በጎንደር ከተማ የሚገኘው የቤተ እስራኤላውያን መጠለያ ሙሉ በሙሉ ሊዘጋ ነው

June 28, 2013

በመስከረም አያሌው

በኢትዮጵያ የሚኖሩ ቤተ እስራኤላውያንን ለመጨረሻ ጊዜ ለማጓጓዝ በታቀደው እቅድ መሰረት የማጓጓዙን መጠናቀቅ ተከትሎ ለበርካታ ቤተ እስራኤላውያን ለመጠለያ እና ለመማሪያነት ሲያገለግል የነበረው የጎንደር ቤተ እስራኤላውያን መጠለያ ጣቢያ በመጪው መስከረም ሙሉ ለሙሉ እንደሚዘጋ ተገለፀ።
የእስራኤል አለም አቀፍ ልማት መምሪያን ጠቅሶ ብሉምበርግ ድረ-ገጽ እንደዘገበው ኢትዮጵያ ውስጥ በመኖር ላይ ያሉትን ቤተ እስራኤላውያን ለመጨረሻ ጊዜ የማጓጓዝ ስራ የፊታችን ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ይከናወናል። ቤተ እስራኤላውያኑን ለመጨረሻ ጊዜ ለማጓጓዝ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ከወዲሁ የተጠናቀቁ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የመጨረሻዎቹ ሁለት ሺ ቤተ እስራኤላውያንም በእስራኤል ባለሞያዎች ተለይተዋል። ለጉዞ የተዘጋጁት ቤተ እስራኤላውያንም የመጨረሻውን የህክምና ምርመራ እና ለእስራኤል ዜግነት የሚያበቃቸውን ምርመራ ማጠናቀቃቸው ታውቋል።
በርካታ ቤተ እስራኤላውያን ህይወታቸውን ሲመሩበት እና ወደ ተስፋይቱ ምድር እየሩሳሌም የመሄጃ ጊዜያቸውን ሲጠባበቁበት የነበረው በጎንደር የሚገኘው የቤተ እስራኤላውያን መጠለያ ጣቢያም የቤተ እስራኤላውያኑን መልቀቅ ተከትሎ መጠለያ ጣቢያው ሙሉ ለሙሉ ተዘግቶ ለሌላ አገልግሎት ይውላል ተብሎ ይጠበቃል።
የእስራኤል መንግስት በበኩሉ ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የሚገቡትን ቤተ እስራኤላውያን ለመቀበል ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጿል። ለበርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ቤተ እስራኤላውያን በተለያዩ ጉዞዎች ወደ እስራኤል ያመሩ ሲሆን፤ ባለፉት አስርት አመታት ውስጥ እስራኤል የገቡ እና እዚያው የተወለዱ ከ102ሺ በላይ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላውያን ማህበረሰብ በእስራኤል ይገኛሉ። ይህ በመጪው ሐምሌ መጨረሻ የሚደረገው የቤተ እስራኤላውያን ጉዞ የመጨረሻው ጉዞ መሆኑ እና ከእንግዲህ በዚህ መልኩ ወደ እስራኤል የሚገቡ ኢትዮጵያውያን እንደማይኖሩ ተገልጿል። በአሁኑ ወቅትም ወደ ሰባት ሺህ የሚጠጉ ፈላሽሙራዎች በመላው እስራኤል በስደተኞች መንከባከቢያ ተቋም ውስጥ ይገኛሉ።n

ምንጭ፡ ሰንደቅ ጋዜጣ

Previous Story

ኢሳት – በደረጀ ሀብተወልድ (ጋዜጠኛ)

Next Story

የምህረት ደበበ መፅሃፍ – (ከተስፋዬ ገብረአብ)

Go toTop