ክብሪት የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮት – (በያሬድ አይቼህ)

በያሬድ አይቼህ ፥ ጁላይ 5፥2013

በቱኒዚያው ህዝባዊ ንቅናቄ የተጀመረው የአረቡ ህዝብ ቁጣ ፡ እንደገና ሌላ የግብጽ ፕሬዘደንት ከስልጣን ገፍትሮ ጣለ። በቲኑዚያ የተጫረው ፡ የሊቢያውን ጋዳፊ አቃጥሎ ፡ የየመኑን ፕሬዘዳነት አባሮ ፤ አሁንም በሶርያ እየነደደ ነው። ይሄንን ሁሉ የህዝብ ቁጣ የጫረው አንድ ጥፊ ነበር። አዎ! ጥፊ።

በአገራችንም የሚጭረው ክብሪት የሚጠብቅ ህዝባዊ የነጻነት የፍትህና የዴሞክራሲ አብዮት እያጉረመረመ ነው።

ጉዳዩ እንዲህ ነው። በ2011 ቱኒዚያዊው የኮሌጅ ምሩቅ ወጣት መሃመድ ቦአዚዚ 8 የሚሆኑ ቤተሰቦቹን እና ዘመዶቹን የሚያስተዳድርበት ገቢ ሚያገኝበትን የፍራፍሬ ጋሪ ፓሊስ ያግትበታል። መሃመድ መክፈል የነበረበትን ክፍያ ከፍሎ የፍራፍሬ መሸጫ ጋሪውን ሊያስለቅቅ ሲሞክር ፓሊሱ ፡ የመሃመድን ሟች አባቱን ሰድቦ ፡ በጥፊ ጭው ያረገዋል።

መሃመድ ከተሰማው ጥልቅ ውርደትና ሰሚ ማጣት የተነሳ ሰውነቱ ላይ ነዳጅ አርከፍክፎ ራሱን ያቃጥላል። የመሃመድን አበሳ የሰሙ ቱኒዝያውያን የኑሮ ውድነት ፡ ከፍተኛ ስራአጥነት ፡ የምግብ ዋጋ መናር ፡ የመናገር ነጻነት መነፈግና ሌሎች የፓለቲካ ጭቆናዎች የተነሳ ቁጣቸው ገነፈለ። ቁጣቸው ቤን አሊን ከ23 ዓመት ስልጣን ላይ ነቅሎ ከአገር አባረረው። ይህ ሁሉ የጫረችው ያች ጥፊ ናት።

ያች ጥፊ ናት ቤን አሊን ጭው ፡ ሙባረክን ጭው ፡ ጋዳፊን ጭው ፡ አሁን ደሞ ሙርሲንም ጭው ያደረገቻቸው። ጥፊዋ ለሁለት አመታት የሶርያውን ባሻርን ጭው ፡ ጭው እያደረገችው ትገኛለች። አብዮታዊ ጥፊዋ ወደ አገራችን ለመግባት እያንዣበበች ይመስለኛል።

ህዝባችን በኑሮ ውድነት ታይቶ በማይታወቅ መንገድ እየተንገላታ ፡ በሙስና የተዘፈቀ አመባገነናዊ ፋሽስት መንግስት እያሰቃየው ፡ የፈለገውን እያሰረ ፡ የፈለገውን እየገደለ ፡ የፈለገውን ከመሬት እያፈናቀለ ፤ የሙስሊሙ የሃይማኖት ነጻነት ተደፍሮ ፡ የክርስትያኑን ሱኖዶስ ከፋፍሎ ፤ የፓለቲካ ምህዳሩን ዘግቶ በምንገኝበት በዚህ ወቅት ክብሪት ከየት ይመጣ ይሆን?

ክብሪት የሚጠብቀው ህዝባዊ የነጻነት ፡ የፍትህ እና የዴሞክራሲ አብዮት በኢትዮጵያ ሚፈነዳበት ጊዜው እየተቃረበ ነው።

ማን ይሆን የኢትዮጵያን ህዝባዊ የነጻነት አብዮት የሚጭረው? ታሪክና ትውልድ በጉጉት እየጠበቀ ነው።

– – – –

ጸሃፊውን ለማግኘት፦ yared_to_the_point@yahoo.com

Previous Story

ESFNA 2013: የኢትዮጵያ ቀን በሜሪላንድ በደመቀ ስነ ሥርዓት ተከበረ

Next Story

አንድነት በመንግስት ጥያቄ መሰረት የጎንደርን ሰላማዊ ሰልፍ ለሐምሌ ሰባት አዘዋውረናል አለ

Go toTop