የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ሕንጻውን በተቃውሞ ከበው ዋሉ

June 28, 2013

ቋሚ ሲኖዶስ በመጪው ማክሰኞ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ ይጠበቃል
‹‹በኀይል ላይ ኀይል ጨምሬ እጠብቅሃለኹ›› /ዘላለም/
‹‹መናፍቅን ማውገዝ እንጂ ሥልጣን መስጠት አይገባም›› /ደቀ መዛሙርቱ/
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት የኮሌጁን አስተዳደር ሕንጻ በመክበብ የማስገደጃ ርምጃዎችን መውሰድ መጀመራቸው ተገለጸ፡፡

ሐራ ተዋሕዶ ብሎግ እንደዘገበው፦
ደቀ መዛሙርቱ ዛሬ፣ ሰኔ ፳ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ከማለዳው 12፡30 ጀምሮ የአስተዳደሩን ሕንጻ መግቢያና ዙሪያ መተላለፊያዎቹን በመክበብ መምህራኑና የቢሮው ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች እንዳይገቡ ሲከላከሉና ቀደም ብለው የገቡትንም በትእዛዝ ቃል ሲያስወጡ መታየታቸው ተዘግቧል፡፡

‹‹ከማለዳው 12፡00 ላይ በመኝታ ክፍሎቻችን ኮሪዶሮች የፊሽካና የጭብጨባ ድምፅ ተሰማ፤ ከክፍላችን ስንወጣ ወደ አቡነ ጢሞቴዎስና ሌሎች መምህራን ቢሮ የሚያስገባው የሕንጻው ደረጃና መተላለፊያ በከፍታ ድምፅ በሚዘምሩ ተማሪዎች ተዘግቶ ነበር፤›› ያለ አንድ የተቃውሞው ተካፋይ የቢሯቸውን ቁልፍ ጥለው የሸሹ ሓላፊዎች እንደነበሩ ተናግሯል፡፡

የደቀ መዛሙርቱ ቁጣ የነደደባቸው የሹመት ተስፈኛው ዘላለም ረድኤትና የበላይ ሓላፊው ሊቀ ጳጳስ ከበባው እስኪያበቃ ድረስ በአካባቢው አልታዩም፡፡ የኮሌጁ ሪጅስትራር ሓላፊ ማልደው ገብተው ከተቀመጡበት ቢሮ በትእዛዝ ለመውጣት የተገደዱ ሲኾን ንጋት ላይ የመጡ ሦስት መምህራን ኹኔታው ተገልጾላቸው በክብር እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ በበላይ ሓላፊው ቀጥተኛ ትእዛዝ ጠቅ/ቤተ ክህነቱ በስኬሉ የማያውቀው ደመወዝ እንደሚከፈላቸው ከሚነገርላቸው ሦስት ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች አንዷ የኾነችው ልዩ ጸሐፊያቸው ከተግሣጽ ጋራ ከስፍራው እንድትርቅ መደረጉ ተገልጧል፡፡

ከቀትር በኋላ 7፡30 ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የአጣሪ ኮሚቴው አባላት ከኾኑት የፓትርያሪኩ ልዩ ጸሐፊ አቶ ታምሩ አበራ፣ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊና የአጣሪ ኮሚቴው ጸሐፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ፣ የአስተዳደር መምሪያ ዋና ሓላፊ መዝገበ ጥበብ ቀሲስ ዮሐንስ ኤልያስ ጋራ በመኾን ወደ ግቢው ደርሰዋል፡፡

ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ የአዳራሽ ውይይት ከማካሄዳቸው በፊትና በኋላ ከኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ጋራ መገናኘታቸው ታውቋል፡፡ 180 ያህል ከሚኾኑ ደቀ መዛሙርት ጋራ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱና ሓላፊዎቹ ባካሄዱት ውይይት በአጣሪ ኮሚቴው ተጠንቶ የቀረበው ባለሦስት ነጥብ የመፍትሔ ሐሳብ ስለምን ተግባራዊ እንደማይኾን ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች ከኮሌጁ አቅራቢያ ወደሚገኘው የአቡነ ጢሞቴዎስ መኖርያ ቤት ጎራ ብለው መውጣታቸውን የታዘቡት ደቀ መዛሙርቱ፣ ‹‹በአቡነ ጢሞቴዎስ ላይ ላለመወሰን የጓደኝነት ሥራ አትሥሩ፤ ከጓደኝነት ሃይማኖት ይበልጣል፤›› ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

