ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 02/2012ዓ.ም (አብመድ) ጥምቀት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዝገቡ ለአማራ ክልል የተለዬ አንድምታ እንደሚኖረው የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡ ክልሉ ጥምቀት በዩኔስኮ እንዲመዘገብ አማራ ክልል ጥያቄ ከማንሳት ጀምሮ ምላሽ እስኪገኝ ድረስ በባለቤትነት ይሠራ እንደነበርም ተመላክቷል፡፡
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሙሉቀን አዳነ (ዶክተር) ለአብመድ እንደተናሩት የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ እንዲመዘገብ የአማራ ክልል መንግሥት ሰፊ ጥረት አድርጓል፡፡ ጥያቄው ተቀባይነት ማግኘቱም ለአማራ ክልል የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የተለየ አንድምታ እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የጥምቀት በዓል በክልሉ በተለዬ መልኩ እየተከበረ መምጣቱን ተከትሎ ነው መመዝገቡ ለአማራ ክልል ቱሪዝም የተለዬ ፋይዳ ይኖረዋል ያስባለው፡፡
ባለፈው ዓመት የጥምቀት በዓልን ለማክበር ወደ ጎንደር 17 የአውሮፕላን በረራ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡ በዓሉ በባሕር ዳር ከተማ እና በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራም የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች በስፋት የሚታደሙበት ነው፡፡ በዩኔስኮ በተመዘገበበ ማግስት የሚከበር መሆኑ ደግሞ የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል በተለዬ ስሜት ተጠባቂ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
‹‹የተለያዩ አካባቢዎች ልዩ ልዩ በዓላት በልዩ ድባብ ይከበራሉ›› ያሉት ዶክተር ሙሉቀን የልደት በዓልን በላልይበላ፣ ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር፣ እንግጫ ነቀላን በደብረ ማርቆስ፣ የፈረስ ጉግስን በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ የሻደይ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላትንም በየአካባቢያቸው ዕውቅና ተሰጥቷቸው በስፋት እንዲከበሩ የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ነው ዶክተር ሙሉቀን የተናገሩት፡፡
የአማራ ክልል ቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ዳሬክተር አቶ ነህምያ አቤም የዶክተር ሙሉቀንን ሐሳብ አጠናክረዋል፡፡ ጥምቀት በወካይ ቅርስነት እንዲመዘገብ ጥያቄ ቀርቦ ሁለት ዓመታት መቆየቱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ እንቅስቃሴው ግን ከዚያም ቀደም ብሎ የተጀመረ መሆኑን ነው አስታውሰዋል፡፡ ረጅም ጊዜ በወሰደው ሂደትም በርካታ ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ መስፈርቱን የጠበቀ ጥናት በመሥራት፣ መረጃዎችን በማጠናከር እና በማደራጀት ሥራ ተሰማርተው እንደነበርም አስታውቀዋል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥትም በማይዳሰስ ቅርስነት በዩኔስኮ ማኅደር እንዲመዘገብ ጥያቄ ከማንሳት ባለፈ ከፌዴራል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ባልተናነሰ መልኩ በልዩ ትኩረት ሲሰራ እንደነበር አመላክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በሂደቱ ትልቅ ሥራ መሥራቷን ነው አቶ ነህምያ የተናገሩት፡፡ ጥያቄውም ምላሽ አግኝቶ በዩኔስኮ መዝገብ የማይዳሰስ የሰው ልጆች ክዋኔ ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ጥምቀት በዩኔስኮ መመዝገቡ የሀገሪቱን ዕውቅና በማሳደግ እና ገጽታዋን በመገንባት የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን የተናገሩት አቶ ነህምያ ‹‹በተለይም የጥምቀት በዓል በስፋት ለሚከበርበት የአማራ ክልል የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ይበልጥ ያነቃቀዋል›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ከጫማ አሳማሪዎች እስከ ሆቴሎች እና ባንኮች የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም የጎላ ነው፡፡
‹‹በቀጣይም አሸንድዬ፣ ሻደይ እና ሶለል በዓልን በወካይ ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥያቄ አቅርበን ምላሽ እየጠበቅን ነው›› ያሉት ዳይሬክተሩ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የክልሉ መንግሥት የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ አማራ ክልል በርካታ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሯዊ፤ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ነው፡፡ እነዚህን ቅርሶች በዩኔስኮ ከማስመዝገብ ባለፈም ማኅበረሰቡ ባለው ፀጋ ልክ ተጠቃሚ እንዲሆን ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይሠራል ብለዋል አቶ ነህምያ፡፡
የፌዴራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ለሁሉም መገናኛ ብዙኃን በጋራ መግለጫ ነው የምሰጥ በማለቱ ማካተት አልተቻለም።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