እስክንድር ነጋ በታዛቢዎች አማካይነት ከአቢይ አህመድ ጋር የሚያደርገው ድርድር የአማራውን ህዝብ የተሟላ ነፃነት የሚያጎናፅፈው ወይስ ለዝንተ-ዓለም ኋላ ቀር ሆኖና ኑሮው ጨልሞበት እንዲቀር የሚያደርገው ?

January 27, 2025

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

 ጥር 19 2017(January 27, 2025)

ሰሞኑን እስክንድር ነጋ “እመራዋለሁ የሚለውን የፋኖ ክንፍ” በመወከል ከአቢይ አህመድ አገዛዝ ጋር፣ እሱ እንደሚለው ውይይት፣ በመሰረቱ ድርድር እንዳደረገ በተለይም እነ ሀብታሙ አያሌው በሚቆጣጠሩት የኢትዮጵያ 360 ዲግሪ ሚዲያ ሰምተናል። ከመንግስት ጋር ለማደራደር የተገኙት ታዛቢዎች ደግሞ የውጭ አገራት ዓለም አቀፋዊ ስም የተከናነቡ ድርጅቶች ናቸው። የእነዚህ ታዛቢዎች ዋና ተግባር ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ አንድ መንግስት አስተዳድረዋለሁ በሚለው ህዝብ ላይ ስንትና ስንት ወንጀል ከፈጸመ፣ ወይም ደግሞ ስልጣን ላይ ለመውጣት ርስ በራሳቸው የሚዋጉ ኃይሎች ህዝባቸውን ካጫረሱና ህዝቡም ተስፋ ከቆረጠ በኋላ የመጨረሻ መጨረሻ ለዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው የሚስማማና በቀላሉም የሚጠመዘዝ አገዛዝ በመመስረት ድሮ የነበረውንና አሁንም ያለው የተመሰቃቀለ ሁኔታ እንዲቀጥል ማደረግ ነው። ከእነዚህ ዐይነት ድርጅቶች በስተጀርባም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ወይም ሲአይኤ እንዳለበት ይታወቃል። የእነዚህ ተዛቢዎችም ዋና ዓላማ ከላይ የተጠቀሰው ነገር ብቻ ሳይሆን፣ አንድ አገዛዝ በህዝቡ ላይ የፈጸመው ወንጀል እንዲረሳ ማድረግ፣ ወይም ትክክል ነው ተብሎ ሰፊው ህዝብ እንዲቀበለው ማድረግና ወንጀል ፈጻሚዎችም ከማንኛውም ወንጀል ከተጠያቂነት እንዲያመልጡ ማድረግ ነው።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ እስክንድር ነጋ እመራዋለሁ የሚለው የፋኖ ክንፍ ከአቢይ አገዛዝ ጋር ለመደራደር መሻት በመሰረቱ የጠቅላላውን የአማራን ህዝብ ብቻ ሳይሆን፣ ጠቅላላውን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጎዳና የነፃነትና የዲሞክራሲ ፍላጎቱን የሚያጨልምበት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት እንዳይወጣም የሚያደርገው የከፋፍለህ ግዛው አካሄድ ነው። እስክንድር ነጋ በስልጣን ጥም ያበደና በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የበላይነት መንፈስ የታነፀ ግለ-ሰብ እንደሆነ ግልጽ ነው። ከወያኔ ጋር ባደረገው ግብግብ እስርቤት እንደገባ ይታወቃል፤ ብዙም ተሰቃይቷል። ይህንንም በመጠቀም በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች አግኝቷል። እነዚህ ደጋፊዎች ደግሞ እስክንድር ነጋን እንደ ጀግና ከመቁጠርና ከማመን በስተቀር እስክንድር ነጋ ምን ዐይነት ርዕይና ፍልስፍና እንዳለውና፣ የተወሳሰበውንም የአገራችንን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህል፣ የኢኮሎጂና የስነ-ልቦና ቀውስና፣ ሌሎች ልዩ ልዩ ችግሮች እንዴት እንደሚፈታ የሚያውቁት አንዳችም ነገር የለም። አብዛኛዎቹም ከመጮህና ግለሰብን ከማምለክ ውጭ በአጠቃላይ ሲታይ ሰለፖለቲካና፣ በተለይም ደግሞ ስለዓለም አቀፍ ፖለቲካ የሚያውቁት ምንም ነገር የለም። በተጨማሪም የወያኔና የአቢይ አህመድ አገዛዝ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በመደገፍ ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ተግባራዊ ያደረጓቸውን አገር አፍራሽና ህዝብን በታታኝ ነገሮች በመመርመርና በማጥናት የራሳቸውን ፍርድ ለመስጠት ያልቻሉና የማይችሉ ናቸው። ስለሆነም ይህንን የተደናበረና የአላዋቂ የማህበረሰብ ክፍል አካል ድጋፍ በማድረግ ነው እስክንድር ነጋ በቀላሉ ዕውቅናን ለማግኘት የቻለው።

የእስክንድር ነጋን የትግል የህይወት ታሪኩን ለተከታተለ የጠራ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ አመለካከት የለወም። 27 ዓመት ወያኔ ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜና፣ በአቢይ አህመድም ከተተካ በኋላ ሁለቱም አገዛዞች በጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያደረሱትን መጠነ-ስፊ ጥቃት፤ በተለይም በጦርነት፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና በማህበራዊና በሌሎችም ነገሮች የሚገለጸውን አንዳችም ሀተታ በፍጹም አልሰጠም። እንደሚታወቀው የህወሃትም ሆነ የአቢይ አህመድ አገዛዝ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በግብረ-አበሮቹ ኢትዮጵያን ለማፈረካከስና ሰፊውም ህዝባችን ድንብርብሩ እንዲወጣ ለማድረግ ስልጣን ላይ የወጡ ናቸው። ባለፉት ሰላሳ ሶስት ዓመታት በአገራችን ምድር የተካሄደው የኢኮኖሚ ፖሊሲና ጦርነቱም የኢትዮጵያ ህዝብ አጀንዳዎች ሳይሆኑ የአሜሪካን ኢምፔሪሊዝም አጀንዳዎች ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ የህወሃትም ሆነ የአቢይ አህመድ አገዛዝ በራሳቸው አስተሳሰብ  በመመራት አገራችንን በዕውቅ ለመግዛትና ህዝባችንን ከድህነት ለማላቀቅ ሳይሆን ለዝንተ-ዓለም ደሀና ለማኝ ሆኖ እንዲቀር ማድረግ ነው። በተጨባጭ በምድር ላይም የሚታየው ሁኔታ ይህንን ነው የሚያረጋግጠው። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የግብረ-አበሮቹም ዋና ዓላማ በነፃ ገበያና በነፃ ንግድ ስም አሳበው አንድን ኃይል ስልጣን ላይ ካወጡ በኋላ የአንድን አገር የጥሬ-ሀብት በመቆጣጠርና በመዝረፍ ሰፊው ህዝብ ደሀ ሆኖ እንዲቀር ማድረግ ነው። በዚያውም በስለላ ድርጅትና በከባድ መሳሪያ በታጠቀ ወታደር የሚታጀብ አገዛዝ በማድረግ ሰፊው ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነቱን እንዳይጎናፀፍ፣ ወይም በፍርሃት እንዲኖር ማድረግ ነው። በአብዛኛዎቹ የአፍሪካና በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ ያለው ሁኔታ ይህንን ነው የሚያረጋግጠው። በአንዳቸውም የአፍሪካና በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ በራሱ ፍልስፍናና በነፃ አስተሳሰብ እየተመራ አገሩን የሚያስተዳድር አገዛዝ በፍጹም የለም። ለዚህም ነው በአብዛኛዎቹ የአፍሪካና በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ ስንትና ስንት የጥሬ-ሀብትና ልዩ ልዩ ሰብሎችንና ፍራፍሬዎችን ለማፍራት ወይም ለማብቀል የሚችል ፍሬያማ መሬት እያለ ሰፊው ህዝብ በጣም ጥቂት በሆኑ፣ ለምሳሌ እንደ ቡና፣ ካካኦ፣ ሙዝና ኦቾሎኒ …ወዘተ. ምርቶች ላይ ብቻ በማትኮር በድህነት ዓለም ውስጥ የሚኖረው። የተለያዩ አገዛዞችም ዋና ዓላማ ይህ ዐይነቱ የአስተራረስና የአኗኗር ስልት እንዲቀጥል በማድረግ ሰፊው ህዝብ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ነፃና ሁለ-ገብ የሆነ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ ማድረግ ነው። ፍሪድሪሽ ሊስት የሚባለው የ19ኛው ክፍለ-ዘመን የኢኮኖሚና የፍልስፍና የጀርመን ምሁር የነበረውና የእንግሊዝን የነፃ ንግድ ፖሊሲ አጥብቆ የታገለው እንደሚያስተምረን አንድ አገር በማኑፋክቸሪንግ ላይ፣ እንዲያም ሲል በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የሆነ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚና ገበያ ከሌላት በውጭ ኃይሎች በቀላሉ ትጠቃለች፤ በባህልና አንድን አገር በሚያስተሳስሩ ልዩ ልዩ ነገሮችም ልትዳብር በፍጹም አትችልም እንደሚለን የህውሃትም ሆነ የአቢይ አህመድ አገዛዝ ይህ ዐይነቱ ነገር በአገራችን ምድር ተግባራዊ እንዳይሆን ነው የሰሩትና የሚሰሩትም። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነት አገዛዞች ዘራፊ አገዛዞች(Predatory States) በመባል ይታወቃሉ። በዓለም አቀፍ የፊናንስ ካፒታል ቁጥጥር ስር ያሉና በእነሱም የሚታዘዙ ናቸው።

