የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኙ ቢዚ ሲንግናልበዳግማዊ ትንሳኤ ዋዜማ ሊካሄድ የነበረውና የተሰረዘው የቢዚ ሲግናል ፣ ጃ ሉድ እና ናቲ ማን የሙዚቃ ኮንሰርት ወደ ሌላ ቀን መዛወሩ ተሰማ።
በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ከታላቁ የአቢይ ፆም ፍፃሜ በዃላ እና በዳግሚያ ትንሳኤ ዋዜማ ሁለት ታላላቅ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን በቴዲ አፍሮ እና አቡጊዳ ባንድ እንዲሁም በጃማይካዊው የሬጌ ሙዚቃ ተጫዋች ቢዚ ሲግናል ፣ ጃ ሉድ እና ናቲ ማን አማካኝነት እንደሚካሄድ ላለፉት ሳምንታት በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ሲተዋወቅ የቆየ ቢሆንም በሚሊኒየም አዳራሽ ሊካሄድ የታሰበው የነቢዚ ሲግናል የሙዚቃ ኮንሰርት የፊታችን ቅዳሜ ሚያዚያ 18 (አፕሪል 26) ቀን እንደማይካሄድ ለማረጋገጥ ተችሏል::
ከተለያዩ የውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደተረጋገጠው በአዲስ አበባ በተመሳሳይ ቀን ሁለት ታላላቅ ኮንሰርቶችን ማካሄድ የሙዚቃ አፍቃሪውን ከመከፋፈል አልፎ ሁለቱንም ኮንሰሮች ሊጎዳና ምናልባትም አንደኛውን ወገን ሊጠቅም እንደሚችል በመገመቱ በተለይም የቴዲ አፍሮና አቡጊዳ ባንድ የጊዮን ኮንሰርት ገና የዝግጅቱ ቀን ሳይደርስ በሙዚቃ አፍቃሪው ህብረተሰብ ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ መጠበቁና በማስታወቂያ እና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች ገዝፎ መውጣቱ የነቢዚ ሲግናል ኮንሰርት አዘጋጆችና አርቲስቶች የዝግጅታቸውን ቀን ለመቀየር ተስማምተዋል::
በዚህም መሰረት የቴዲ አፍሮ እና አቡጊዳ ባንድ የሙዚቃ ዝግጅት አስቀድሞ በታቀደው ቀንና ቦታ የፊታችን ቅዳሜ ሚያዚያ 18 (አፕሪል 26) ቀን በጊዮን ሆቴል የሚደረግ ሲሆን የነቢዚ ሲግናል ፣ ጃሉድ እና ናቲ ማን የሚሊኒየም አዳራሽ ኮንሰርት ከሁለት ሳምንት በዃላ ይካሄዳል ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጊዮኑን የሙዚቃ ዝግጅት የድምፅና መድረክ ቅንብርን ለመምራት ዝነኛው የሳውንድ ኢንጅነር ጃማይካዊው ኤሮል ብራውን ከ አሜሪካ አዲስ አበባ ገብቷል::
የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት የመግቢያ ዋጋ መደበኛው 400 ብር ሲሆን ቪ አይ ፒ ደግሞ 700 ብር መሆኑን ካዘጋጆቹ ለመረዳር ተችሏል::
የሙዚቃ አፍቃሪው በሁለቱም ታላላቅ ኮንሰሮች ላይ ለመገኘት እንዲችል የዝግጅቶቹ ቀናት መለያየታቸው መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን ይታመናል።