ከያሬድ አይቼህ –
ጃዋር መሀመድ እንግዳ ሆኖ በፓልቷክ ዛሬ እሁድ ቀርቦ ነበር። ቃለ-ምልልሱን ከ1000 በላይ ሰዎች አዳምጠዉታል። ዋናዎቹ ጠያቂዎች የሲቪሊቲው አባ-መላ (አቶ ብርሃኑ እርገጤ) እና የቃሌው ማይጨው ነበሩ።
አባ-መላ ጃዋርን አጣብቂኝ ውስጥ ለማስገባት ሞከረ። አንዴ ኦህዴድ አባል ነበርክ አለው። ጃዋር “የማንም ድርጅት አባል ሆኜ አላቅም አለ”። አባ-መላ ጃዋርን የኦሮሞ አስገንጣይ አርጎ ለማቅረብ ሞከረ ፤ አልተሳካለትም። ጃዋር መጀመሪያ ኦሮሞ ፡ ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ መሆኑን አስረግጦ አቀረበ።
ኦሮሞ እና አማራ ምሰሶዎች ናቸው የሚለው ንድፈ-ሃሳብ ሲቀርብ ጥሩ ንድፈ-ሀሳብ ሆኖ አግኝቼው ነበር። ሆኖም ግን ኦሮሞዎችን እንደ መሰላል ተጠቅሞ ፡ የኦሮሞዎችን ብሄራዊ ማንነት ሳይቀበል ፡ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመፍጠር እንደማይቻል ግልጽ ይመስለኛል። አሁንም የኦሮሞ-አመራ ምሰሶነት ለአገራችን ነጻ መውጣት ብሩህ ተስፋ ብዬ አምናለሁ።
– ጥንድ-ምሰሶ –
የኦሮሞ-አማራ ጥንድ-ምሰሶነት ሃቅ ነው። በህዝብ ብዛት አንጻር ፡ በኢትዮጵያ መንግስት የ2004 ዓ.ም. መረጃ መሰረት ፡ የኦሮሚያ ህዝብ የኢትዮጵያ 36% ሲሆን ፡ የአማራ ክልል ህዝብ ብዛት የኢትዮጵያ 22% ነው። በድምሩ 58% ነው ፤ የሁለቱ ህዝቦች ምሰሶነት ከዚህ ጭብጥ የተነሳ ነው።
ምሰሶዎቹ በኢትዮጵያ ፓለቲካ ተወዳዳሪ የሌለው የፓለቲካ ሃይል የመሆን እምቅ ችሎታቸው ግልጽ ነው። ነገር ግን እንዴት ነው ሁለቱ ሊሂቃን ጎን-ለጎን በመቆም የኢትዮጵያ ምሰሶ የሚሆኑት? አባ-መላ እና ማይጨው በሚሉት መንገድ ሊሆን አይችልም ፤ የኦሮሞ ሊሂቃን ፡ እኛ አማራዎች በቀረጽነው ኢትዮጵያዊነት ውስጥ እንዲካተቱ ማደርግ አይቻልም።
– ኦሮሚያ –
አንዱ በተደጋጋሚ ጠያቂዎቹ ጃዋርን ለማጥቃት የሞከሩበት መንገድ “ኦሮሚያ ሚባል አገር የለም” በማለት ነው። ለመሆኑ ወፍ ዘራሽ የሆነ አገር አለ እንዴ? ሁሉም አገር ሰው ሰራሽ እኮ ነው። አሜሪካ የዛሬ 400 አመት አልነበረም ፤ አሁን ግን አለ። ኤርትራ የዛሬ 20 ዓመት በፊት አልነበረችም ፤ አሁን ግን አለች።
ኦሮሚያም አለች። ባለፉት 22 ዓመታት የኦሮሞ ህዝብ ስነልቦና በኦሮሚያዊነት ተጠግኗል ፡ ተቀርጿል ፡ ተደራጅቷል። የቁቤ ትዉልድም ወደ ሃላፊነት ተረካቢነት እየገሰገሰ ነው። የቁቤ ትውልድ የሚያቀው ኦሮሚያን ብቻ ነው ፤ ‘እምዬ ኢትዮጵያን’ አያቅም።
