የአርሰናል የምንጊዜውም ምርጥ ተጫዋች ዴኒስ ቤርካምፕ “ከአርሰናል ጋር መሥራት እፈልጋለሁ” አለ

October 15, 2013

ከይርጋ አበበ

ጥበበኛው ሆላንዳዊ የቀድሞ የአርሴናል አጥቂ ዴኒስ ቤርካምፕ ከአርሴናል ጋር የመሥራት ፍላጎት እንዳለው ተናገረ።

የ44 ዓመቱ የአያክስ አምስተርዳም ምክትል አሰልጣኝ ዴኒስ ቤርካምፕ የቀድሞ ክለቡን በአሰልጣኞች ስታፍ ውስጥ አብሮ መሥራት እንደሚፈልግ የገለጸ ሲሆን፣ «የአጥቂዎች አሰልጣኝ በመሆን የቀድሞ ክለቤን ማገልገል ብችል ደስተኛ እሆናለሁ። ደግሞም ክለቡ ጥያቄዬን እንደሚቀበለው ተስፋ አደርጋለሁ።» በማለት ለዴይሊ ሜይል ጋዜጣ ተናግሯል።

ለአርሴናል ከ420 በላይ ጨዋታዎችን ተጫውቶ 120 ኳሶችን መረብ ላይ ያሳረፈ ሲሆን፣ በክለቡ በነበረው ቆይታም ከፈረንሳዊው ቲዬሪ ሆንሪ ጋር የፈጠሩት ጥምረት ክለቡን ለበርካታ ውጤቶች እንዳበቃው ይታወቃል።

ይህንን ከግምት ያስገባው ሆላንዳዊው ኮኮብ የቀድሞ ክለቡን የፊት መስመር ተሰላፊዎች ልምዱን በማካፈልና የቴክኒካል ሥልጠናዎችን በመስጠት አርሴናልን የማገልገል ፍላጎቱን ገልጿል።

በአርሴናል ስላሳለፈው ጊዜ ተጠይቆ « በአርሴናል ጥሩ የሆነ መቀራረብ ነበረ። ሁልጊዜም ደስተኛ ነበርኩ። በአርሴናል በመጥፎነቱ ብዬ የማስታውሰው ጊዜ አልነበረም። ክለቡ ሁሌም በአእምሮዬ የሚጠፋ አይደለም። ወደዚህ ክለብ ተመልሶ መሥራት ደግሞ የኔ ትልቁ ምኞቴ ነው። ደስተኛ ሆኜ መሥራት የምፈልገው ደግሞ በተለይ አጥቂዎችን በማሠልጠኑ ላይ ሆኜ ነው።» በማለት አስተያየቱን ለጋዜጣው ሰጥቷል።

በ1995 የውድድር ዓመት መገባደጃ ላይ ከጣሊያኑ ግዙፍ ክለብ ኢንተር ሚላን ወደ አርሴናል በሰባት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ፓውንድ የተዘዋወረው ዴኒስ ቤርካምፕ፣ በወቅቱ የእርሱ የዝውውር ክፍያ የክለቡ ክብረ ወሰን ነበር። የዴኒስ ቤርካምፕ የዝውውር ክብረወሰን የተሰበረው ከሃያ አንድ ዓመታት በኋላ ሲሆን፤ ገንዘቡም 42 ነጥብ 5 ሚሊዮን ፓውንድ ነበር። በዚህን ያህል ገንዘብ ወደ አርሴናል የተዘዋወረው ጀርመናዊው የጨዋታ አቀጣጣይ ሜሱት ኦዚል መሆኑ ይታወቃል።

በአውሮፕላን መጓዝ የሚፈራው ዴኒስ ቤርካምፕ ስለ አዲሱ የአርሴናል ፈራሚ ኦዚል ሲናገር «አርሴናል ከሪያል ማድሪድ የተሰጠው ልዩ ስጦታ ነው። ያለምንም ጥርጥር በቡድኑ ውስጥ ልዩነትን መፍጠር የሚችል ኮኮብ ነው። የስምንት ዓመት የዋንጫ ድርቃቸውን ለመቅረፍም የኦዚል መፈረም ትልቅ ጠቀሜታ አለው።» በማለት ነበር የተናገረው።

አያይዞም ስለ ወቅቱ አርሴናል አስተያየት ሲሠጥ « አርሴናል ሜሱት ኦዚልን ማስፈረሙ የክለቡን መነቃቃት ለመፍጠር ያስቻለው ሲሆን፣ በመሃል ሜዳ ላይ ያለበትን ክፍተት ለመድፈን ማቲው ፍላሚኒን ማስፈረሙ ደግሞ ክለቡ ይበልጥ የተዋጣለት እንዲሆን ያስችለዋል።

«ከኦዚል በተጨማሪ ሌሎች ጥራት ያላቸው የመሃል ሜዳ ተጫዋቾችም በክለቡ እንደሚገኙ ይታወቃል። ነገር ግን ክለብህ ልዩነትን ሊፈጥር የሚችል ልዩ ተጫዋች የሚያስፈልግበት ጊዜ አለ። አርሴናል ደግሞ ለዚህ ፍላጎቱ ጀርመናዊውን ኮከብ በክለቡ ማግኘት ችሏል።» ሲል በሜሱት ኦዚልና ማቲው ፍላሚኒ ለአርሴናል መፈረም የተሰማውን ደስታ ገልጿል።

ዴኒስ ቤርካምፕ በ2006 እኤአ ከእግር ኳስ ከተገለለ በኋላ በቀጥታ ያመራው እግር ኳስን «ሀ» ብሎ ወደ ጀመረበት አያክስ አምስተርዳም ሲሆን፣ የፍራንክ ዲ ቦር ረዳት በመሆን ነበር አሰልጣኝነትን የጀመረው።

Previous Story

Health: የአልኮል መጠጦችና እፆችና ወሲብ [Let’s Talk About Sex…& Alcohol]

Next Story

በደብረ ማርቆስ ዩነቨርስቲ ተማሪዎችና በመንግስት መካከል ረብሻ ተነስቷል

Go toTop