እስክንድር ነጋ ዕውነተኛ ፖለቲከኛና የህዝብ ተቆርቋሪና፣ ለዕውነተኛ ዲሞክራሲና ነፃነት የሚታገል ቢሆን ኑሮ ይህ ሁሉ የኢምፔሪያሊስቶች መሰሪህ ተግባር በገባው ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ለህዝብና ለአገር ተቆርቋሪ፣ እንዲሁም ለዕውነተኛ ዲሞክራሲና ነፃነት እታገላለሁ የሚል ቢሆን ኖሮ በፍጹም አንድን ኃይል ወይም ህዝብን የሚከፋፍል ስራ ባልሰራ ነበር። የተከፋፈለ ኃይልና የጠላቶችን ሴራ በሚገባ የማያውቅ ደግሞ በምንም ዐይነት ዕውነተኛ ነፃነትን አያገኝም። ይህን ትተን አቢይ አህመድ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በህዝባችን ላይ፣ በተለይም በአማራው ወገናችን ላይ የፈጸመውን ፋሺሽታዊ ድርጊት ስንመለከት ማንኛውም ኃይል ከእንደዚህ ዐይነቱ ፋሺሽታዊ ኃይል ጋር እደራደራለሁ የሚል ከሆነ ራሱ ዲሞክራት አይደለም። ዋናው ፍላጎቱም በአቋራጭ ስልጣን ላይ ለመውጣትና የራሱን የስልጣን ጥም ለማርካት ብቻ ነው። እንደዚህ ዐይነት ኃይልም በመሰረቱ ዋናው ዓላማው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምንና የግብረ-አበሮችን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚታገል ነው ማለት ነው። ስለሆነም የእስክንድር ነጋ አካሄድና የከፋፍለህ ግዛው ስትራቴጂ በጥብቅ መወገዝ ያለበት ነው። ማንኛውም አገር ቤትም ሆነ ውጭ ያለ በአማራው ህዝባችን ላይ የደረሰውንና የሚደርሰውን በደል የሚያወግዝ ሁሉ የእስክንድር ነጋንና የግብረ-አበሮቹን የውንብድና ሴራ ማውገዝ አለበት። በሜዳ ላይ የሚዋደቁት የተለያዩ የፋኖ ድርጅቶች በዚህ ሳትወናበዱና ኃይላችሁን ሰብሰብ በማድረግ በዕውነተኛ ፍልስፍናና የሳይንስ መሰረት ላይ በመሰባሰብ ትግላችሁን ማፋፋም አለባችሁ። ከፋሺሽታዊው አቢይ አህመድና በብልፅግና ስም ከሚያወናብዱት ተከታዮቹ ጋር በመደራደርና የጋራ መንግስት በመመስረት የአማራውም ሆነ ጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነታቸውን ሊጎናፀፉ በፍጹም አይችሉም። አማራውም ሆነ ጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተሟላ ነፃነታቸውን ሊጎናፀፉና የተከበረ አገር ሊመሰርቱ የሚችሉት እንደዚህ ዐይነት የኢምፔሪያሊስቶች፣ በመሰረቱ ፋሽዝምን በሚያስፋፉት የሚደገፍና የሚመከር የአቢይ አህመድ አገዛዝና መሰረቱ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ሲወገድ ብቻ ነው። የእስክንድር ነጋም አካሄድና ርዕይ በፍጹም ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም። የእስክንድር ነጋ ርዕይ ቀኝ የሆነና ጠቅላላውን ህዝባችንን ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት ሊያላቅቀው የሚችል አይደለም። ህዝባችን እየተሽመደመደና ማንም የውጭ ኃይል እየመጣ እንዲጨፍርበት የሚያደርግ ፋሽሽታዊ አካሄድ ነው።  የእስክንድር ነጋ የትግል አካሄድም የኢትዮጵያ ህዝብ ዋና ጠላት ብቻ ሳይሆን የጠቅላላው የጥቁር ህዝብም ጠንቅ ነው። ምክንያቱም ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች እንደዚህ ዐይነቱን የተሽመደመደና ምንም ዐይነት ርዕይ የሌለውን ኃይል በመጠቀም ነው አንድን አገርና ህዝብ ለዝንተ-ዓለም ጨለማ ውስጥ በመክተት ነፃና የተከበረ አገር እንዳይገነባ የሚያደርጉት። መልካም ግንዛቤ!!

 

fekadubekele@gmx.de

www.fekadubekele.com

 

 

6 Comments

  1. የወንድሜ ፈቃድ ሃሳብ ሁለት ነገሮችን ይዟል። አንደኛው አማካሪ አስታራቂና ሰላም ፈላጊ መስለው በመሃላችን የሚገቡ የውጭ ሃይሎች ራስ ጠቀም ግብና አላማ ሲሆን ሁለተኛው የፋኖ አንድ ክንፍ ለሰላም እደራደራለሁ ማለቱ ለአማራ ህዝብ በጎነት የለውም የሚል ነው። የመጀመሪያው ሃሳብ እኔም የምጋራው በመሆኑ መፍትሄው መንቃትና ራስን ለውጭ ሃይሎች ተጠቃሚ ላለማድረግ ብልሃትን መፈለግና እሳትን በእሳት ሳይሆን በብልሃትና በዲፕሎማሲ መታገል ነው። ይህ ደግሞ የሚሆነው በምድሪቱ ሰላም ሲኖር ብቻ ነው። ያኔ ከውጭም ከውስጥም ሆነው እኛኑ ለማባላትና ለማዳከም ሥፍራ አይኖራቸውም።
    በመሰረቱ የፋኖ ሁለት ዓመት የዘለቀ ፍልሚያ የአማራን ህዝብ ሰቆቃ ያባባሰና ህዝቡን ወደ ኋላ የመለሰ ለመሆኑ ሥፍራው ላይ ተገኝቶ መመልከት ይቻላል። የስማ በለው ወሬ ተከትፎና ታሽጎ ስለሚቀርብ እውነቱን ለመለየት ያስቸግራል። ዛሬ በአማራ ክልል ማረስ ያቆሙ፤ ንግድ ቤታቸው የተዘጋ፤ ከትምህርት የተፈናቀሉ፤ ህክምና በማጣት የሚያልቁ፤ የሚበላና የሚጠጣ ጠፍቶ በረሃብ የሚያልቁ እልፎች ናቸው። የዚህ እልቂት መንስኤው ደግሞ የፋኖና የብልጽግና ፍትጊያ ነው። በመሃል ላይ እንደ ገና ዳቦ እሳት የሚዘንብበት ነጻ እናወጣሃለን የምንለው ያ መከረኛና በስሙ የሚነገድበት ህዝብ ነው። በሃበሻ ፓለቲካ ዋናው ችግራችን ሰላም በጦር መሳሪያ ሃይል ብቻ ይመጣል ብሎ የማመን በሽታችን ነው። ዘፈኑ፤ ግጥሙ፤ መጣጥፍና ዲስኩሩ ሁሌ በለውና በይው ስለሚል ሰከን ብሎ ነገሮችን ለማየት ጊዜ አይገኝም። ዘፈኑ የቂጥሽ የባትሽ፤ ፉከራ መጣሁብህ ወዪልህ በመሆኑ ቆም ብሎ ጦርነት ለሰው ልጅ አይበጅም በማለት በየብሄራቸው እሳት የሚቆሰቁሱትን ሁሉ ተው ይህን መንገድ ሞክረነው የተረፈን የለም አማራጭ እንፈልግ እንደማለት ዛሬም ጦርነት፤ ትላንትም ጦርነት ለማንም ለምንም አይጠቅምም።
    እስክንድር ነጋም ሆነ ሌሎች የፋኖ አመራሮች ማወቅ ያለባቸው በጋራ ከብልጽግና ጋር ሆነው የሚያፈናቅሉትንና የሚያወድሙትን ህዝብ ዞሮ ተመለሶ እንደነበረ ለማድረግ ጭራሽ የማይቻል መሆኑን ነው። የነቃ ብርሌ አይሆንም እቃ እንዲሉ። ጦርነት ጥሎ የሚያልፈው የሚታይና የማይታይ የስነ ልቦና ጠባሳ አይን ከሚያየው የስጋ ጉዳት የላቀ ነውና ጦርነትን ተደራድሮ ማቆም ብልህነት ነው እንጂ የሽንፈት ምልክት አይደለም። አዎን ይገባኛል የሃገራችን ነገር ” ቆርጥምን ሰድጄ ጎርድምን” እንዲሉ መሆኑን ለማወቅ ዋቢ ማቆም አያስፈልግም የምናየው ነውና። የ70 ዓመት አዛውንት ላይ የ6 ዓመት እስራት የሚፈርድ፤ የሚያጠቡ እናቶችን ጨለማ ቤት የሚዘጋ፤ በዚህም በዚያም የአማራን ህዝብ ቀን በሰጣቸው የኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኞች መሰቃየት ከአንድ ሃገር እመራለሁ ከሚል መንግስት የሚጠበቅ እንዳይደለ ግልጽ ነው። ግን ሃበሻና ፓለቲካ እንዲያ ነው ሁሉ መፈነካከት። ይህን እልፈት የለሽ የብሄር ፓለቲካና የክልል ስርግብ ለማርገብ የሚቻለው በጦር መሳሪያ ሳይሆን በሰላም ሙግት ነው ባይ ነኝ። የብልጽግናው መንግስትና የታጣቂ ሃይሎች ከየትኛውም ወገን ይሁን በሰላም ለሰላም መደራደር ሁሉንም አሸናፊ ያደርጋል እንጂ ተሸናፊ አይኖርም። ግን አንደራደርም የሚሉትም ወገኖች ቢሆኑ ከጅም ቢያመልጡ ከተኩላው ይፋጠጡ ስለሆነባቸው እንጂ ሰላምን የሚጠላ የታመመ ሰው ብቻ ነው። ለዚህ ነው ፋኖዎች ዋስትና ሰተውና ተቀብለው በሰላም ለመኖር ትጥቅ ማውረድ ያለባቸው።
    ባጭሩ የዓለም የፓለቲካ ኡደት ከሃገራችን የዘርና የክልል ፓለቲካ ጋር ተዳምሮ በህዋላ ሊጠፋ የማይችል እሳት ቦግ ብሎ ይነድና ምድሪቱን አመድ እንዳያደርጋት ማሰቢያ ጊዜው አሁን ነው። ወያኔን እናቶች እያለቀሱ ጦርነት እንዲቀር ሲለምኑት እንባቸውን ረግጦ የሆነውን አይተናል። አሁንም ገና አላረፈም። የፓለቲካ ንፋሱ አሁን ከመቀሌ ወደ አስመራ ነፍሶ የጠላቴ ጠላት በሚል ሂሳብ ሁለቱ ሃይሎች ጥምረት ፈጥረው ውጊያ አይጀምሩም ብሎ ማሰብ አርቆ አለማየት ነው። አምባገነኖች ለስልጣን ማቆያ ከሚጠቀሙበት ዋናው መሳሪያ ሰውን ለሃገርህ ለወገንህ ለድንበርህ ለነጻነትህ እያሉ ማፋለም ነው። ለዚህ ነው ሰላም ቀዳሚ አማራጭ የሚሆነው። በመሆኑም ሌሎችም የፋኖ እዞች የሰላም ድርድርን እንደ አንድ አማራጭ ማየቱ የተሻለ ነው ባይ ነኝ።

