ሸንጎ ለዘ-ሐበሻ የላከው መግለጫ የሚከተለው ነው፦
መስከረም ፲፱ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.
September 29, 2013
በዛሬው ዕለት በአዲሰ አበባ ውሰጥ የታየውን ታላቅ ሰላማዊ ትእይንተ ህዝብ በአመርቂ ሁኔታ ላሰተባበሩት እና ለውጤት ላበቁት አንድነት ፓርቲንና የ33ቱ ፓርቲዎች ስብስብን “እንኳን ደስ አላችሁ” እያልን የትግል አጋርነታችንንም እንገልጻለን።
እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ ገዥው ክፍል የሰልፍ ቦታ በመከልከል፣ ለስልፉ በመቀስቀስና በማስተባበር ተግባር ላይ የተሰማሩትን በማዋከብ፣ በማሰር፣ ወዘተ…. ይህ ሰላማዊ ሰልፍ እውን እንዳይሆን ቢሞክርም፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የፍራቻ ድባብን ሰባብረው፣ ለመብታቸው መከበር ቆርጠው መነሳታቸውን በዚህ ሰላማዊ ትእይንተ ህዝብ ላይ በመሳተፍ አሳይተዋል።
ይህ በጨዋነት እና እጅግ በሰለጠነ ሁኔታ ተጀምሮ የተጠናቀቀው ትእይንተ ህዝብ፣ ቀደም ሲል ከተካሄዱት ሰለማዊ ሰልፎች ጋር ተዳምሮ ሲታይ ህዛባችን ለዓመታት በገዥው ቡድን የደረሰበት ግፍና ከፋፋይነት አብቅቶ መብቱ ሳይሸራረፍ እንዲከበር ለማድረግ ቆርጦ መነሳቱን ያመለክታል።
ይህ የህዝብ መነሳሳት በቀጣይነት እንዲገፋና ወደ “አርድ አንቀጥቅጥ” ሃይልነት እንዲቀየር፣ ትዕግስትና ጥበብ የተሞላበት ቀጣይና የጋራ እንቅስቃሴን ማካሄድ አስፈላጊ ነው እንላለን። በዚህ አኳያ አንድነት ፓርቲና 33ቱ ፓርቲዎች በቀጣይነት ለማካሄድ ላቀዱት ህዝብን ያሳተፈና ማእከል ያደረገ ትግል ያለንን አድናቆትና ድጋፍ እንገልጻለን።
በህዝባችን ላይ የተጫነው የግፍ አገዛዝ አክትሞ በምትኩ ሁሉም ዜጎች በእኩልነት የሚኖሩባት፣ የሰብዓዊ መብት በተግባር የሚከበርባት፣ የህግ የበላይነት የሚረጋገጠባት፣ አንድነቷ በምንም መልክ ለድርድር የማይቀርብባት፣ ዜጎቿ ሁሉ የሚኮሩባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚደረገው ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም ዜጋ ትግሉን እንዲደግፍና ተግባራዊ ተሳትፎውንም ከፍ እንዲያደርግ ጥሪያችንን እናቀርባልን።
በውጭው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦች እና ድርጅቶችም ይህ ውጤትን በማሰመዝገብ ላይ የሚገኝ እንቅስቃሴ ይበልጥ እንዲያድግና ስር እንዲሰድ ቀጥተኛ ድጋፋችሁን እንድታበረክቱ፣ ይህን ትግል ለማደናቀፍና ለማጣጣል የሚጥሩትንም አበክራችሁ እንትታገሉ ጥሪ እናቀርባለን።
የተባበረንና ህዝብን ማእከል ያደረገን ትግል ሊያግድ የሚችል ምንም ሀይል የለም።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)