በነአቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ 28 ክሶች እንዲሻሻሉ ፍርድ ቤት በየነ

May 31, 2014

(ዘ-ሐበሻ) የቀድሞውን የጉምሩክ ባለስልጣን የእነ አቶ መላኩ ፈንታን የሙስና ክስ የሚመለከተው ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት በተጠርጣሪዎቹ የክስ መዝገቦች ክስ መቃወሚያ ላይ ዛሬ ብይን አስተላለፈ። ከአዲስ አበባ ለዘ-ሐበሻ የደረሱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዛሬው ዕለት የተሰየመው ችሎት ከሁለት ሳምንት በፊት ከሳሽ አቃቢ ህግና የተከሳሽ ጠበቆች ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያና ምላሽ ተንተርሶ ግልጽ ባልሆኑና ማብራሪያ በሚፈለጉ ጉዳዮች ላይ አከራክሮ ብይን ለመስጠት የነበረ ሲሆን በዚህም መሠረት 28 ክሶች እንዲሻሻሉ ፍርድ ቤቱ አዟል።

በዛሬው እለት የተሰየመው ፍርድ ቤት እንዳለው እነ መላኩ ፈንታን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ነጋዴዎች የሚገኙባቸው ሶስት መዝገቦች ውስጥ ከተካተቱ 138 ክሶች መካከል 28 የሚሆኑት እንዲሻሻሉ የተወሰነ ሲሆን በ3ኛው የክስ መዝገብ ከጉቦ ጋር የተያያዙ ክሶች ከዋናው መዝገብ እንዲነጠሉም ተወስኗል።

የቀድሞው የጉምሩክ ባለስልጣንት አቶ መላኩ ፈንታ “ከገቢ በላይ ሃብት ማካበት” በሚል የተመሰረተባቸውን ክስ በተመለከተም በመንግስት ከተቀጠሩ ወዲህ ያላቸው ገቢና ሌላም ገቢ ካላቸው ተዘርዝሮ እንዲቀርብ ፍርድቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ሰኔ 3 ቀን 2006 ዓ.ም የተሻሻለውን ክስ ለማየት ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን ለዘ-ሐበሻ የደረሱት መረጃዎች ጠቁመዋል።

Previous Story

Health: HPV ክትባት አብዛኛውን የአባለዘር እከክ (Genital Warts) እና አብዛኛውን የማኅጸን ነቀርሳ (Cervical Cancer) ለመከላከል ያስችላል

Next Story

በማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ፤ የሲኖዶስ ጉባኤ በፓትርያርኩና ጳጳሳቱ ፍጥጫ ተቋጨ – (አዲስ አድማስ ጋዜጣ)

Go toTop