    • ተስፋይ

      ድርድር ስትል አእምሮህ ውስጥ ምን ሃሳብ አለ እስክንድርስ ሊያሳካ የሚችለው ምን ሊሆን ይችላል? እንደምታውቀው ትግሬዎች ኢትዮጵያን በዘር ካቧደኑ በኋላ ታሪኩም ትግሉም የሃብት ክፍፍሉም በዘርና በተሰጠህ ቦታ ሁኗል ከዚህ ስንነሳ እስክንድር ጎጃም፤ሸዋ፤ወሎ፤ጎንደር ኑሮ በዘሩ ችግር አልደረሰበትም አዲስ አበባ ነበር ኑሮውን ያደረገው ባልደራስ ብሎ መነሻና መዳረሻው ያልታወቀ ይዞት የተነሳው አላማ ምን እንደሆነ ሳይታወቅ ብድግ ብሎ ጫካ ገባ ተባለ።

      አንተ ደጋግመህ የምትኮንናቸው የአማራ ፋኖዎች ትግሬ ሃይል አደራጅቶ ደፍጥጧቸው ሲሄድ አብይና ሽመልስ ሲያላግጡ መዳረሻቸው አዲስ አበባ እንደሆነ ሲገባቸው “አገር ሲወረር ዝም ብሎ ማየት ባህልህ አይደለም ማርከህ ታጠቅ” ተባለ ለነብሱ ሳይሳሳ በተንቀለቀለው ጦርነት በባዶ እጁና በብትር ገብቶ ሃገር የምትጠብቅበትን ታላቅ ተልእኮ ፈጸመ። ቀራቅር ላይ በተደረገው ጦርነት የአማራ ወጣት የሰራው ጀብድ ወደፊት ኢትዮጵያ መልሳ ስትቋቋም በአቶ ተክሌ የሻው የፊት መሪነት በፊልምና በመጻፍ ይወጣል ብለን እናምናለን። የኢትዮጵያ ህዝብም ለህልውናው ሰው ሁኖ ተከብሮ እንዲኖር የአማራ ወጣት ምን እንዳደረገለት ግንዛቤ ይኖረዋል። የትግሬዎች ሃሳብ ተሳክቶ ቢሆን እንደ ሞሶሎኒ ህዝቡን ጠምደው እንደሚያርሱት ካለፈው ግፈኛ አገዛዛቸው ለመረዳት አስቸጋሪ አይሆንም።

      ጦርነቱ ካለቀ ከጥቂት ወራት በኋላ ሳይሆን ልክ ጦርነቱ እንዳለቀ አብይ መሃመድ “ድልን አትደልቁ” በማለት በሚዲያ ቀርቦ የነዛን ልጆች ሞትና ገድል አኮሰመነ ቀጥሎም “ጠብመንጃ ነካሽ አትሁኑ” ብሎ ተራ ስድብ ሰደበ በተከታታይ አማራው ላይ የሚተፋው ትፋት የጀመረው ልክ ወደ ስልጣን በመጣበት ጊዜ በባህር ዳር ኮንፍረንሱ ነበር ጠያቂው “እርሶ በሚመሩት መስተዳደር (ኦሮሚያ) ውስጥ ወንድሞቻችን ተገደሉ ተባረሩ ይህን ያስተካክሉን ተብሎ ቢጠየቅው ” ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ብላችሁ አማራ አማራ ስትሉ ነገሩን ታበላሹታላችሁ” በማለት ደነፋ። እንዲህ የአማራ ጥላቻ አጥንቱ ውስጥ ዘልቆ ለገባው አራጅ ነው ፋኖ ተምበርክኮ አብይ አህመድ እግር ይውደቅ የምትለን? ስለ አማራ ያለህ አመለካከት የተዛባ ነው ምክንያቱን ግን ከርቀት መገመት ይከብዳል። ይህ የመጀመሪያህ አይደለም ለሰላም የቆምክ በማስመሰል ፋኖን የቀጠቀጥክበት ብዙ ኮመንትህን ላቃብልህ እችላለሁ።

      ለመሆኑ ድርድር ምንድነው ማን ከማን ይደራደራል በድርድርስ የሚቀርቡት ጥያቄዎችና ግለሰቦች እነማን ናቸው መዳረሻውና ግቡስ ምንድነው? እነዚህ ሁሉ ታስበው ነው ተደራዳሪዎቹ ወደ ድርድር የሚቀርቡት። እስክንድር ነጋ ከላይ እንደጨረፍኩልህ የጥቃቱ ሰለባ አይደለም የሩቅ ሰው ነው ምሬ ወዳጆን፤ ማርሸት ጸሃዩን ወይም ሌሎችን ሁኖ አማራ ላይ የደረሰውን ችግር መረዳት ይከብደዋል። ሌላው ከጠቅላላው ፋኖ የእስክንድር ተከታዮች ከግምት አይገቡም ድርድር ሰጥተህ መቀበል ነው ምንም ለማይጎዳ ጠላት ምን ሊሰጡት ይችላሉ? የአዳነች አቤቤ ምክትል ሊያደርጉት ይችላሉ እሱም ይህን ካገኘ እንደ ብርሃኑ ነጋ ወይም ግርማ ሰይፉ፤ በለጠ ሞላ እድሜ ለብልጽግና እድገት በእድገት ሁነናል ይልሃል።

      ጥሩ ጽሁፎችን አንብበን አትርሱኝ በሚል መልኩ ውሃ ትቸልስበታለህ የሃሳብ ጥራት ያስፈልጋል የሚሰጠው ኮሜንት ጸሃፊው የጻፈውን ተንተርሶ መሆን አለበት ፍየል ወደዛ ቅዝምዝም ወዲህ በአብይ ሰልችቶናል። ለማንኛውም ጊዜው መልካም ነው ስለ ድርድር ከላይ ዶር በፍቃዱ የጻፈልህ አለ እሱም ካላረካህ ቆፈር ቆፈር አድርግ ድፍረት ይሆንብኛል እንጅ ቅልቅል የሌለህ ትግሬ ሳትሆን አትቀርም በፋኖ ጥላቻ ያበድክ። ከላይ እንደገለጸልህ በሻሸመኔ በጁዋርና፤በአብይ ፤ሽመልስ የተደራጁ ቄሮዎች በኦሮሞ የተገደለውን አጫሉን ለማካካስ ከተማውን በደም አበላ ሲያጥቡት ከንቲባው ለሽመልስ ምክር ቢጠይቅ “እናውቃለን ሁለተኛ አትደውልልኝ ግባና ተኛ” ነበር ያለው። ከነዚህ ሰዎች ነው ድርድር ይደረግ የምትለን?

