ባርሴሎናና ሪያል ማድሪድ በሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ሊገናኙ ይችላሉ

April 14, 2013

በአሰግድ ተስፋዬ

በእንግሊዙ ዌምብሌ ስታዲየም በሚካሄደው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ የስፔኖቹ ባርሴሎናና ሪያል ማድሪድ ሊገናኙ ይችላሉ።ትናንት ከሰዓት በኋላ በስዊዘርላንድ ኒዮን ከተማ የወጣው የሩብ ፍጻሜ ድልድል ዕጣ ባርሴሎናን  ከጀርመኑ ሻምፒዮን ባየር ሙኒክ ፣ ሪያል ማድሪድን ከቦሩሲያ ዶርት ሙንድ አገናኝቷል።
በዚህ መሠረት ባርሴሎናና ሪያል ማድሪድ ተጋጣሚዎቻቸውን የሚያሸንፋ ከሆነ በፍጻሜው የመገናኘት እድል ይኖራቸዋል ማለት ነው።
ሁለቱ የጀርመን ክለቦች ባየር ሙኒክና ቦሩሲያ ዶርትሙንድ የሩብ ፍጻሜን የመጀመሪያ ጨዋታ በሜዳቸው እንደሚያደርጉም የወጣው ድልድል አመልክቷል ።
ሪያል ማድሪድ ለሩብ ፍጻሜው መድረስ የቻለው የቱርኩን ጋላታሳራይ እግር ኳስ ክለብ አምስት ለሦስት በሆነ አጠቃላይ ውጤት በመርታት ሲሆን ሌላው የስፔን ተወካይ ባርሴሎና ከፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንት ጄርሜን ጋር ሦስት ለሦስት አቻ ተለያይቶ ከሜዳው ወጪ ብዙ ባገባ በሚለው ሕግ ተጠቃሚ ሆኖ መሆኑ ይታወሳል።
አዲሱ የቡንደስ ሊጋው ሻምፒዮን ባየር ሙኒክ በበኩሉ የጣሊያኑን ጁቬንቱስን አራት ለዜሮ በሆነ አጠቃላይ ውጤት በመርታት ሩብ ፍጻሜውን ሲቀላቀል ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በበኩሉ ማላጋን ሦስት ለሁለት በመርታት ነው ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለው ።
ሪያል ማድሪድና ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በሊጉ የምድብ ድልድል ጨዋታም አንድ ምድብ የነበሩ ሲሆን በየርገን ክሉፕ የሚሰለጠነው የጀርመኑ ክለብ በሜዳው የስፔኑን ተወካይ ሁለት ለአንድ መርታቱ ይታወሳል። ሁለቱ ክለቦች በበርናባው ባደረጉት የመልስ ጨዋታ ሳይሸናነፉ ሁለት ለሁለት ተለያይተዋል።
ከትናንቱ የሩብ ፍጣሜ ድልድል በኋላ የዶርትሙንድ ስራ አስኪያጅ ሐንስ ዮአኪም ዋትዝ በሰጡት አስተያየት « የምድብ ድልድል ጨዋታዎቹን በማየት ማድሪድ የሚፈራን አይመስለኝም። እኛ እንድምናከብራቸው ሁሉ እነሱም እንደሚያከብሩን አስባለሁ » ብለዋል።
የቀድሞ የስፔን ብሔራዊ ቡድን የፊት መስመር ተሰላፊና የአሁኑ የማድሪድ አምባሳደር ኤሚሊዮ ቡትራጌኖም የምድብ ጨዋታዎቹ ውጤት በዚህኛው ላይ ተጽዕኖ እንደሌላቸው ያምናሉ። « ለዶርትሙንድ ከፍተኛ አክብሮት አለን። ሁለት ጊዜ ከነሱ ጋር ብንጫወትም ልናሸንፋቸው አልቻልንም ። ለፍጻሜ ለመድረስ ካለን ፍላጎት የተነሳ የአሁኑ ጨዋታ ውጤት የተለየ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን » ሲሉም ገልፀዋል።
የባየር ሙኒክ ሊቀመንበር ካርል ሄይንዝ ሩሚኒጌ ክለባቸው ከአውሮፓ ምርጡ ክለብ ጋር በመደልደሉ ደስተኛ መሆናቸውን ከገለጹ በኋላ « ሁለት ምርጥ ጨዋታዎችን የምንመለከት ይመስለኛል » በማለት ጨዋታውን በተመለከተ አስተያየት ሰጥተዋል።

Previous Story

የኢሳት 3ኛ አመት ክብረ-በዓል የሙስሊሞች ብቻ ነው እንዴ? ከ ልጅ ተክሌ

Next Story

‹‹የ33ቱ ፓርቲዎች ጥያቄ በአጭር ቃል ሲቀመጥ ‹አሯሯጭነት በቃን!› ነው›› – አቶ ተመስገን ዘውዴ

Go toTop