(ዘ-ሐበሻ) በደቡብ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ክልል ይኖሩ የነበሩ የአማራ ተወላጅ ኢትዮጵያውያንን ካለካሳና በማናለብኝነት እየተደረገ ያለውን የማባረር ድርጊት በመቃወም ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ።
ከጠዋቱ በ9 ሰዓት የተጠራውና በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ መኖሪያ ቤት ኋይት ሀውስ ፊት ለፊት በተደረገው በዚህ ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ወትሮ ከሚደረጉት ሰላማዊ ሰልፎች ቁጥሩ በዛ ያለ ኢትዮጵያውያን መገኘታቸውን የዘ-ሐበሻ የዲሲ ዘጋቢ ተናግሩዋል።
እንደዘ-ሐበሻ ዘጋቢ ከሆነ በአማሮቹ ላይ የሚደረገውን መፈናቀል ለመቃወም በጠዋቱ ወደ ኋይት ሐውስ ያመሩት ሰልፈኞች የኢትዮጵያ መንግስትን ድርጊት በመቃወም የተለያዩ መፈክሮችን ያሰሙ ሲሆን የኦባማ አስተዳደርም በጉዳዩ ላይ ትኩረት እንዲያደርግበት ጠይቀዋል።
የወያኔ መንግስት በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጽመውን ግፍ እንዲያቆም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የጠየቁት እነዚሁ ኢትዮጵያውያን ሰልፈኞች አማሮቹ ከቤኒሻንጉል ጉምዝም ሆነ ከደቡብ ክልል ንብረታቸውን ጥለው ሲባረሩ የተፈጸመባቸውን ድብደባና ግፍ አውግዘዋል።
የሰልፉን ሁኔታ የሚያሳይ አጭር ቪድዮ ይመልከቱ።
ከዚህ ቀደም በጀርመንም ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ መደረጉ አይዘነጋም።