      ሂትለር ጋር ድርድር ተደርጓል ትግሬዎች ጋር ድርድር ተደርጓል ጀርባቸው ተሰብሮ ክድርድር ውጭ አማራጭ ስለሌላቸው ተምበርክከው ስለጠየቁ ነው። ጃል ሰኚ ተደራድሮ ገብቷል እንደሚባለው የብርሃኑ ጁላ ምክትል ሁኗል ለጊዜው። የተነሳበት አላማ ተሳክቷል ሰምተሃል? እኛ አልሰማንም አንተ ሰምተህ ሊሆን ይችላል ።የሽመልስ ጦር ግን ሰኚ የነበረበትን ቦታ እያረሰው ነው። ሌንጮ ለታ፤ዳውድ ኢብሳ፤ዲማ ነገዎ በድርድር ገብተዋል የተደራደሩት ለነሱ ምቾት( ቤት፤ደሞዝ፤መኪና) እንጅ ቁመንልሃል ላሉት ህዝባቸው አይደለም። ጁዋር መሃመድም በድርድር ገብቶ ነበር ቢሊየነር ሲሆን የድሮው ጁዋር አልሆነም ሲከተለው የነበረው ቄሮ ወይ ከትምህርት ወይ ከስራ ሳይሆን ጫቱን እየበላ ጀርመን የሰጠውን ባንድራ አናቱ ላይ አስሮ ብቻውን ያወራል። እንደሚመስለኝ አንተም ለፋኖ የምትመኘው ድርድር እንዲህ አይነት ሳይሆን አይቀርም። በነገራችን ላይ ፋኖ ጫካ ገብቶ ተጎሳቁሎ ስታየው ምንም የማያውቅ የገበሬ ጦር አድርገህ ሳትገምተው አልቀርህም ለዚህም ይመስላል አዘውትረህ ምክሬን ስሙ ተናግሪያለሁ በሚል መልኩ ከስር የምትጽፍላቸው። ወዳጄ ነገሩ እንደዛ አይደለም በሁለት እጅ የማይነሱ ብዙ ምሁራን ውስጣቸው አሉ። አብይ ወድ ስልጣን ሲመጣ ኢንጅነር ስመኘውን ገድሎ ከዘይኑ ጀማል ጋር እየሳቁ ያወጡትን መግለጫ ተመልከተው፤ አሳምነው ጽጌ “ያለንበት ዘመን ካለፈው የከፋ ነው” ብሎ የአብይን አካሄድ በመረዳቱ ለአማራው ሚዛን ያስጠብቃሉ የተባሉትን እነ ዶክተር አምባቸውን ጨምሮ ምን እንዳደረገ የታወቀ ነው። ወደ ጫካ የገቡት ዶ/ር ፕሮፌሰሮችም ወደፊት ይህ ስርአት እስካለ ሰርተዉ መኖር ስለማይችሉ ያንን ለመከላከል መሰለኝ ጫካ የገቡት ይህ ውሳኔ ምን ያህል ጭንቀት እንዳለው ገምተው። አገኘሁ ተሻገር፤ብርሃኑ ነጋን፤አረጋዊ በርሄን….. ሁነው ስብሰባ ሲኖር ለአብይ ሻይ እያፈሉ መኖር ክብራቸውን ስለተፈታተነው እንደ አባቶቻቸው በክብር መሞትን የመረጡት። ስለዚህ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጥ። ለማንኛውም ጽሁፍ ከመላክህ በፊት ትንሽ አብላላው።
      ሰላም ሁን

      • እኔ ባለፈውና በአሁኑም የሃበሻ ፓለቲካ አንድ አማካይ የሆነ ነገር እታዘባለሁ። ሁሉ ነገር በጦርነት ይፈታል እያሉ ማላዘን። አንድ ጥይትና አንድ ሰው እስኪቀር በለው ያፋከሩት ጉዶች ነፍሴ አውጭኝ ብለው ያን ሰራዊትና ህዝብ ለሻቢያና ለወያኔ አስረክበው ነው የፈረጠጡት። በኢትዮጵያ የፓለቲካ ፓርቲ ታሪክ ውስጥ ሁለገብና ሁለአቀፍ የነበረው ኢሕአፓ እልፎችን አስበልቶና በልቶ የመከነው እርስ በእርሱ በመነካከስ ነው። ሻቢያ በኤርትራ ባርነት ወይስ ነጻነት በማለት ምርጫ ሰጠሁ ብሎ በ 99% ድምጽ ነጻነትን መረጠ የተባለው ህዝብ ዛሬ ላይ ከፊትና ከህዋላ እየተተኮሰበት ምድሪቱን ትቶ የሚሽሽ ሆኗል። 50 ዓመት ሙሉ በትግራይ ህዝብ የነገደው የወያኔ ጥርቅም ደግሞ እልፎችን አስጨርሶ ዛሬ ላይ ደግሞ ቋንጣና ድርቆሽ አዘጋጅ እንዋጋለን እያለን ነው። እንግዲህ ወንድሜ ወደ ኋላ ያለፈ ታሪካችን ስንመለከት አንተ ለምትለው ፍልሚያና የነጻነት ናፍቆት ትምህርት የሚሰጠን ሆኖ አናገኘውም። የድሃ ልጆችን ማስጨረስና መጨረስ ለብሄርም ሆነ ለሃገር የነጻነት ፍንጣቂ ጮራ አያስገኝም!
        ፋኖ አልተገፋም፤ የአማራ ህዝብ በሄደ በመጣው በደል አልደረሰበትም ያልኩበት ሥፍራ የለም። የእኔ ቀዳሚ ሃሳብ ለድርድርና ለሰላም መንገድም ቦታም መስጠት መልካም ነው ባይ ነኝ። ሲጀመር እከሌና እከሊት እያሉ ሰውን በስም በመጥራት የፓለቲካ ጥላሸት መቀባት ማወቅ አይደለም። ስለዚህ ከላይ በስም እየጠራህ የኮነንካቸውን ሰዎች ስታጣጥል የራስህንም ሃሳብ እያጠለሸህ መሆኑ ሊረዳህ ይገባል። ስድብ፤ ዘለፋ፤ ያዙኝ ልቀቁኝ ባይነት የሃገራችን ቋጠሮ ያጠብቃል እንጂ ውሉን እንድንፈልግ ጊዜ አይሰጠንም። አንተና መሰሎችህ ተቆርቋሪ የሆናችሁለት የአማራ ህዝብ ደግሞ ሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ገብቶ በረሃብ፤ በበሽታና በጦርነት እየተጠበሰ ይገኛል። ፋኖና ሌሎችም ጠበንጃ አንጋቾች እንዘጥ እንዘጥ የሚሉባት የሃበሻ ምድር ያላት አንድ አማራጭ በሰላም ነገሮችን በመፍታት የብልጽግናን መንግስት በምርጫ ማሸነፍ ነው። የትጥቅ ትግልን እንደ አማራጭ የያዙ ወገኖች ግን ሊገነዘቡ የሚገባቸው ፍልሚያው እስከ መቼ ነው? በመሃል የሚጎዳው ማን ነው በማለት ሊያገናዝቡ ይገባል። አሁን የአማራ ክልል እየተባለ በሚጠራው ስፍራ ያለው ሁኔታ ለሁሉ አማች ነው። ህዝቡ ማንን ተገን ያድርግ? አጋችና ዘራፊውን መለየት ያልተቻለበት ጊዜ ላይ ነን። የመንግስት ታጣቂ ይሁን ፋኖ ወይም ሌላ በፋኖ ስም የሚነግድ ሊታወቅ አይችልም። በምድሪቱ ህግና ስርዓት ፈርሷልና! በማህል እንደ ገና ዳቦ እሳት ውስጥ ያለው የአማራ ህዝብ ነው። ይህ ሊገታ ይገባል። ለሰላም መንገድ መስጠትም አንድ አማራጭ ነውና ይሞከር ባይ ነኝ። በቀረው የእኔና አንተን የመሰሉ ወገኖች እዚህ ድህረ ገጽ ላይ መጎሻሽም ለሃገራችን ሰላምና ብልጽግና የሚቋጥረው ፍሬ የለም። ለሰላም መቆሜ ካልተዋጠልህ መተው መብትህ ነው።

