ቤተ ክርስቲያንን በመከፋፈል ትርፍ ማግኘት አይቻልም- ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም መግለጫ

July 27, 2022

የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የኒዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም መግለጫ ሰጡ።

ሐዋ. ፳፫፥፭ “በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ ቃል አትናገር” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል መነሻ በማድረግ መግለጫውን የጀመሩት ብፁዕ አቡነ አብርሃም በአንድ ቅዱስ ፓትርያርክ ላይ በጥራዝ ነጠቅነት የተሳሳተ መረጃ መስጠት ትክክል አለመሆኑን በመጥቀስ ቅዱስነታቸው ቤተ ክርስቲያን ይወክላሉ። እሳቸው ባሉበት ኹሉ ቤተ ክርስቲያን አለች። እሳቸውን የሚናገር እየተደፋፈረ ያለው ቤተ ክርስቲያንን ነው። በዚህም ቤተ ክርስቲያን ታዝናለች” ብለዋል።
በሀገር ውስጥና በውጭ ላለችው ቤተ ክርስቲያን አባት የሆኑ አባትን በዚህ መንገድ መናገር ሉዋላዊ የሆነች የኢ/ኦ/ቤ/ክንን እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምእመናንን መድፈር ነው ያሉት ብፁዕነታቸው
ቤተ ክርስቲያንን በመከፋፈል ትርፍ ማግኘት አይቻልም ሲሉ አብራርተዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም ቤተ ክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናትን በውጪ ሀገር መትከል ከጀመረች ጀምሮ ጽላት በአሰራሯ መሰረት ትልካለች።
የታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት እና ልጆቿ በረሃብ እየተገረፉ የጠበቁትን ሁኖ ሳለ ቤተ ክርስቲያን ቅርስ ታሸሻለች ብሎ ማሰብ ንስሐ ያስገባል።
ይህ የቅዱስነታቸውን ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንን ክብር መንካት ነው ብለዋል።
መንግሥት ለምን ብሎ መጠየቅ እና መመርመሩ ተገቢ ነው። ነገር ግን ቅርጽና ቅርስ መለየት ያስፈልጋል። በቀጣይም በጉዳዮ ላይ ግልፅነት ለመፍጠር ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በቀጣይ እንወያያለን በማለት በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
ዜናው የማህበረ ቅዱሳን ነው

 


 


የቤተ ክርስቲያኗ ፓትርያርክ ልዩ ፅህፈት ቤት ለሃይማኖታዊ ስርዓት የሚውሉ ቅርሶችን ከአገር ይዞ ለመውጣት የተከተለው አካሄድ የአሰራር ስርአትን ያልተከተለ ነው -የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን

ሐምሌ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ልዩ ፅህፈት ቤት ለሃይማኖታዊ ስርዓት የሚውሉ ቅርሶችን ከአገር ይዞ ለመውጣት የተከተለው አካሄድ የአሰራር ስርአትን ያልተከተለ መሆኑን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

በቅርስነት የተመዘገቡም ያልተመዘገቡም ቁሶች ከአገር መውጣት የሚችሉት የባለስልጣኑን ማረጋገጫ ሲያገኙ ብቻ መሆኑንም ባለስልጣኑ ጠቁሟል።

ሰሞኑን የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ማቲያስ ከኢትዮጵያ ውጪ መሔዳቸው ይታወቃል።

ይህንን ተከትሎም የፓትርያርክ ልዩ ፅህፈት ቤት ሃይማኖታዊ ስርዓት የሚካሔድባቸውን መገልገያዎችን ከአሰራር ስርአት ውጭ ከአገር እንዲወጡ ለማድረግ ሞክሯል በሚል በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወር እንደነበርም እንዲሁ።

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በጉዳዩ ዙሪያ ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ ቅርሶች በአገር ሃብትነት የተመዘገቡ በመሆናቸው ልዩ ጥንቃቄና ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

ቅርሶች በመንግስት፣በተቋማትና በግለሰብ እጅ ሊኖሩ እንደሚችሉ ገልጸው ባሉበት ቦታ ግን ልዩ ጥበቃ ማድረግ የግድ የሚያስፈልግ ሲሆን ከሀገር ውጭ ለማንቀሳቀስ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ።

በሀገሪቱ ያሉ ሐይማኖታዊም ሆነ ሌሎች ቅርሶችና በቅርስነት ያልተመዘገቡ ቁሶች በተለያዩ ምክኒያቶች ከአገር ሊወጡ የሚችሉበት አግባብ እንዳለም ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

ለአብነትም፣ለምርምር፣ለኤግዝቢሽንና ባዛር ለኪነ-ጥበብ ስራዎች እንዲሁም ለባህል ልውውጥ ከአገር ውጭ እንዲወጡ ይፈቀዳል።

ይሁን እንጂ በቅርስነት የተመዘገቡም ያልተመዘገቡም ቁሳቁሶች ከአገር ከመውጣታቸው በፊት በአገሪቱ ሕግ አግባብ ሊወጡ እንደሚገባም አብራርተዋል።

ቅርሶቹን ይዞ የሚንቀሳቀስ የትኛውም አካል ወይንም ተቋም በቅድሚያ ለቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን ፍቃድ መጠየቅ ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

በህጉ መሰረትም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የቅርሱን የቆይታ ግዜ፣ የሚሄድበት ምክኒያትና ሁኔታ እንዲሁም ዝርዝር ጉዳዮችን ካጤነ በኋላ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የፍቃድ ደብዳቤን የሚጽፍ ይሆናል።

በቀጣይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለጉምሩክ መስሪያ ቤት ካስተላለፈው በኋላም የአሰራር ስርአትን ከተከተለ በኋላም ቅርሱ በአግባቡ ተጠብቆና ተከልሎ እንዲጓጓዝ ይደረጋል ነው ያሉት።

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ በእምነቱ ዘንድ ትልቅ ስፍራ ከሚሰጣቸው መካከል ታቦትን ጨምሮ ሌሎች ሐይማኖታዊ ቅርሶችን ወደ አሜሪካ ለማድረስ ሂደት ላይ የተፈጠረው አለመግባባት የአካሄድ ስህተት እንደገጠመ ነው ያብራሩት።

በዋናነትም ሰሞኑን የቤተክርስቲያኗ ቅርሶችን ወደ ሌሎች አገራት በማንቀሳቀስ ሒደት ውስጥ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ፍቃድ ባለመጠየቁ የተፈጠረ ክፍተት መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እውቅና ውጪ ቤተ-ክህነት በቀጥታ ለጉምሩክ ባለስልጣን የፍቃድ ደብዳቤ መላኩ አግባብ ባለመሆኑ ጉምሩክ ላይ የተፈጠረ አለመግባባት ነው ብለዋል።

ህጋዊ ስርአቱን ባልተከተለ መንገድ ከአገር ሊወጡ የነበሩ ቅርሶችና ቁሳቁሶች በቤተክርስቲያኗ ሰዎች ወደ ቤተክህነት እንዲመለሱ መደረጉ ተገልጿል።

ኢዜአ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

አብይና መግለጫው – አብይና ተግባር

Next Story

ከሀገር ውጭ ለሚገኙ መቅደሶቻችን ታቦታትና ንዋያተ ቅድሳት ይዞ ለመሔድ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን የመጀመሪያውም ብቸኛውም አባት አይደሉም

Go toTop