ይሄንን ጭብጥ አባ-መላ እና መሰል ወገኖቻችን ይክዳሉ። ነገር ግን የኦሮሞ-አማራ ሊሂቃን በህብረት መስራት ሚችሉት የአማራ ሊሂቃን የኦሮሞን ኦሮሚያዊነት ሲቀበሉና ሲያከብሩ ብቻ ነው። “መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ ፡ ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ” የሚለውን ማንነት የማይቀበሉ የአማራ ሊሂቃን የኢህአዴግ እድሜ አስረዛሚዎች ናቸው።
የኢህአዴግ አምባገነናዊ ስርዓት ህዝባችንን በሙስና ፡ በኑሮ ውድነት ቸነፈር ፡ በፍትህ መጥፋት ፡ በሰብአዊ መብት ጥሰት ፡ በፓለቲካ እስረኝነት እና በሃይማኖት መብት ጥሰት በሚያንገላታበት በአሁኑ ጊዜ ፡ የኦሮሞዎችን ኦሮሚያዊነት አልቀበልም ማለቱ አርቆ አለማሰብ ነው።
– አማራዎች ምን እናድርግ? –
አማራዎች ራሳችንን እናስቀድም። አማራዎች በቅድሚያ ለአማራ ህዝብ መብት እንቁም። ያንን ለማድረግ የምንችለው ከኦሮሞ ወገናችን ጋር ጥንድ-ምሰሶ በመሆን እንጂ የኦሮሞን ሊሂቃን ማንነት በመናቅ አይደለም።
የኦሮሞን ማንነት ካልተቀበልን ፡ የቀድሞ ገዢዎቻችን በኤርትራ ላይ የፈጸሙትን አይነት የስትራቴጂ ስህተት እንደግማለን። የአጼ ሃይለስላሴ መንግስት ኤርትራን በኮንፌደሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር አዋህዶ ቢሆን ኖሮ የኤርትራ ህዝብ አሁን ባለበት ስቃይ ውስጥ አይገባም ነበር ፤ የብዙዎችም ህይወት በከንቱ አይጠፋም ነበር።
የአማራ ሊሂቃን እንንቃ!! ኤርትራ ጥቂት ሚሊዮን ህዝብ ብቻ የያዘ ነው ፤ ኦሮሚያ ግን ትልቅ ነው። አቅማችንን አውቀን ከኦሮሞ ሊሂቃን ጋር በመከባበር ፡ በመቀባበል እና በጋራ ጥቅም ላይ ባተኮረ ስትራቴጂ አሁን በላያችን ላይ የተንፈራጠጠውንና የበሰበሰውን የህወሃት መንግስት በቀላሉ ማንበርከክ እንችላለን።
አባ-መላ : ማይጨው እና እንዲሁም እነሱን መሳይ ወገኖቼ፦ የሻገተውን ፡ ያለፈበትን እና የነፈሰበትን ፤ እንዲሁም አማራዊነት የበላይ የሆነበትን ኢትዮጵያዊነት ለታሪክ እንተወው። ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን በቂ ምህዳር ባለው መድብለ-ብሄር ማንነት እንተካው።
ህወሃት በተንገዳገደበትና በበሰበሰበት በዚህ ወቅት አዲስ አስተሳሰብና አዲስ እይታ በመያዝ ለኢትዮጵያውያን ነጻነት እንታገል። የኦሮሞና-አማራ ሊሂቃን በዚህ መልክ በመስራት ወደ ድል እንገስግስ።
ከአክብሮት ጋር!
ቪቫ ኦሮሚያ! ቪቫ ኢትዮጵያ!
– – – – – – –
የጸሃፊው አድራሻ፦ yared_to_the_point@yahoo.com