  2. ሰላም ወንድም ተስፋ በመጀመሪይ ጽሁፌን ስላነበብክና ስለ ወንድማዊ ትችትህም አመሰግናለሁ። አዎ እኔም በሰላም የማምንና በአንድ አገር ውስጥ ያለ ችግር፣ በተለይም በጦር የሚካሄድ ትግል በሰላም መፈታት እንዳለበት አምናለሁ። የተሟላ ሰላም ሲኖር ብቻ ነው የአንድ አገር ህዝብ ሃሳቡን በመሰብሰብ በአገር ግንባታ ላይ ሊሰማራ የሚችለው።
    ይህ እንደዚህ እንዳለ ሆኖ በመጀመሪያ ደረጃ ሁላችንም ማወቅ ያለብን እ.አ በ2018 ዓ.ም አቢይ አህመድ ከወያኔ ስልጣን ሲረከብ አብዛኛዎቻችን አሜን ብለን ነው የተቀበልነው። ይህንን በሚመለከት እኔም በጊዜው የፖለቲካ ሂደቱ እንዴት መያዝ እንዳለበትና፣ ቅድሚያም መሰጠት ባለባቸው ነገሮች ላይ ሰፋ ያለ ሀተታ ሰጥቻለሁ። የነገሩን ሂደት ተከታትለህ ከሆነ አቢይ አህመድ ስልጣኑን ከተረከበ ከአንድ ዓመት በኋላ ውስጥ ለውስጥ ባደራጀው ኃይል በተለይም ኦነገዎችን በማሰማራት በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ወይም ምዕመናን ላይ በመነሳት ቁጥራቸው የማይታወቁ ምዕመናን እየተሳደዱ ተደብድበዋል። ቤተክርስቲያናትም ወድመዋል። ሸዋ ውስጥ የሚገኙ የንግድ ከተማዎች እንዳለ ወድመዋል። ራሱ ሻሸመኔ በኦነግ ሰዎች ነው ልትወድም የቻለችው። በጊዜው የከተማው ከንቲባ ኃይል እንዲላክለት ለእነ ሺመለስ አብዲሳ ሲደውል አርፈህ ተቀመጥ ነው የተባለው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ከዚይ በኋላ ኦሮሚያ ክልል በሚባለው ቦታ እጅግ በተመሰጣጠረ መንገድ እየሰራና እየነገደ በሚኖረው አማራው ወገናችን ላይ በመነሳት ቁጥራቸው የማይታወቁ ብዙ አማራዎች ተገድለዋል። ራሳቸው አማራ አግብተው የሚኖሩ የኦሮሞ ሴቶችም አርግዘው ለመውለድ ከደረሱ በኋላ ወደ ሆስፒታል ሲሄዱ ከአማራ ተጋብተው መኖራቸው ስለታወቀ ተገቢውን ህክምና ሳያገኙ እንደተሰቃዩ በጊዜው ተመዝግቧል።
    ወደ አማራው አካባቢ ስለሚካሄደው ጦርነት ጋ ስንመጣ በመጀመሪያ ደረጃ ጦርነቱን የከፈተው የአቢይ አህመድ ወታደር ነው። እንደሚታወቀው በአማራው ክልል ብቻ ሳይሆን በኦሮሞ ክልልም የታጠቀ ኃይል አለ። ይሁንና ወያኔ በተደጋጋሚ በከፈተው ጦርነት የሚሰቃየውና የሚገደለው የአማራው ህዝብ ነው። ወያኔ በከፈተው የመጀመሪያው ጦርነት ወያኔ ሊሸነፍ የቻለው በአማራው ልዩ ኃይልና በፋኖዎች ቆራጥ ትግል ነው። የኋላ ላይ ወያኔ ከተዳከመ በኋላ ትንሽ ወራት ከተቆየ በኋላ ወያኔ አዘናግቶ በአማራው ላይ ጦርነት ይከፍታል። በወሎ ውስጥ የደረሰውን ግፍ፣ የከተማ ውድመትና፣ የሀብት ዘረፋ የተከታተልክ ይመስለኛል። ወያኔም በጊዜው ሰተት ብሎ ሊገባ የቻለው የአቢይ አህመድ ወታደሮች ሁኔታውን ስላመቻቹለትና አማራውም ፊዚካሊም ሆነ ሳይኮሎጂካሊ እንዲዳከም ታስቦ ነው። በዚህም አማካይነት አማራው ሲዳክምና አቅምም ሲያጣ ለመከላከል ስለማይችል በቀላሉ ታላቁን ኦሮምያ መገንባት እንችላለን የሚል ስሌት አለ። በመሰረቱ የአንድ የማዕክላዊ አገዛዝ ኃላፊነትና ዋና ተግባር በተለይም እንደዚህ ዐይነት የውጭ ጠላት በመመሰል የሚመጣን ኃይል፣ ወያኔን ማለቴ ነው፣ ከአካባቢው ህዝብና ታጣቂ ኃይል ጋር መክቶ መመለስ ሲገባ አቢይ አህመድና ግብረ-አበሮቹ እንደዋና ጠላት አድርገው የወሰዱት የአማራውን ህዝብና ፈናዎችን ነው። ስለሆነም ከሁለት ዓመት ጀምሮ የሚካሄደው ጦርነት የአማራውን ህልውና ለመከላከል የሚደረግ ትግል ስለሆነ በመሰረቱ በፋኖዎችና በእነ አቢይ አህመድ መሀከል ብቻ የሚደረግ ጦርነት አድርጎ መውሰድ እጅግ አደገኛ ነው። ጠቅላላውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጠጋ ብለህ ተከታትለህ እንደሆነ ወያኔዎችም ሆነ እነ አቢይ አህመድ ብሄረሰቦቻቸውን ሽፋን አድርገው የሚታገሉት የሰፊውን ህዝቦቻቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የስነ-ልቦናዊና ሌሎችም ችግሮች ለመቅረፍ ሳይሆን በውጭ ኃይል እየታዘዙና እየታገዙ የራሳቸውን የስልጣን ጥም ለማርካት ብቻ ነው። የሚያስጠብቁትም ጥቅም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን ጥቅም ነው። ወያኔም ሆነ በአቢይ አህመድ የሚመራው ብልጽግና ፖለቲካ ማለት ምን ማለት እንደሆን የገባቸው ቢሆን ኖሮ እንወክለዋለን የሚሉትን ህዝባቸውን ችግሩን ሊቀርፉለትና ሰላማዊ ኑሮም እንዲኖር ማድረግ የሚችሉት በተለያዩ ጊዜያት አዳዲስ ቅራኔዎችን በመፍጠር ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚስማማ አጀንዳ መተለም ሲችሉ ነበር። ይሁንና ባህርያቸውና ወይም በመንፈሳቸው የቀረጹት አጉል ስሌት ስላለ ፖለቲካሊ ማሰብ የሚችሉ አይደሉም። ስለሆነም አዳዲስ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመፍጠር ጠቅላላውን ህዝባችንን በቀላሉ ሊወጣ የማይችለው ማጥ ወይም ችግር ውስጥ ከተውታል። በአማራው ክልል የሚካሄደውን ጦርነት ትተን በኮሪዶር ልማት ስም አዲስ አበባ ከተማው ውስጥ የሚካሄደውን የቤቶችን ማፈራረስ ስንመለከት ስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች የሚሰሩትን ስራ የሚያውቁ አይደሉም። እንደዚህ ስል ከተማዋ መጽዳት የለባትም፤ አዳዲስ ቤቶችም መሰራት የለባቸውም ማለቴ አይደለም። ለማለት የፈለጉት አንድን ከተማ በተሻለ መንገድና ለሁሉም ህዝብ በሚስማማ መልክ እንደገና ለማዋቀር ከተፈለገ ከአምስት እስከ አስር ዓመት የፈጀ የከተማ ዕቅድ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የከተማ ግንባታ ዕቅድ አውጭዎች፣ አርኪተክቸሮች፣ ሶስዮሎጂስቶች፣ ሳይኮሎጂስቶችና ኢኮኖሚስቶች አንድ ላይ በመሆን በማጥናትና የመጨረሻ ላይ አንድ ውጤት ላይ ከደረሱ በኋላ ቤቶችን በዕቅድ መስራት ይቻላል። ከተማይቱንም በአዲስ መልክ ማዋቀር ይቻላል። እንደምታውቀው በአንድ ከተማው ውስጥም ሆነ በአንድ አገር ውስጥ ቤት ተከራይተው ወይም ገዝተው ለመኖር የሚፈልጉ ሀብታሞች ብቻ ሳይሆኑ ደሃውም ወይም ደግሞ አነስተኛ ገቢም ያለው ህዝብ ቤት ተከራይቶ ለመኖር ይፈልጋል። ይህም ማለት ከተማይቱን በአዲስ መልክ ማዋቀር አለብኝ ብሎ አንድ የከተማ አስተዳደር ሲነሳ በግምት ወይም በአቦሰጡኝ ሳይሆን ብዙ ነገሮችን ግምት ውስጥ ማስገባት አለበት። ካለበለዚያ በአቦሰጡኝ የሚሰሩ ስራዎች ልንወጣው የማንችለው የማህበራዊ፣ የባህልና የህሊና ቀውስ ውስጥ ነው የሚከቱን። አዳዲስ አገዛዞችም ስልጣንን ሲረከቡ በዚያው ነው የሚቀጥሉት። እንደዚህ ዐይነት በአቦሰጡኝ የሚካሄድ የከተማ ግንባታና የቤት ስራ በተለያዩ የሶተኛው ዓለም አገሮች ዋና ከተማዎች ውስጥ የሚታዩ ናቸው። ሌጎስ፣ ናይሮቢ፣ አክራና፣ ሌሎችም የማዕከለኛውና የደቡብ አሜሪካ ከተማዎች ያለው ችግር ይህ ነው። በየአገሮች ውስጥ እንደሰው ማሰብ የማይችሉ አዳዲስ የንዑስ ከበርቴው መደብ ኃይሎች ስለተነሱና ስልጣንንም ስለተቀዳጁ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመመሰጣጠር እንደ እኔ ያለውን መናጢ ደሃ ህዝብ መቆሚያና መቀመጫ እያሳጡት ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ማፊያዊ ስራን ለሚሰሩ፣ ለሌቦችና ለማጅራት መቺዎች አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። ስለሆነም ሁሉም ነገር በተጠናና ግልጽ በሆነ መልክ ከረጅም ጊዜ አንፃር መታቀድና መገንባት አለበት። ለከብቶች ማደሪያ እንኳ በረት ሲሰራ ታስቦና ታቅዶ ነው። የሰው ልጅ ሰውም ስለሆነ አጠረ ረዘመ፣ ደሃ ሆነ ሀብታም ሁሉም ክብርን ይፈልጋል። ከዚህ አንፃር ስንነሳ አዲስ አበባ ውስጥ የሚሰሩትን ቤቶች ወይም አፓርትሜንቶች ስትመለከት ማን እንደሚከራይ፣ ወይም ገዝቶ መኖር እንደሚችል ግልጽ አይደለም። ከበስተጀርባው ያሉት አሰሪዎችም እነማን እንደሆኑ የሚታወቅ ጉዳይ አይደለም። እንደምገምተው ክሆነ የሚሰሩትንም አፓርተሜንቶችና ቪላቤቶች በቪዲዮ ስመለከት በአገር ውስጥ ከበርቴዎች ወይም በመንግስት ብቻ የሚሰሩ አይደሉም። ለማንኛውም ስለጦርነት አላስፈላጊነትና ሰለ ሰላም አስፈላጊነት ሲወራ እነዚህ ነገሮችም ከቁጥር ውስጥ መግባት አለባቸው። በየከተማዎች ውስጥ እንደዚህ ዐይነት ወንጀል የሚሰራ አገዛዝ በተቀረው ሰፊው ህዝባችን ላይም ጦርነት ከማካሄድ የሚመልሰው ነገር የለም። የሚያካሂደውም ጦርነት የውክልናና አገሪቱን በአጠቃላይ ለመበወዝና ሰፊውም ህዝብ ብዥ ብሎበት አቅጣጫውን እንዲያጣና የኑሮንም ትርጉም እንዳይረዳው ለማድረግ ነው። ከዚህ ሁኔታ ስነሳ እነአቢይ አህመድና በተቅላላው የብልጽግና ሰዎችና ሌሎችም በኢሊት ደረጃ የሚቆጠሩት ምሁራዊ በሆነ መንገድ በተወሳሰበ ነገር በማሰብ ጤናማ ስራዎችን ለመስራት የሚችሉ አይደለም። ችንቅላታቸው በተበላሸ መልክ ስለተቀረፀ ወይም ፕሮግራምድ ስለሆነ ሁልጊዜ የሚታያቸው አመጽ ነው። ችግሮችንም በአሻጥርና በጉልበት መፍታት የሚችሉ ነው የሚመስላቸው። በተለይም የስውን ልጅ የህሊና አወቃቀር አስመልክቶ እንዴት በተበላሹ ሁኔታዎች መንፈሱ እንደሚቀረጽን ወደ አመጽም እንደሚያመራ ግሩም ግሩም በሆነ መልክ የተደረሱ የህሊና ሳይንስ መጽሀፎች አሉ። የአንድ ሰውም መጥፎም ሆነ ጥሩ አስተሳሰቡ የሚቀረጸው ከልጅነቱ ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ ይታወቃል። ስለሆነም ከእኛ አገር ስልጣኝኝ ከተከናነቡ ሰዎች ብዙ ቁም ወይም ቀና ነገር መጠበቅ ስህተት ይመስለኛል።
    ወደ መሰረተ ሃሳብህ ስመጣ እስክንድር ነጋ ከፋኖዎች ጋር ሆኖ የሚታገልና በአመራር ውስጥም እስካለ ድረስ ብቻውን የጎን ውይይት ወይም ድርድር ከእንደዚህ ዐይነት ፋሽሽታዊ ከሆነ አገዛዝ ጋር ማድረግ አልነበረበትም፤ የለበትም። በእኔ ዕምነትና ሳይንሳዊ ግንዛቤ አቢይ አህመድና ግብረ-አበሮቹ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እየተጠመዘዙ ነው በህዝባችን ላይ ጦርነት የሚያካሂዱት። ስለሆነም አርበኛ ነው ወይም አይበገርም ብለው የሚያስቡትን ኃይል በማዳከም ወይም በመደምሰስ በኢትዮጵያ ምድር ለራሳቸው የሚስማማ ቅምጥ አገዛዝ ማስቀመጥ ይፈልጋሉ። ይህንን ዕቅዳቸውን ዘለዓለማዊ ለማድረግ የሚችሉት ደግሞ በአገራችን ምድር የእነሱን እርኩስ ተግባርና ዓላማ የሚቃወመውን መደምሰስ ከቻሉ በኋላ ነው። ለጊዜው ህወሃትንና አቢይን ተጠቅመው አገራችንን እዚህ ዐይነት ደረጃ ላይ አድርሰዋታል። ወደፊትም አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር ይፈልጋሉ። ለዚህ ደግሞ ኃይልን የሚከፋፍል ተላላኪ ኃይል አዘጋጅተዋል። ይህም እስክንድር ነጋና ከአሜሪካ ሆኖ የሚያቀነባብረው እነ ሻለቃ ዳዊትና አንዳንድ ከሃዲዎች ናቸው። ስለሆነም ነገሩ መታየት ያለብት ከሁለመንታዊ አንፃር በመነሳትና የውስጥ ቡችላ ኃይሎች ከውጭው ኃይል ጋር ተመሰጣጥረው በመስራት ህዝባችን እንደ ሰው መኖር እንዳይችል ከሚደረገው ስሌት አንፃርም መመርመር አለበት። ስለሆነም እነአቢይ አህመድና ግብረአበሮቹ፣ እንዲሁም ሌሎች የአሜሪካ ቡችላዎች ከቁጥጥር ውስጥ እስካልገቡ ድረስ ወይም እስካልተወገዱ ድረስ በአገራችን ምድር ዘላቂ ሰላም በፍጹም አይገኝም የሚል ዕምነት አለኝ። የኢትዮጵያ ህዝብ የተሟላ ዕድገትና ሰላምን ይፈልጋል። መስራት የሚችል ዜጋ ሁሉ እየሰራ መኖር ይፈልጋል። ትምህርት ቤት ገብቶ ለመማር የሚፈልገው ሁሉ አመቺ ሁኔታዎች ያስፈልጉታል። ለዚህ ደግሞ ጠቅላላውን ህዝብ ሊያስተባብር የሚችልና የውጭ ኃይሎችን አጀንዳ የማይከተል ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ያስፈልጋል። ስለዲሞክራሲያዊ አገዛዝም ስናወራ በዲሞክራሲዊ መርሆች ላይ መቋቋም ስላለባቸው ተቋማትም ማውራት አለብን። ይህም ማለት ህዝባችን የተማሏ አገልግሎት ሊያገኝ የሚችለው ዘመናዊና ዲሞክራሲያዊ ተቋሟ ሲገነቡ ብቻ ነው። ካለበለዚያ ትግል የሚባለው ነገር መረሳት አለበት። እነ አሜሪካና ግብረአበሮቹም በምንም ዐይነት ይህ የተቀደስ ዓላም በአገራችን ምድር እንዳይተገተበር ያልተቋረጠ ትግል ያደርጋሉ። የእኛ ትግል ደግሞ የእነርሱን እርኩስ ዓላማ ማጨናገፍ መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ የጠራ አመለካከትና ትብብር ያስፈልጋል። ሁሉም ኃይል ህዝባችንን ሊያሰባስብና የመንፈስም ጥንካሬ ሊሰጠው በሚችል ርዕይ ዙሪያ መሰባስብ አለበት። ይህም ማለት የውጭ ኃይሎችን መለማመጡን ማቆም አለበት። የዲፕሎማሲም ትግል ብሎ ነገር የለም። በተረፈ አመሰግናለሁ።

