ጎበዜ ሲሳይ በያዝነው በነሐሴ ወር በቆቦ አካባቢ ስለነበረው ሁኔታ የተናገረው ሃቅ ጉዱ የተጋለጠውን የብልጽግና ካድሬ መንጋ እያጥውለወለው ሰንብቷል። ጉዳዩን ከማስተካከል ይልቅ ለምን ተነገረ ብሎ እምቧ ከረዩ ማለት ለውድቀት የሚዳርግ አባዜ ነው። እሱ የተናገረው እስኪ ምን አዲስ ነገር አለው? መረጃውን ሚዲያዎችና መንግሥት ሲያፍኑት ስለከረሙ እንጂ አምናስ በዚሁ መንገድ አልነበር የጦርነቱ አስቀያሚ ገጽታ የነጎደው? ሁሉም የሚያውቀው ነው። ሁሉም ስል ከብልጽግና መንግሥታዊ ጡሩምባ ሌላ የመረጃ ምንጭ ለመስማት የሚፈልግ ሰው ሁሉ ማለቴ ነው።
እኔ ራሴ ያነጋገርኳቸው ከመንዝ የተወሰዱ ሚሊሻዎች ትግራይ ድንበር ላይ ከተዘረገፉ በኋላ ድጋፍ ይቅርና ምእራብና ምሥራቅ ሰሜንና ደቡቡን ሳይነግሯቸው ለሕወሃት ከበባ ጥለዋቸው ጠፍተዋል። የጓደኛዬ አጎቶች ካንድ ቤት ሦስት ዘምተው ሁለቱ እለቱን ሲማረኩ አንደኛው በቀንና በጨለማ እግሩ ወዳመራው ደንብሮ ያለ እህል ውሃ ከሳምንት በላይ ተጉዞ የኤርትራ ሠራዊት እጅ ወድቋል። ለቤተሰቦቹም በኤርትራ ሲም ካርድ ደውሎ ደህንነቱን አስረድቷል። በሌላ በኩል እልፍ የጎጃም ሚሊሺያ ባዶ እጁን ያለ አንዳች ትጥቅ እንዲህ በካድሬ ተከዜ ድንበር ላይ ተዘርግፎ በካባድ መሣሪያ ዱቄት መደረጉን ከነቪዲዮው እነዘመድኩን ለቅቀውት እንደነበር ማንም አይዘነጋውም። ለብዙ ሰው የሚደንቀው ነገር እነዚህ አመራሮች በሰው ሕይወት እንዲህ ከቀለዱ በኋላ እነሱ በሕይወት ጭራሽም በሥልጣን መቀጠላቸው ነው።
እና ምኑ ነው አዲሱ ነገር?
አዲሱ ነገር ልዩ ኃይሉን ያለ በቂ የአመራር ቅንብር ውጊያ ቀጠና ውስጥ መዘርገፉ፣ ሳይነግሩና ሳይቀናብሩትም ጥለውት መሸሻቸው ይሆን? ይህስ ቢሆን ከሕወሃት ጋር በተደረገ ውጊያ ላይ አልሰማን ይሆናል እንጂ በከሚሴና ሸዋ ከኦነግ ፒፒ ጋር በተደረጉ አውደ ውጊያዎች ተደጋግሞ የተፈጸመና እጅግ ብዙ የአማራ ልዩ ኃይል የረገፈበት እጅግ የተደጋገመ የክህደት አይሉት የቅሽምና ከባድ ወንጀል አይደለምን? እና ጎበዜን ለቀቅ፣ እምነታችሁን፣ አመራራችሁን ጠበቅ ማድረጉ ይሻላል። ሴራውን እንደሆነ የወሎ ሕዝብ ጎበዜ ሳይነግረው ተክዶ፣ ተዋርዶ፣ ተዘርፎ፣ ቆስሎና ሞቶ በተግባር ደርሶበት ነጋሪ ሳይፈልግ ያውቀዋል። የጣማችሁን ሥልጣን ማስቀጠል ከፈለጋችሁ ሴራውን ትቶ ከምር መታገል። ባርያ በራሷ ወፍጮ መጅ ትደብቃለች ይባላል። አሁን የባርያ አመል እንጂ የአቢይ አህመድና የኦህዴድን ሥልጣን ለማስጠበቅ ደሜን ላፍስስ ብሎ በዘመተ ሰው ላይ ደባ መሥራት፣ ስንቅ፣ ጥይትና ተተኳሽ መከልከል፣ እያፈገፈጉ ማስፈትጀት ምን የሚሉት ጅል፣ ጅላጅል፣ ጅላንፎነት ነው?
NEILOSS –Amber