጪ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ እነኚህ ምልክቶች ከዕይታ ማዕከል ጀምሮ ወደ ውጪ የሚሄድ የተለያየ ቀለማት ያለው ብልጭታ፣ በእይታ ክልል ውስጥ ማየት የማይቻልበት ክብ ስፍራ መፈጠር ናቸው፡፡ ቀላል የሚባለው (aura) ምልክቶች፣ በአንዱ እጅ ላይ፣ በአፍና አፍንጫ አካባቢ፣ የራስምታቱ በተፈጠረበት የጭንቅላት ጎን የመጠቅጠቅ ስሜት መኖር ናቸው፡፡ የሚግሬይን የራስምታት ተጠቂ፣ ህመሙ ከተወው በኋላ ለሃያ አራት ሰዓታት ያክል የአቅም ማጣት፣ በድምፅና ብርሃን የመረበሽ ምልክቶች ያሳያል፡፡ በዚህ ጊዜ አንዳንድ የህመሙ ተጠቂዎች፣ ህመማቸው ሊያገረሽም ይችላል፡፡
ክላስተር የራስምታት (cluster headache)፣ በአንድ ሳምንት ወይም ወር ላይ ተጠቂውን በተደጋጋሚ አጥቅቶ፣ ከዚያ የወራት ወይም ዓመታት እረፍት ሰጥቶ እንደገና በመምጣት ይታወቃል፡፡ (cluster headache) ሲከሰት በቀን ሁለት ጊዜ ተጠቂውን የሚያሰቃይ ሲሆን፣ አንዴ የተከሰተው ህመም ከሰላሳ ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ተኩል ቆይቶ ይጠፋል፡፡ ህመሙ በየቀኑ በተመሳሳይ ሰዓት በመምጣት ይለያል፡፡ ተጠቂውን ከእንቅልፍ የሚቀሰቀስበት ሁኔታም የተለመደ ነው፡፡ እጅግ ሰቅጣጭ አይነት ሲሆን፣ አንዱ አይን አካባቢ ወይም ከአይን ጀርባ የተፈጠረ ይመስላል፡፡ አንዳንድ የበሽታው ተጠቂዎች፣ ህመሙን ‹‹አይኔ ውስጥ እሳት ተቀምጧል›› በማለት ይገልፁታል፡፡ የተጠቃው አይን ይቀላል፣ ያነባል፡፡ ህመም በተፈጠረበት የጭንቅላት ጎን (ወይም አይን) ያለው የአፍንጫ ክፍል (ቀዳዳ) ይታፈናል፣ እንዲሁም ንፍጥ ይወጣዋል፡፡ የዚህኛው አይነት የራስምታት ተጠቂዎች፣ ከሚግሬይን የራስምታት ተጠቂዎች በተቃራኒው ይቅበዘበዛሉ፣ ከወዲህ ወዲያ ይራወጣሉ፤ ጭንቅላታቸውን ከግድግዳ ጋር ያጋጩታል፡፡
የራስምታት በራሱ ጊዜ ሲከሰት (የበሽታ ምልክት ካልሆነ) ምክንያቱ የአንጎል የደም ስሮች መስፋትና በዚሁ የተነሳ በአንጎል ውስጥ በደም ስሮች አካባቢ ያሉ የነርቭ ስሮች፣ ከሰፉት የደም ስሮች በብዛት በሚወጡ ኬሚካሎች መለብለባቸው ነው፡፡ ይህ የነርቮች መቆጣት ነው እንግዲህ የራስምታት የሚባለው፡፡ እንደ ሜግሬይን ያሉ የራስምታት አይነቶች ከራስምታት ውጪ በሆኑ በተለያዩ ምልክቶች፣ ለምሳሌ ማስመለስ እና ማቅለቀሽለሽ የመታጀባቸው ምስጢር ደግሞ የራስምታቱ ጠቅላላውን የነርቭ ስርዓት ማወክ መቻሉ ነው፡፡ ለምሳሌ ሚግሬይን የራስምታት የሰውነትን (sympathetic nervous system) ያውካል፡፡ ይህ የነርቭ ስርዓት ሲነቃቃ (ሲታወክ) ደግሞ በስሩ ያሉ የሰውነት ስርዓቶች (ለምሳሌ የምግብ መፍጨት ስርዓት) ይታወካል፡፡ ለዚህም ነው ከሚግሬይን የራስ ምታት ጋር ብዙ አይነት የጤና መቃወስ ምልክቶች የሚታዩት፡፡