    ፈቃዱ በቀለ

  3. ወንድሜ ፈቃድ – እይታችን ያው ነው። የህዝባችን ሰላምና አንድነትን ማስቀደም። እንዴት፤ በየት፤ ወዴትና መቼ እንደርሳለን የሚለው ጉዳይ ግን ለእኔም ለአንተም ጊዜ የሸፈነው በመሆኑ አልታየንም። ከምናየውና ከሚዳሰሰው ስንነሳ ግን ሃገራችን ጭንቅ ላይ እንዳለች አከራካሪ አይሆንም። የዚህ የመከራ መርዝ ደግሞ በወያኔ የተረጨ የክልልና የብሄር ፓለቲካ ነው። አሁን ላይ ደግሞ የኦሮሞ ምሁራን ጨልጠው የጠጡት የዘርና የቋንቋ ፓለቲካ ይኸው እንሆ እያፋጀን ይገኛል። መስሎን እንጂ በዚህ ሂደት ጊዜአዊ አትራፊ እንጂ ቋሚ አትራፊ አይኖርም። የዓለም የፓለቲካ ንፋስና የአፍሪቃው የትርምስ መሬት ሰንብቶ የሚወልደውን በጭራሽ መገመት አይቻልም። ግን ዝንተ ዓለም ሲገዳደሉና ሲፋለሙ ከመኖር አጭር ዘመን፤ አጭር ህይወት በሰላም ኑሮ ማለፍ ምንኛ ይናፍቃል። ያ ግን በሃበሻ ምድር የሚገኝ ሃብት አይደለም። ያለፈውን የከፋ የከረፋ ስርዓት ዛሬ ላይ ሰዎች ሲናፍቁት መስማትና ማንበብ የዛሬውን ድርቡሻዊ አገዛዝ ከበፊት መክፋት ያሳያል። ስናሳዝን። ለዚህ ይሆን ገጣሚው እንዲህ ያለው። ሰላምህ ይብዛ ዶ/ር ፈቃድ!
    የትናትናውን ዛሬ ላታገኘው
    ብለህ አትናገር ደሞ ለዛሬ ሰው
    ቀኑን ከተረከብክ እስከ አሰስ ገሰሱ
    የዛሬ ሆነሃል አንተም ልክ እንደ እርሱ። (ግጥም ማቴዎስ ከተማ)