ዘላለም ረድኤትን የኮሌጁ ዲን ለማድረግ በአቡነ ጢሞቴዎስ የሚደረገው ዝግጅት ፈጽሞ ተቀባይነት እንደማይኖረው ደቀ መዝሙሩ በግልጽ ተናግሯል፡፡ የአጣሪ ኮሚቴው ድካም ዋጋ ሊሰጠው እንደሚገባ የገለጹት ደቀ መዛሙርቱ፣ ‹‹መናፍቅን ማውገዝ እንጂ ሥልጣን መስጠት አይገባም፤›› በማለት ለዕረፍት በሚወጡበት በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ዘላለም ረድኤትን በዲንነት ለመሾም መታቀዱን በጥብቅ እንደሚቃወሙት አስታውቀዋል፡፡ የደቀ መዛሙርቱ ቁርጥ አቋም ‹‹በኀይል ላይ ኀይል ጨምሬ [ከኀይል ወደ ኀይል ተሸጋግሬ] እጠብቅሃለኹ›› እያለ ሲዝት የሚሰማውን የዘላለም ረድኤት ብርቱ የሥልጣን ምኞት በከንቱ የሚያስቀር ነው ተብሏል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ‹‹ሳይጣራ ሰው አይታገድም›› ብለው እንደነበረ ሁሉ ከኮሌጁ እንዲባረርና ስለ ሃይማኖቱ ሕጸጽ ወደ ሊቃውንት ጉባኤ ቀርቦ እንዲጠየቅ የተወሰነበት ዘላለም ረድኤት ማንነቱ ተጣርቶ ከታወቀ በኋላ የሚታየው ዳተኝነት እንደሚያሳዝናቸው አልሸሸጉም፤ ኮሌጁን ከመናፍቅ የመጠበቅ ግዴታ ያለባቸው በመኾኑም የዓመቱ ተመራቂዎች ይኹኑ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ጉዳዩን እስከ መጨረሻው በባለቤትነት እንደሚከታተሉት አስጠንቅቀዋል፡፡

ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የኮሌጁ ዲን እንዲኾኑ የተፈቀደላቸው መልአከ ብርሃን ፍሥሓ ጌታነህ ምድባቸው ወደ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የተቀየረው በዘላለም ረድኤት የተለመደ ክፉ ምክርና በአቡነ ጢሞቴዎስ እንቢታ ነው፡፡ የዘላለም ረድኤት ክፉ ምክር፣ ‹‹በማታ ተማሪ [የድጓ፣ ቅዳሴና ቅኔ ዐዋቂው መልአከ ብርሃን ፍሥሓ ጌታነህ በኮሌጁ ተከታታይ መርሐ ግብር ነው በዲግሪ የተመረቁት] እንዴት እንመራለን?›› የሚል እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ይህንንም ራሱ ዘላለም ሲያስረዳ፣ ‹‹በቀኑ መርሐ ግብር የሚገኘው የቴዎሎጂ ዲግሪ በማታው ተከታታይ መርሐ ግብር ከሚገኘው ዲግሪ ጋራ እኩል መታየት የለበትም፤›› በሚል መብራራቱ ተገልጧል፡፡

የኮሌጁን የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ በተለያዩ ማባበያዎችና ተንኮሎች በመቅረብ ጥቅሙንና ሥልጣኑን ለማስጠበቅ የሚጥረው ዘላለም ረድኤት፣ ያለደረጃው የኮሌጁን ሐላፊዎች (በተለይ ጥንተ ነውሩን የሚያውቁበትን)፣ መምህራንና ሠራተኞች በማሸማቀቅ ይታወቃል፡፡ ሐራዊ ምንጮች በተወለደበትና ባደገበት በሆለታ ኪዳነ ምሕረት አጥቢያ የሚያሰባስቧቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት ደግሞ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ወደ ፕሮቴስታንት አዳራሽ እየሰበከና እየመለመለ በማስኮብለል በሚገባ ይታወቃል፡፡ ዘላለም ረድኤት ለሊቀ ጳጳሱ እንደነገራቸው፣ አሁን በኮሌጁ ያለው የደቀ መዛሙርቱ ተቃውሞና የሚዲያ ዘገባዎችም በእርሱ ብቃት ማነስና መናፍቅነት የተቀሰቀሰ ሳይኾን ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን ሤራ ነው፡፡››

ብፁዕ ዋና ጸሐፊውና ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ለደቀ መዛሙርቱ የማረጋጊያ ትምህርትና ምክር ሰጥተዋል፤ በአጣሪ ኮሚቴው የቀረበው ሪፖርትና የመፍትሔ ሐሳብም የቋሚ ቅ/ሲኖዶስ አባላት ተሟልተው በሚገኙበት በመጪው ሳምንት ማክሰኞ በሚደረገው መደበኛ ስብሰባ ቀርቦ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥበትና ውጤቱን በማግሥቱ ረቡዕ እንደሚያሳውቋቸው ቃል ገብተውላቸዋል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች ውይይቱ እንዳበቃ በደቀ መዛሙርቱ ተወካዮች መሪነት የኮሌጁን መማርያና ማደርያ ክፍሎች፣ ቤተ መጻሕፍቱንና የምግብ ቤት አዳራሽ እንዲሁም መጸዳጃ ክፍሎች ሳይቀር ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፤ በኹኔታውም በእጅጉ ማዘናቸው ተገልጧል፡፡ መዝገበ ጥበቡስ ምን ተሰምቷቸው ይኾን?!

Previous Story

ሐረርነት እና ጎንደርነት!

Next Story

Health: እባካችሁ ንጥሻ ገደለኝ፣ አስም እንዳይሆንብኝ ፈርቻለሁ

Go toTop