የበሽታ ምልክት ተደርጎ የሚቆጠረውን የራስምታት የሚያመጡ የተለያዩ ምክንቶች አሉ፡፡ በጭንቅላት ላይ ደረሰ አደጋ፣ በአንጎል ውስጥ የሚፈጠር ብግነት፣ የአንጎል ደም ስሮች ውስጥ የሚከሰት ጓጓላ፣ የአንጎል የደም ስሮች መለጠጥ፣ መሳሳትና መፈንዳት፣ በድንገት ከፍተኛ ደረጃ የሚደርስ የደም ግፊት፣ የጭንቅላት ላይ የደም ስሮች መብገን፣ በአይን ውስጥ ድንገት የፈሳሽ ግፊት መጨመር (ግላውኮማ)፣ በተደጋጋሚ ለካርቦን ሞኖክሳይድ ጋዝ መጋለጥ፣ የፓርኪንስንስ በሽታ፣ ጭንቀትንና ደም ግፊትን ለማከም የሚውሉ አንዳንድ መድሃኒቶች፣ ያለ ሐኪም የሚታዘዙ የራስ ምታት መድሃኒቶችን ያለ አግባብ መጠቀም፣ አንዳንድ የልብ ህመሞች (cardiac ischemia)፣ የአንጎል ውስጥ እጢ፣ ማጅራት ገትር፣ የመሳሰሉት ሁኔታዎች የራስ ምታት ያመጣሉ፡፡ የበሽታ ምልክት ተደርጎ የሚታየው የራስምታት፣ ለህይወት አስጊ የሆኑ እንደ የአንጎል እጢ፣ ማጅራት ገትር፣ በአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ ችግሮች ጠቋሚ ሊሆን ሲችል፣ ቀላል የሚባሉ ችግሮች እንደ ቡና ሱስ የማሳሉትንም ሊያሳይ ይችላል፡፡ በአብዛኛው ግን የበሽታ ምልክት የሆነው የራስምታትና ራሱ እንደ በሽታ የሚቆጠረው የራስምታት (migraine, clusture, tension) ተቀላቅለው በአንድ ሰው ላይ የሚታዩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ለምሳሌ (tension headache) ወይም በበሽታ ምክንያት የሚመጡ የራስምታት የሚግሬይን የራስምታትን ሊቀሰቅሱ ብሎም አብረው ሊታዩ ይችላሉ፡፡
የራስምታት አይነቶችን ለመለየት እንዲሁም የበሽታ ምልክት ይሁን ወይስ በራሱ በሽታ፣ ለመለየት የሚደረጉ የተለያዩ ምርመራዎች አሉ፡፡ በተለይ በበሽታ ምክንያት የሚታየውን የራስምታት መንስኤ ለማወቅ እንደ (MRI, CT scan) የማሳሰሉት መሳሪያዎች ወሳኝ ሲሆኑ፣ የደም ምርመራ ማድረግም ለራስምታቱ መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ የተለያዩ ችግሮችን (የማጅራት ገትርን ጨምሮ) ለመለየት ያስችላል፡፡ የራስምታትን መንስኤ በተለያዩ መሳሪያዎችና የላብራቶሪ ምርመራዎች መለየት ቢቻልም ሐኪም የሚያደርገው የአካል ምርመራና ከበሽታው የሚወሰደው መረጃ ግን በሽታውን ለመለየት ምትክ የለሽ ነው፡፡
የራስ ምታት እንዴት ይታከማል?
በሌሎች በሽታዎች የተነሳ የሚመጣውን የራስምታት ለማከም፣ በመጀመሪያ የራስምታቱ መንስኤ የግድ መለየት ይኖርበታል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ፣ የራስምታቱን ነጥሎ ማከም መሞከር ግን ስኬታማ ካለመሆኑም በላይ፣ መንስኤዎቹ ስር እንዲሰዱ ጊዜ ይሰጣል፡፡ የራስምታት በራሱ እንደ በሽታ ከሆነ ግን የተለያዩ ህክምናዎች የራስምታቱን ብቻ ለማጥፋት ይሰጣሉ፡፡