  4. ሰላም ውድ ወንድሜ አቶ ተስፋ የምትለው በከፊል ዕውነት ሊሆን ይችላል። ጥያቄው ግን ህወሃትም ሆነ ሌሎች የብሄረሰብን አርማ ይዘው የተነሱ፣ ወይም ደግሞ ተጨቁነናል፣ መብታችን ተገፏል ብለው ግብግብ ውስጥ ሲገቡ ከራሳቸው አንፃር ብቻ ሳይሆን ከጠቅላላው የህዝባችን ሁኔታ በመነሳት በጊዜው የነበረውንና በልዩ ልዩ መልክ የሚገለፀውን ችግር ለምን ማየት ተሳናቸው? የሚለው ጥያቄ ነው መነሳት የነበረበት። በሌላ አነጋገር፣ በእኔ ዕምነት የነበረው ጭቆና ከፊዩዳላዊ ስርዓት ጋር መያያዝ የነበረበትና፣ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍልም የሚመለከት ነበር። አብዛኛዎቹ ችግሮችም ሆን ተብለው የተፈፀሙ አልነበሩም። ጠለቅ ያለ ንቃተ-ህሊና ባልዳበረበትና ሰፋ ያለም ምሁራዊ እንቅስቃሴ በሌለበት አገር ውስጥ ነገሮች በሙሉ እንደልማድ ወይም እንደተፈጥሮአዊ ተደርገው ይወሰዱ የነበረው። እዚህ አውሮፓ ውስጥም ከፊዩዳሊዝም ወደ ካፒታሊዝም የተደረገውን ሽግግርና መሠረታዊ ለውጥ ስንመለከት ምሁራዊ እንቅስቃሴ ወደ 600 ዐመት ፈጅቷል። አልፎ አልፎ የጦር ትግል የሚካሂድ ቢሆንም አብዛኛው እንቅስቃሴ በምሁራዊ ጥናትና ምርምር የተደገፈ ነበር። ለዚህ ነው ለህብረተሰብ ለውጥና ዕድገት የሚጠቅሙ እንደ ፍልስፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ኢኮኖሚክስ፣ ሶስዮሎጂ…ወዘተ. የመሳሰሉ ዕውቀተች ሊፈልቁና ሊዳብሩ የቻሉት። በዚህም ምክንያት ነው ካፒታሊዝም ሲስፋፋና የምርት ኃይሎችም ሲዳብሩ በዚያው መጠንም ጭንቅላት አርቆ ማሰብ የቻለው። ወደ አገራችን ስንመጣ ግን በጭንቅላት ስራ ላይ ከመረባረብ ይልቅ አትኩሮአችን በጦር ትግል ላይ ስለሆነ ጭንቅላት ከመዳበር ይልቅ እየቀጨጨ ሊመጣ ቻለ። ጭንቅላት በቀጨጨበት አገር ውስጥ ደገሞ ራሽናሊ ማሰብና መወያየት በፍጹም አይቻልም። ምሁራዊ ውይይት ከሌለ ደግሞ ማመንና ማሳመን በፍጹም አይቻልም። እንደምናውቀው የየብሄረሰቦች መሪዎች ነን የሚሉት ትንሽ ፊደል የቆጠሩና አንዳንዶችም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገብተው የመማር ዕድል ያገኙ ነበሩ። መማር ማለትም ለመመራመርና አንድንም ችግር ከተወሰነ ሁኔታ በመነሳት መመልከት ሳይሆን ጠቅላላውን የአገሪቱን ሁኔታ በመውሰድ መመርመርና ጭቆና አለ ከተባለ ስልጣን ላይ የነበሩትን ሰዎች የተወሰነ የዕውቀት መሠረታቸውንም መመርመር በተገባ ነበር። እንደሚታወቀው ዕውቀትና ንቃተ-ህሊና አንድን አገር ለሚያስተዳድሩ ሰዎች ወሳኝ ነገሮች ናቸው። ምክንያቱም ንቃተ ህሊናው የዳበረ ሰው ኃላፊነት ይሰማዋል፣ ጥያቄም ያነሳል፣ በምድር ላይ የሚታዩ ነገሮችንም ዝምብሎ አያልፍም፣ በአጭሩ የሚሰራው ስራ የሰለጠነ ይሆናል። ስለሆነም እነዚህ ነገርችን ሳይመረምሩ አንዳች ችግርን ሊፈጥር የሚችል ውሳኔ ላይ መድረስ በችግር ላይ ችግር መደረብ ይሆናል። በሌላ አነጋገር ጨቋኝ የሚባሉት የህብረተሰብክፍሎች በጊዜው ይሰሯቸው የነበሩ ነገሮች በአቦሰጡኝ ስለሆነበረ ጨቋኞች ናቸው እያሉ መፍረዱ የጭንላትን ኢቮሉሽናዊ በሆነ መንገድ ለመዳበር እንደሚችል አለመረዳት ነው። ጭንቅላት ደግሞ ሊዳብርና የተደበቁ ልዩ ልዩ ጥሩ ባህርዮችን ሊጠቀምብቻው የሚችለው በጥሩ ወይም በትክክለኛ ዕውቀት የተኮተኮተ እንደሆነ ብቻ ነው። ይህንን በሚመለት በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ከፍተኛ የግንዛቤ እጦት ያለ ይመስለኛል። እንዲያው እያንዳንዱ አቢዮታዊ መፈክሮችን ይዞ ስለተነሳ፣ ወይም ዲሞክራሲ ዲሞክራሲ እያለ ሲጮህ ዕውነትም ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን የሚያሰፍን ይመስለኛል። አንድ ሰው ወይም ድርጅት ስልጣን ላይ በሚወጣበት ጊዜ እረውነተኛው ባህርይው ይታያል። ከዲሞክራሲ ይልቅ አፋኝ ይሆናል። ምሁራዊ ኃይል ሲዳብር፣ የምርት ኃይሎች ሲያድጉ የዚያን ጊዜ የሚከራከርና የሚጋፈጥ ሲኖር የገዢ መደቦችን መቆጣጠር ይቻላል።
    ስለሆነም በጊዜው የነበረውን የአገራችንን ሁኔታ በጠባቡ መመልከቱና አንድ ውሳኔ ላይ መድረሱ በሻብያ፣ በወያኔና በኦነግ ብቻ ላይ የሚሳበብ ሳይሆን የተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎችም ችግር ነበር። እነሱም ጥቂት መፈክሮችን በመያዝ፣ወይም እነዚያን እንደዋና ምክንያት በማድረግ ነው ወደ ትግል ውስጥ ሰተት ብለው የገቡት። ይህም ማለት ዛሬ ለሚታየው የአገራችን ምስቅልቅል ሁኔታና የጎሳን ጥያቄ አንስቶ እዚያው ላይ ሙጭጭ ብሎ መቅረት የተማሪው እንቅስቃሴም የራሱ የሆነ ትልቅ ድርሻ አለው። በሌላ አነጋገር፣ ዛሬ በአገራችን ምድር ለሚታየው ችግር ወያኔንና ኦነግን፣ ወይም ብልፅግናን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም። በእርግጥ እነዚህ ኃይሎች ጊዜ አመጣልን በማለትና የውጭ ኃይሎች መሳሪያ በመሆን የአገራችንን ሁኔታ የባሰውኑ ምስቅልቅሉን አውጥተውታል፣ በቀላሉም መፍትሄ እንዳይገኝለት አድርገዋል። ሻቢያና ወያኔ የሲአይኤ መጫወቻዎች የነበሩና የሚያደርጉትን የማያውቁ ነበሩ። በሲአይኤም ድጋፍ ነው እነ መለሰ ዜናዊ ስልጣን ላይ ሊወጡ የቻሉት። ሌሎችም ከጎሳ ፖለቲካ ነፃ የነበሩ አንዳንድ ሚኒስተሮች፣ ጄኔራሎችና ቢሮክራቶች የማያውቁትን ኮሙኒዝምን በመጥላትና የሲአይኤ መሳሪያ በመሆን የፖለቲካ ጥራት አንዳይኖር አድርገዋል። ኢድህም እንደዚሁ በሲአይኤ በመጠመድና መሳሪያ በመሀን ብዙ ነገሮችን ካመሰቃቀለ በኋላ ድምጥማጡ ጠፍቷል። አንዳንድ የማርክሲዝምን ሌኒንዝምን ስም የተከናነቡ መሪዎችም ዋናው ተልዕኮአቸው የርስ በርስ ጦርነት በመቀስቀስ አብዮቱን ማዳፈን ነበር። ይህም ተሳክቷል። ለዚህ ውለታቸውም አንዳንዶች በአውሮፕላን በመወሰድ አሜሪካ እንዲኖሩ ተደርገዋል። እነዚህ ሁሉ በመደመር ነው ደርግን አውሬ ያደረጉትና ቁጥራቸው የማይታወቁ ወጣቶችንና ምሁሮችን እንዲጨርስ ያስገደደው። ድርጊቱ ትክክል ነው ማለቴ አይደለም። በአጭሩ አርቆ አለማሰብ የሚያስከትለውን አደጋ ለማመልከት ብቻ ነው።
    ይህ ሁሉ ከሆነና ደርገም ከስልጣኑ እንዲባረር ከተደረገ በኋላ አገራችን የማንም መጨፈሪያ ማድረጉ ከባድ አይሆንም። አንድም ታዛዥ ኃይል ስልጣን ላይ አውጥቶ ትዕዛዝ ብቻ እንዲፈጽም ማድረጉ ቀላል ነው። ስለሆነም የወያኔ ስልጣን ላይ መውጣትና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አገልጋይ መሆን የታሪክ አጋጣሚ ሳይሆን ግዴታ ነበር። ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ የተከተለው ፖሊሲ የአገሪቱን አንድነት የሚያስጠብቅ፣ ህዝቡን የሚያስተሳስርና ቀስ በቀስም ከድህነት በማላቀቅ ጠንካራ አገር እንዳይገነባ ያደረገው የውጭ ኃይሎችን አጀንዳ ብቻ እንዲፈጽም በመደረጉ ነው።
    በጊዚው የጎሳ ፌዴራሊዝምም በአሜሪካና በተቀሩት የካፒታሊስት አገሮች ይደገፍ ነበር። አገሪቱን ለመከፋፈልና በሄራዊ ሰሜት እንዳይዳብር የሚያመች ስለነበር አጥብቀው ይደገፉ ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ ተግባራዊ የሆነው የኒዎ-ሊበራሊዚም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብሄራዊ ስሜት የሌለው የህብረተሰብ ክፍል ለማፍራት የሚያመች ነበር። አገሩን ሊሸጥ የሚችልና የብልግና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ የሚያደርግ የህብረተሰብ ክፍል ብቅ ሊል ችሏል።
