“ ቀጠለ…ወደ እሳቱ” – ጌታቸው አበራ

June 9, 2022

እንደ እሳት እራቷ – እንደ ቢራቢሮ፣
ብር… ትር… እያለ – ክንፎቹን ሰትሮ፣
ሙቀቱን ሳይለካ – ትርፍና ኪሳራ፣
ብርሃኑ መስሎት – መንገድ እሚመራ፣
እሚቋቋም መስሎት – በሰላ አንደበቱ፣
የመቅለጡን ጉዞ – ቀጠለ ወደ እሳቱ!

፩. ቁጭ ብሎ አሸልቦት- ላይ-ታቹን ሳያማትር፣
ከጊቢው የተነሳው – ከወንበሩ እግር ስር፣
ባውሎ-ነፋስ ፍጥነት-አገር ያዳረሰው፣
ሰደድ-እሳት ደርሶ-ድንገት ያስወገደው፡

፪.ቁርጥ ቀን ሲመጣ – ድንገት ተፈናጥሮ፣
ያመለጠ መስሎት – ባየር ተወርውሮ፣
ከህሊናው ርቆ ሊያመልጥ ሳይሳነው፣
በጸጸት ልዩ እሳት…፣
ባገር ናፍቆት ነዲድ ሲቆላ እሚኖረው፤

፫.ሕዝባዊ ማዕበል – ወላፈን ለብልቦት፣
የእሳቱን ጣጣ – መሸከም ተስኖት፣
ሸሩን የቀመረው – ተንኮሉን ያደራው፣
አንጎሉ ፈንድቶ – የተሰናበተው፤

፬.ሙቀት ሲያይልበት – እሳቱ ሳይበላው፣
“በየሱስ ስም!” ብሎ- ሮጦ ያመለጠው፤

… ቢያንስ በእኛ ዕድሜ – ያየናቸው “አራቱ”፣
ዞረው፣… ዞረው፣…ዞረው፣… ሲገቡ ከእሳቱ፣
እንዴት እንዳልሰማ፣ እንዴት እንዳላየ ‘እንደተበለቱ’፣
እኔስ ግራ-ገባኝ፣ እንጃኝ! “እንጃ-አባቱ”!

ተው ቢሉት እሚያውቁ – እሳቱ የታያቸው፣
እምቢኝ ብሎ ሄደ – ጎሪጥ እያያቸው፣
የእርሱስ መጨረሻ – ክዋኔው ናፈቀኝ፣
እንዳህያው ሥጋ..
አልጋ ሲሉት መደብ- መረጠ መሰለኝ፤
“ያላወቁ አለቁ”- ነበረ ተረቱ፣
እያወቁ ማለቅ- ጉዞ ወደ እሳቱ!

ጌታቸው አበራ
ሰኔ 2014 ዓ/ም
(ጁን 2022)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የኦህዴድ ብልፅግና ተረኝነት እና የ2015 የበጀት ምደባ

Next Story

“ሰሞኑን በጎንደር ማክሰኝት ከተማ በመንግስት ታጣቂዎች በንፁሃን ላይ የተወሰደው የከባድ መሳሪያ እርምጃ ለእኔ መንግስታዊ ሽብር ነው” ሲሉ የአማራ ፋኖ አንድነት በጎንደር ሰብሳቢ ሻለቃ ሰፈር መለስ

Go toTop