የቀድሞው ኦህዴድ የአሁኑ ኦዴፓ የፖሊት ቢሮ አባልና የኢህአዲድ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ሃላፊ ሆነው ተሾሙ፡፡ በመሆኑም ለስድስት ወራት ያህል የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ከፍተኛ አማካሪ ሆነው የሰሩትን አቶ ፍፁም አረጋን ተክተዋቸዋል፡፡ ለተለያዩ ሚዲያዎች የመረጃ ምንጭ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ፍፁም ቀድሞ ወደነበሩበት የፌዴራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ቢሯቸው ተመልሰዋል፡፡ አቶ ሽመልስ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት የፕሬስ ሴክቴሪያት ጽ/ቤት፣ የብቃትና ፖሊሲ ሚዘና ጽ/ቤት፣ የአገር ደህንነት ጉዳይ አማካሪ ጽ/ቤትና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤትን ይመራሉ፡፡
በዚህም መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፓርላማ ሲጸድቅ በርካታ የኦህዴድ አባላት ሲቃወሙት ሕወሃትን አግዘው እጃቸውን በማውጣት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የደገፉት በሚንስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት እና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ የነበሩትን ወ/ሮ ደሚቱ ሐምቢሳን ስልጣናቸው በአቶ ሽመልስ ስር ተጠቃሏል::
አቶ ሽመልስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰብአዊ መብት የማስተርስ ዲግሪ፣ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ (UNISA) ፖስት ግራጁየት ዲግሪ በፖለቲካል ፊሎሶፊ አግኝተዋል፡
በተያያዘ ዜናም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ስር የፕሬስ ሴክሬታሪ ጽህፈት ቤት የተቋቋመ ሲሆን፥ ወይዘሮ ቢልለኔ ስዩም ሀላፊ ተደርገው ሲሾሙ ወይዘሮ ሄለን ዮሴፍ ደግሞ ምክትል ሆነዋል፡፡
ወ/ሮ ቢለኔ ስዩም እሩያን የተሰኘው የሴቶች መብት ተሟጋች ድርጅት መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሲሆኑ ሚያዚያ 11 ቀን 2010 ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ግልጽ ደብዳቤ ፅፈው ነበር፡፡ በዚያ ደብዳቤያቸው በርካታ ምክሮችን ለአብይ አህመድ አስተላልፈውላቸው ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግብረዋቸዋል፡፡ ከእነዚህም ውጸስጥ በደብዳቤያቸው በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሴቶች ተሳትፎ 50 በ 50 እንዲሆን አሳስበዋቸው ነበር፡፡ በዚያ ግልፅ ደብዳቤ እንዲህ ብለው ነበር፡፡
50-50 ካቢኔ በዓለማችን ውስጥ ባሉ ሃያላን ሃገራት ውስጥ ተመጣጣኝ የጾታ ተዋጽኦ ያለው ካቢኔ መደበኛ እና የተለመደ እየሆነ የመጣ ሲሆን እርስዎም ይህንኑ የአመራር ዘይቤ እንዲከተሉ እናበረታታለን። ሆኖም ግን፣ የዚህ ካቢኔ አወቃቀር ከዚህ በፊት “በወንዶች ይዞታ” ስር የነበሩ የኃላፊነት ቦታዎች፤ ማለትም፣ የውጭ ጉዳይ፣ የንግድ፣ ኢንዱስትሪ፣ ፋይናንስ እና መከላከያ፤ ወደ ኢትዮጵያውያን ሴቶች የእውነት መሸጋገራቸውን የሚያንጸባርቅ እንዲሆን አጥብቀን እንጠይቃለን። ለእነዚህ የኃላፊነት ቦታዎች ሴቶችን የመምረጥ ሂደቱ ለኢትዮጵያውያን በሙሉ ማህበራዊ ፍትሕን ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነትም እንዲሁ የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት።
https://www.youtube.com/watch?v=s7RE3J58cdA