የሚግሬይን የራስምታትን ለማከም፣ እንደ የራስምታቱ ክብደት የተለያዩ መድሃኒቶች ይሰጣሉ፡፡ ቀለል ላለ የሚግሬይን የራስምታት፣ ያለ ሐኪም ትእዛዝ የሚወሰዱ እንደ ፓራሲታሞል፣ አስፕሪን፣ ዳይክሎፊናክ፣ ኢንደሜታሲን፣ አይቡፕሮፊን የመሳሰሉ መድሃኒቶችን መውሰድ ይቻላል፡፡ ቢሆንም ህፃናት እና በአስራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆች አስፕሪን ባይወስዱ ይመረጣል፡፡ የጨጓራ በሽተኞችም ከፓራሲታሞል ውጪ ያሉትን የህመም ማስታገሻዎች ከመውሰዳቸው በፊት ሐኪማቸውን ማማከር ይገባቸዋል፡፡ የጉበትና የኩላሊት ህመምተኞችም የራስምታት መድሃኒቶችን ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መጠቀም የለባቸውም፡፡
ከበድ ላለ ሚግሬይን እንደ ergotamine ያሉ መድሃኒቶች ተመራጭ ናቸው፡፡ የሚግሬይንን የራስምታት የሚቀሰቅሱ የተለያዩ ሁኔታዎች ለምሳሌ፣ ጭንቀት፣ የእንቅልፍ መዛባት፣ ፆም፣ አብረቅራቂ ነገሮችን መመልከት፣ አንዳንድ ሽታዎች፣ የሲጋራ ጭስ፣ አልኮል መውሰድ፣ ቸኮሌት፣ ቡና ወዘተ… ማስወገድ ህመሙ አስቀድሞ እንዳይከሰት ያደርጋል፡፡ የዚህ ህመም ተጠቂ ህመሙን የሚቀስቅስበት ምን ሁኔታ ወይም ነገር እንደሆነ ለይቶ በማወቅ ቀስቃሹን ነገር ወይም ሁኔታ ማስወገድ ይኖርበታል፡፡
ክላስተር የራስምታት ለማከም የተለያዩ ህክምናዎች አሉ፡፡
አንዴ የጀመረውን ህመም ለማስቆም መቶ በመቶ የሆነ የኦክስጅን ጋዝ ከ8-10 ሊትር በደቂቃ ለዚሁ በተዘጋጀ ማስክ አማካይነት ከ10-15 በመተንፈስ፣ ጎን ለጎንም የ(triptan) ወይም (ergot) ዝርያ መድሃኒቶች መውሰድ ፍቱን ነው፡፡ ይህን አይነቱን የራስምታት አስቀድሞ ለመከላከል የ(calcium blocker) ዝርያ መድሃኒቶችን መውሰድ ይቻላል፡፡
(tension headache)ን ለማከም፣ ለቀላል ሚግሬይን የተጠቀሱትን ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የሚወሰዱ መድሃኒቶች መጠቀም ይቻላል፡፡
ከቀላሉ ጉንፋን እስከ ወባ እንዲሁም እስከ ጭንቅላት እጢ ያሉ በሽታዎች ምልክት ሊሆን፣ እንዲሁም በራሱ እንደ በሽታ ሊከሰት የሚችለው የራስምታት አፈጣጠርና ህክምና ይህንን ይመስላል፡፡ S

Previous Story

ሕልምና የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተቃራኒው ይተረጎማል

Next Story

Sport: ከመንደር ሱቅ ጠባቂነት እስከ የአለም ምርጥ አሰልጣኝነት

Go toTop