ወ/ሮ ሰምሀር ከበደ እባላለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት የምኖረው በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 6 የቤት ቁጥር 336/68 ውስጥ ነው፡፡ በ1970 ዓ.ም. በአስመራ ከተማ ተወልጄ ያደኩ ሲሆን ከኤርትራ ተፈናቅዬ በ1983 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጥቻለሁ፡፡ ሻዕቢያ አብርሮኝ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣሁ በኋላ ሌላ በደል ደረሰብኝ፡፡ እናቴ ወ/ሮ አልማዝ ገ/ሕይወት በ1987 ዓ.ም. ከኪራይ ቤቶች ህጋዊ ውል ተዋውላ ቀጠና 4 ወረዳ 2 የቤት ቁጥር 202/ሀ በሆነውን የንግድ ቤት እየሰራሁ እያለሁ በ1995 ዓ.ም ልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት የንግድ ቤቱን በተመለከተ የነበረውን ክርክር ለእናቴ የተወሰነላት ቢሆንም የወሰነውን ውሳኔ በመጣስ ቤታችንን እስከነ ንብረቱ ለሌላ ወገን አስተላልፎብናል፡፡ የፍ/ቤቱም ውሳኔ በእጄ ላይ ይገኛል፡፡ amharic.thehabesha.com
በ1989 ዓ.ም. የኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ ከወ/ሮ አልማዝ ገ/ሕይወት ጋር ህጋዊ ውል ተዋውሎ በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 6 የቤት ቁጥር 336/68 የሆነውን 1 ክፍል ሳሎንና 1 ክፍል መኝታ ያለውን ኩሽና አጥር የሌለውን የመኖሪያ ቤት አከራይቷት እኔ ግቢውን ሊሾ በማድረግ 4 ክፍል መኝታ፣ ቤት ሻወር ኩሽና የግምብ አጥር በማጠር የብረት በር በማስገጠም 3 ትንንሽ ልጆቼን ይዤ ስንኖርበት ቆይቻለሁ፡፡ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመረዳጃ እድርና በተለያየ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ የሆንኩና በወረዳው በልማት ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ ወላጅ እናቴ ወ/ሮ አልማዝ ገ/ሕይወት ሰኔ 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቷ በፍ/ቤት ወራሽነቴን አረጋግጫለሁ፡፡ እኔም ነዋሪነቴ በቦሌ ክ/ከተማ ወረደ 6 የቤት ቁጥር 336/68 በሆነው የቤተሰብ ቅፅ ውስጥ ከነቤተሰቦቼ ተመዝግቤ የነዋሪነት መታወቂያ ያወጣሁና በየጊዜው እያደስኩ መኖሬ የሚታወቅ ሲሆን በስሜ በን/ስ/ላ/ክ/ከተማ ወረዳ 01 የቤት ቁጥር ‹አዲስ› በሆነው ባርና ሬስቶራንት ከፍቼ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ይህ ደግሞ ህጋዊ የንግድ ፈቃድና የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር /ቲን ነምበር/ አውጥቼ የምሰራበት ንግድ ቤቴ እንጂ የመኖሪያ ቤት እንዳልሆነ የን/ስ/ላ/ክ/ከተማ አስተዳደር በደብዳቤ ገልጾ ለመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ልኮልኛል፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ይሄንን ትክክለኛ መረጃ ቀርቦለት እያለ ሚያዝያ 24 ቀን 2006 ዓ.ም. በተጻፈው ደብዳቤ ቤቱን በ30 ቀን ውስጥ እንድለቅ ባልለቅ ግን ‹‹ግንቦት 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ባታስረክቢ በፖሊስ እቃሽን በመውሰድ ልጆችሽን በመወርወር እናስወጣሻለን›› በማለት ማስጠንቀቂያ ሰጥቶኛል፡፡ ሻዕቢያ በኃይል አብርሮኛል፡፡ አሁን ደግሞ አገሬ ነች ብየ ከመጣሁበት ኢትዮጵያም ከፍተኛ በደል እየደረሰብኝ ነው፡፡ እኔም ፍትህ ፍለጋ ወደ ከፍተኛ ፍ/ቤት በመሄድ አቤቱታዬን ያቀረብኩ ሲሆን ፍ/ቤቱ አቤቱታዬን ውድቅ አድርጎብኛል፡፡ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ልጆቼ ከእናቴ /ከአያታቸው/ ጋር በዚሁ ቤት ያደጉ መሆኑን የክትባት ወረቀት ማረጋገጫ ነው፡፡ ይህን መረጃ ተንተርሶ ወረዳ 6 ልጆቹ በዛ ቤት ቅፅ ውስጥ የተመዘገቡ እና ነዋሪ መሆናቸውን ገልፆ ለመንግስት ኤጀንሲ ቢፅፍም ‹‹ልጆቹን አናውቃቸውም!