የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንግስት ተቋማት ያሉ ንብረቶችን ለመቆጣጠር በቅርቡ አዲስ መስሪያ ቤት ሊያቋቁም እንደሆነ ተሰማ፡፡ ካፒታል ጋዜጣ እንደዘገበው አዲሱ መስሪያ ቤት የከተማውን አስተዳደር ተሸከርካሪዎች፣ ህንፃዎች፣ ቁሳቁሶችና የቢሮ መገልገያዎችን ሁሉ እየተቆጣጠረ የሚያስተዳድር ይሆናል፡፡
በተጨማሪም የማያስፈልጉና ያረጁ ንብረቶችንም የሚያስወግድ መስሪያ ቤት ነው፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ የሚካሄደው የአስተዳደሩ ምክር ቤት ስብሰባ የዚህን የአዲሱን መስሪያ ቤት እጣ ፈንታ የሚወስን ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት የከተማው ንብረት በግል ድርጅት እየተዳደረ ይገኛል፡፡ ለአስተዳደሩ ቅርበት ያላቸው አንድ ምንጭ እንደተናገሩት እስካሁን ባለው ሁኔታ የከተማው አስተዳደር ያሉትን ንብረቶችና ህንፃዎች እንዲሁም ቤቶች በአግባቡ አያውቃቸውም፡፡
እኚሁ ምንጭ ሲናገሩ ‹‹በቅርቡ በተደረገ ጥናት መንግስት ንብረቱን በአግባቡ እያስተዳደረ እንዳልሆነ ታውቋል፡፡ አንዳንዶቹ ህንፃዎች ከከተማው አስተዳደር ጋር ምንም ግንኙነት ለሌላቸው ሰዎች ሁሉ ተከራይተዋል፡፡ አብዛኞቹ ንብረቶችም መታደስ የሚፈልጉ ናቸው›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም አዲሱ መስሪያ ቤት ከተቋቋመ የመጀመሪያ ስራው የከተማውን አስተዳደር ንብረት መቁጠር ይሆናል፡፡
አዲስ አበባ ብሔራዊ ቴአትር ፊት ለፊት ባለቤት የሌለው ህንጻ መገኘቱ ይታወሳል:: በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በተለይ የዶ/ር አብይ አስተዳደር ከመጣ ወዲህ የተለያዩ ባለቤት አልባ ህንጻዎች እየበዙ ነው::
በተለይም ባለቤት እና ሰው አልባ ኮንደሚኒየሞች በአዲስ አበባ መገኘታቸውን ዘ-ሐበሻ ከዚህ ቀደም መዘገቡ አይዘነጋም::
https://youtu.be/fabcQQpKeQU