በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ የአማራው ማኅበረሰብ እጅግ አሳሳቢ ወቅት ላይ እንደሚገኙ ግልጽ ነው፡፡ በዚህን ከፍተኛ አደጋ እያንዣበበ ባለበት ወቅት ወዳጅን ከማብዛት ይልቅ ጠላትን ማብዛት ሁላችንም ነፃ የምንወጣበትን ጊዜ ማራቅ ነው፡፡ ልብ መግዛትና ወዳጅንና ጠላትን በጥንቃቄ በማበጠር ምርትን ከግርድ መለየት የሚገባን ጊዜ ላይ ነን፡፡
ብዙዎቹ የአማራ አክቲቪስቶች አካሄዳቸውን ማረም እንደሚገባቸው ማሳሰብ እፈልጋለሁ፤ የነሱ ጥፋትም ሆነ ልማት የኔንና የልጆቼን መፃዒ ዕድል ከመወሰን አንጻር ጉልኅ ሚና አለውና፡፡
ስንጽፍም ሆነ ስንናገር ከስሜታዊነትና ከዘረኝነት እንታቀብ፡፡ ዘረኝነት እንደብል ነው፤ መላ ሰውነትን የሚመርዝና ከሰውነት ደረጃ የሚያወጣ መድሓኒት የሌለው ልክፍት ነው፡፡ በመሠረቱ ሁሉም ሰው የአዳም ዘር ነው፡፡ ከዚያ ሲያንስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአንዲት ሀገር ዜጋ ነው፡፡ በዚህች ምድራችን ያልተጋባና ያልተዋሃደ አንድም ጎሣና ነገድ የለም፡፡ ለአንድ ዓላማ ተሠልፎ እርስ በርስ ያለመስማማትና አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬና ሌላ ሌላም ዘውግ እየጠሩ በጅምላው መንቀፍም ሆነ መውቀስ ትልቅ ነውር ነው፡፡ ከእስካሁኑ ወልጋዳ አረማመዳችን ተምረን እርምጃችንን ካላስተካከልን እንጠፋፋለን፡፡ ዘመዳችን ሆኖ የቀረበንን የሌላ ጎሣ አባል ያለ በቂ መረጃና ማስረጃ ስሙን የምናጠፋው ከሆነ ያ ሰው ወይም አክቲቪስት ከሁለት ያጣ ጎመን እናደርገውና ውዥንብር ውስጥ እንከተዋለን፡፡ በዚያን ጊዜ ያ ጠበቃችን ሊሆን ወደኛ የመጣና የኛን የመከራ ቀምበር የተሸከመ የሌላ ነገድ አባል ሚናውን ይለይና በባይተዋርነት ሊቀጥል አለዚያም ወደመጣበት ነገድ ተመልሶ የጥፋት ተባባሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰው በተፈጥሮው ሲገፋ ይገፋል፤ መገፋትን የሚቋቋሙ በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ይህ እንዲሆን የሚጥሩ የአማራው ሕዝብ ተቀናቃኞችና ክፉ አሳቢዎች እንዳሉም ለአፍታም መዘንጋት የለብንም፡፡
ችግራችን በሕዝብ ደረጃ አይደለም፡፡ ዋና ችግራችን በጣም ጥቂት የሆኑ የየጎሣው አባላት የሚያራምዱት የጥፋትና የአፍራሽነት ፍላጎት ነው፡፡ እነዚህን መሰል ዜጎች የጫፉን ሥልጣን ከነተዋረዱ ሲይዙት ሀገር ትረበሻለች፡፡ የዚህ ተቃራኒ ኃይል ሥልጣን ሲይዝ ደግሞ ሀገር ትረጋጋና በልማት ትመነደጋለች፡፡ ቁልፉ እዚህ ላይ ነው፡፡
ስለዚህ የእርስ በርስ መጎሻሸምና የጅምላ ወቀሳና ዘለፋ ይቅር፡፡ አንጀት ከሚቆርጡ የዘረኝነት ስድቦችና ፍርደ ገምድል ብያኔዎች እንታቀብ፡፡ የማቅረብ እንጂ የማራቅ አካሄድን አንከተል፡፡ ሁሉንም መጠራጠርና ማሳደድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን እንወቅ፡፡ እንኳንስ የእኛን እውነታ ተረድቶ አብሮን የሚታገልን በሩቅ ሆኖ እያሳደደን የሚገኝን ሰው ቀርበን በፍቅር ብንይዘው ብዙ አወንታዊ ለውጥ እናመጣለን፡፡
የሌሎች ጎሣዎች አክቲቪስቶችም አቋማችሁ እንደብረት ጠንካራና ጽኑ ይሁን፡፡ ማንም የፈለገውን ቢል በተግባር ልታስተምሩት ከመሞከር ውጪ መልካም ሥራችሁን አትለውጡ፤ በቀላሉ አትሸነፉ፡፡ በትልቁ ትግል ሳትሸነፉ ለተወሰኑ ግለሰቦች ብላችሁ ከታሪክ መዝገብ ራሳችሁን አትሰርዙ፡፡ በአቋማችሁ ጸንታችሁ ለምክንያታዊነት በሃቅ ታገሉ፡፡ በሌሎች ኢትዮጵያውያንም ሆነ በአማራ ሕዝብ ዘንድ ዛሬም ሆነ ወደፊት የሚያስከብራችሁ ለዓላማችሁ ያላችሁ ጽናት እንጂ የግለሰቦች ሙገሣ ወይም ወቀሣ እንዳልሆነ ተገንዘቡ፡፡
ፈጣሪ ለሃቅ የቆሙ መላ ወገኖቻችንንና ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