›› በማለት ሥነ-ምግባር በጎደለውና የህፃናት ልጆቼን የዜግነት መብታቸውን በመግፈፍ፣ እኔ እናታቸውን በመስደብ እና በማዋረድ በልዩ ጉዳይ አቶ ግርማይ ቅርንጫፍ 3 የሥራ ሂደት ኃላፊ እና ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃ/ማርያም እቤቴ ድረስ በመምጣት በአያታቸው ሞት የተጎዱ ህፃናትን እናስወጣችኋለን በማት ኃላፊነታቸው የማይፈቅድላቸውን በደል ልጆቼ ላይ ፈጽ መዋል፡፡
ልጆቼን ለማስተማር የከፈልኩት 36000 (ሠላሳ ስድስት ሺህ ብር/ እና ልጆቼ ዓመት ሙሉ የለፉበትን ትምህርት ግንቦት 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ከሚኖሩበት ቤት በፖሊስ በማስወጣት ትምህርታቸውን የሚያስተጓጉል መሆኑን በመናገር ልጆቹ ከፍተኛ የሆነ የስነ ልቦና ጫና የደረሰባቸው ሲሆን እድሜዋ 12 ዓመት የሆናት ማሪያማዊት ዜና ሥላሴ ከአያቷ ሞት በተጨማሪ የኤጀንሲው ሠራተኞች በተደጋጋሚ ‹‹ቤቱን ትለቃላችሁ›› እያሉ ስለሚያስፈራሩዋት በከባድ ፍርሃትና ጭንቀት የተነሳ ለአዕምሮ በሽታ ተጋልጣ በቦሌ ከፍተኛ የአእምሮ ክሊኒክ እየተረዳችና መድኃኒት እየወሰደች ትገኛለች፡፡ ይህንን ህክምና ማስረጃ ለኤጀንሲው ባቀርብም ወረቀቱን በመቅደድ ‹‹የትም አትደርሽም ስለ ልጆችሽ አያገባንም›› በማለት ሊያስተናግዱኝ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ሻዕቢያ ኢ-ሰብአዊ በመሆነ መንገድ አባርሮኛል፡፡ ወደ አገሬ ከተመለስኩ በኋላም ይህ በደል አልለቀቀኝም፡፡ እኔም ሆነ ልጆቼ እንደ ዜጋ
መብታችን የሚያከብርልን፣ የሚያዳምጠን አካል አላገኘንም፡፡ ይህ ሁሉ በደል ሲደርስብኝ ‹‹አገሬ ግን የት ነው?›› ብዬ እጠይቃለሁ፡፡
በእኔ ላይ ኤጀንሲው የኢትዮጵያ ዜግነትንና ሰብአዊ መብቴን የሚነካ ድርጊት እየተፈፀመብኝ ሲሆን ፍትህ አገኛለሁ ብዬ ለከፍተኛ ፍ/ቤት አቤቱታ ባቀርብም ፍ/ቤቱ ውድቅ ያደረገብኝ በመሆኑ በከፍተኛ ጭንቀት ላይ እገኛለሁ፡፡ በአካባቢዬ ያሉ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ባልደረቦች እና ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ
አባላት የሆኑ ቤት ቀጥለው የሰሩ ሲሆን የሰሩትም በብሎኬት ነው፡፡ እኔ ግን የሰራሁት በጭቃ ነው፡፡ እኔ የቤት ኪራይ የምከፍለው 560 ሲሆን እነሱ ግን የሚከፍት 70 ብር ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እየተፈፀመ ያለው ሙስና ምን ያህል እንደሆነና በዜጎች መካከል ያለውን መድልኦና በደል የሚያሳይ ነው፡፡
አሁንም በመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ሠራተኛ ሆነው የራሳቸውን ደብቀው የሌላውን በመጠቆም እንዲለካና ኪራይ እንዲጨምር በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስፈላጊም ከሆነ ስማቸውንና ያላቸውን የሥራ ኃላፊነት መናገር ይቻላል፡፡ በመጨረሻም የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ያለ አግባብ ግንቦት 21 ቀን 2006 ዓ.ም. በፖሊስ ከነልጆቼ ሊያስወጣኝ በዝግጅት ላይ ስላለ በዚያን ወቅት በእኔና በልጆቼ ላይ የሚደርሰውን በደልና ግፍ ሚዲያዎችና ሌሎች ለኢትዮጵያውያን መብት የሚቆሙ አካላት ሁሉ በቪዲዮ በመቅረፅ ለዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ለህፃናት መብት እና ለኢትዮጵያ
ህዝብ እንዲያሳውቁልኝ እጠይቃለሁ፡፡