    ሌላው በአብዮቱ ጊዜ የተሰራው ስህተት፣ ወይም ቶሎ ብሎ ስልጣን ለመውጣት ግብ ግብ መፍጠር የነቃና የበሰለ ምሁራዊ ኃይል ብቅ እንዳይል አደረገ። በጊዜው ሰፋ ያለ ጥናት ማካሄድና የበሰለ ምሁራዊ ኃይል ሊዳብር የሚችልበትን ሁኔታ ከማመቻቸት ይልቅ ከደርግ ጋር ጦርነት በመክፈት በጊዜው የነበረው ጥቂት የተማረ ኃይል እንዲገደል ወይም እንዲሰዋ ተደረገ። ይህ ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ክፍተትን ፈጠረ። ሻቢያን፣ ህውሃትንና ኦነግን አጠናከራቸው። ኢትዮጵያን ለመቀራመት ዕድል አጋጠማቸው። የአገራችንና የዓለምን ሁኔታ በምሁራዊ መነፅር ከመመርመርና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ትግል ከማካሄድ ይልቅ የጦር ትግልን አማራጭ እንደሌለው አድርገው በመውሰድ መንፈሳቸውን አጨለሙ፤ በዚያውም ጥላቻን አባባሱት። ለተከታታዩ ትውልድም ማስተላለፍ ቻሉ።
    ይህ ዐይነቱ ነገሮችን በጠባብ የመመልከቱ ጉዳይ ለአንድ ኢትዮጵያ እታገላለሁ የሚለውንም የሚመለከት ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ አብዮቱ ከፈነዳና ከተጨናገፈ ከ50 ዓመት በኋላ እንደመመሪያ የሚሆነን ርዕይ ወይም ሳይንሳዊ የመመርመሪያና ችግሮችን የመፍቺያ ዘዴ ማዳበር በፍጹም አልቻልንም። ያንኑ ያንኑ እየደጋገምን ከመነዛነዝ በስተቀር መንፈሳችንን ሰብሰብ የሚያደርግ ቲዎሪ ማዳበር አልቻልንም። እንደሚታወቀው የአንድ አገር ችግር በመጀመሪያ ደረጃ በቲዎሪ ነው መብላላት ያለበት። ነገሮች ከሁሉም አኳያ ከተመረመሩ በኋላ ነው መፍትሄ ማግኘት የሚቻለው።
    ለማንኛውም እነ አቢይም የዚህ የምሁረ አልባና በዲሞክራሲያዊ መርሆች ላይ ያልተገነባ ህብረተሰብ ውጤቶች ናቸው። ያለፈውን የስድስት ዓመት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰንመለከት በደመ-ነፍስ የሚመራ ነው። በኦሮሞ ብሔረሰብ ሽፋን ስር በግሎባል ካፒታሊዝም ቁጥጥር ስር ያለና የእሱን አጀንዳ የሚፈጽም ፋሽሽታዊ አገዛዝ ነው በኢትዮጵያ ምድር የሰፈነው። መገለጫውም ጦርነትን ማካሄድና ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ በእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት የሚደገፍና ሰፊውን ህዝብ ደሃና አቅመ-ቢስ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው። ባጭሩ ብሔራዊ ኢኮኖሚ ሊያስገነባ የሚችል አይደለም።
    ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ዛሬ በአገራችን ምድር ያለው አገዛዝ እንደመንግስት የሚቆጠር አይደለም። የመንግስትነትን ባህርይና ዋና ተግባር ሊያሟላ የሚችል አይደለም። አንድ መንግስት መንግስት ነው የሚያስብለው የጠቅላላው ህዝብ አለኝታ የሆነ እነደሆን ብቻ ነው። አገሪቱም በተሟላ መልክ እንድትገነባና የሰፊው ሀዝብም የውስጠ-ኃይል እንዲጠነክርና ፈጣሪም እንዲሆን ሳይንሳዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፓሊሲ ተግባራዊ የሚያደርግ ከሆነ እንደዚህ ዐይነቱ ኃይል እንደ መንግስት ወይም አገዛዝ ሊቆጠር ይችላል። በተጨማሪም በውጭ ኃይል የሚጠመዘዝ ከሆነ በፍጹም የህዝብ ተጠሪ ሊሆን አይችልም።ምክንያቱም የአንድ መንግስት ወይም አገዛዝ ሌላው ተግባሩ ብሄራዊ ነፃነትን ማስከበር ስለሆነ። በአቢይ አህመድ የሚመራው አገዛዝ እነዚህንና ሌሎች መሰፍርቶችን ሊያሟላ ስለማይቸልና ለአገራችንና ለጠቅላላው ጥቁር አፍሪካ አደጋ የጣለና የሚጥልም ስለሆነ ፀረ ስልጣኔና ፀረ ዲሞክራሲ የሆነ ኃይል ነው። በማያወላግድ መልክ መወገድ ያለበት ነው።
    ይህንን ካልኩኝ በኋላ ሰሞኑን የተከሰተው ሁኔታ የሚጠበቅ ነበር። ከሰማይ ዱብ ያለ አይደለም። እስክንድር ነጋ ቀኝ የሆነና የአምባገነንነትም ስሜት ያለው ነው። መንፈሱ በዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የተገነባ አይደለም። ለኢትዮጵያ ህዝብ የቆመ ቢመስልም የሚሰራው ለአሜሪካን ነው። ይህ ነገር በጭንቅላት ውስጥ መቋጠር ያለበት ጉዳይ ነው። ሌሎችም ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያሉ የዋሁን ወጣት የሚያሳስቱም ቁጥራቸው ትንሽ ነው አይባልም። እስክንድርና እነዚህ ኃይሎች በሙሉ የጠራ አቋም የላቸውም። የአገራችንንም የተወሳሰቡ ጭግሮች እንዴት ደረጃ በደረጃ መፍታት እንደሚችሉ እስካሁን በጽሁፍ መልክ በፍጹም አላሳዩንም። ባጭሩ ዝም ብለው እያታለሉንና እያደነባበሩን ነው።
    ይህንን ካልኩኝ በኋላ አንተ ፋኖዎች የሚያደርገትን የህልውና ትግል ዕውቅና አለመስጠትህ በጣም ያሳዝናል። በእኔ ዕምነት ፋኖዎች የሚያደርጉት የህልውና ትግል መደገፍ ያለበት ነው። ፖለቲካዊ መልክም እንዲይዝ በሳይንስ ላይ የተደገፈ ምክር መስጠት ያስፈልጋል። ስለሆነም ስንጽፍ በጣም ጠንቀቅ ማለት አለብን። የነገሮችን ሂደት በሚገባ ማውጣትና ማውረድ አለብን። ህዝባዊ ባህርይ ያለውንና አገር ወዳድ የሆነውን ከሌለውና ካለው መለየት ያስፈልጋል።። ለዚህ ደግሞ መለኪያ አለ። ስለሆነም የአቢይን አገዛዝና ፋኖዎችን በተለያየ መነፅር ማየቱ በጣም አስፈላጊ ነው። በሌላ ወገን በሁላችንም ዘንድ ያለ ችግር በእነሱም ዘንድ አለ። ይሁንና መረዳት ያለብን ነገር እነሰኡ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ነው የሚታገሉት። የእኛ ተግባርም መሆን ያለበት ባለን ሙያ ወይም በተማርነው ትምህርት ጠለቅ አድርገን በማጥናት የአገራችንን ችግሮች በመመርመር መፍትሄዎችም ለማቅረብ መጣር አለብን። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ታሪካዊ ኃላፊነታችችንን ልንወጣ የምንችለው። በተረፈ ለትችቱ አመሰግናለሁ።

    ፈቃዱ በቀለ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

በወቅታዊ ጉዳይ ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ መግለጫ

Next Story

የአማራ ሕዝባዊ ድርጅት ያደረገው ውይይት ወይስ ድርድር?

Latest from Same Tags

የአማራና የኦሮሙማ ድርድር – በሣቅ አትግደሉን!

ይነጋል በላቸው “አማራ በድርድር የሚፈታ ችግር አልገጠመውም” በሚል ርዕስ በፈረንጆቹ አቆጣጠር Sept. 16, 2023 የሚከተለውን መጣጥፍ ጽፌ እንቅልፍ ሳይበግራቸው፣ ድካም ወፃማ ሳይፈታቸው ለሀገራቸው ትንሣኤ

ኳሷ ያላችው እስክንድር ነጋ ጋር ነው – ግርማ ካሳ

እስክንድር ነጋ በኢትዮ360 ቀርበ ነበር፡፡ ማስታወቂያውን አስቀድሞ ስለሰማሁ ቃለ ምልልሱን አደመጥኩት፡፡ እንደሚታወቀው፣ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ አንድነት ድርጅት የሚባለውን መቋቋምና፣ የድርጅቱ መሪ እስክንድር ነጋ መሆኑን
Go toTop

Don't Miss