የአማራ ህዝብ በተናጠልም ይሁን በቡድን ያሳለፋቸዉን የትግል ሂደቶች መልሶ መገምገም ይኖርበታል
ከዚህ አንፃር የማታገያ አደረጃጀቶቻችን (ድርጅቶች) ለህዝባችን የፈጠሩለትን ተስፋ እና ስጋት፣ የትግሉን ደካማ እና ጠንካራ ጎን በመለዬት አዋጭ የሆነዉን የትግል ስልት መልሶ መንደፍ አለበት፡፡
በመሰረታዊነት የአማራ ህዝብ የትግል አቅጣጫዎችና በዚህም የሚነሱ፣ የተነሱ፣ የሚመለሱ፣ የተመለሱ እና በሂደት ላይ ያሉ ጥያቄዎችን ከግምት ዉስጥ በማስገባት እና ቅደምተከተላዊ ስርአት በማበጀት የገጠመውን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተና በብልሃት ማለፍ ይኖርበታል፡፡
የቀደምት አባቶቻችን ለሺ ዘመናት አሸናፊ የነበሩት በኢትዮጵያ አንድነት እና አብሮነት ፍልስፍና ተመርተዉ ነዉ፡፡ ነገርግን ይህንን የአባቶቹን የአሸናፊነት እና የአንድነት ታሪክ ዛሬ ላይ ለገጠመው ውስጣዊና ውጫዊ ፈተና እንደ መዉጫ ስንቅ፣ እንደመሻገሪያ ድልድይ፣ እንደማሸነፊያ ብልሃት አድርገን ባለመጠቀማችን ህዝባችንን በተለያየ መንገድ ለችግር ዳርገነዋል፡፡
ጣሊያናዊዉ ፕሮፌሰር ሰባስኪ የጣሊያንን ጥናታዊ ሰነድ መርምሮ እንዳስቀመጠዉም “አማራዉ ጀግና ከሆነ ፍጹም ጀግና እና ማንም ከፊቱ የማይቆም ሀያል ነዉ:: ባንዳ ከሆነም ፍጹም ባንዳ ነዉ የሚሆነዉ” እንዳለዉ የትግሉ አሻጋሪ ሃቀኛ ጀግኖችን ለይተን ከፊት ባለማስቀደማችን እና የትግሉን ጠላፊዎችን ደግሞ መንጥረን ባለማረማችን ትግላችን መርህ አልባ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በዚህም ከአንድ ሁለት ሶስት ጊዜ ያህል ቅስማችን ተሰብሯል፡፡ የአዙሪታችን መጠንም ይሰፋ ዘንድ እንደተገደድንም ጭምር፡፡
ከዚህ አንፃር የአማራ ህዝብ አደረጃጀቶችን በተመለከተ በዙሪያዉ ያሉ፣ የአማራን ህዝብ እንደ ጠላት የማይመለከቱ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ ዘዉጌዎች አብረዉት ባይደራጁ እንኳን በተሳሳተ ትርክት ተሳስተው በጠላትነት እንዳይመለከቱት የሚያስችል ሁኔታን ግንዛቤ ዉስጥ ያስገባ እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባል፡፡
ከአማራ ክልል ዉጭ ያለዉ የአማራ ህዝብ በአሰፋፈሩ፣ በጋብቻዉ እና በነበረዉ ስነ-ልቦናዊ እሴቱ የተነሳ ከሌሎች ዘዉጌዎች ጋር በቀጥታ የሚነጥለዉን አስተሳሰብ ከማራመድ መቆጠብ ይገባል፡፡ በተለይ ከአማራ ክልል ዉጭ ያለዉ አማራ የተማረዉ፣ ሀብት የፈጠረ በሚኖርባቸዉ አካባቢዎችና ማህበረሰብ ዘንድ አጠቃላይ ቅቡልነት ያተረፈ ህዝብ ነዉ።
ይሄ ህዝብ ራሱንም ኢትዮጵያንም ለማዳን በአማራ ክልል ከሚኖረዉ የአማራ ማህበረሰብ እኩል ጉልበት፣ አቅም እና ፍላጎት ያለዉ ህዝብ መሆኑን ማመን ይገባል፡፡
እንደ አጠቃላይ የአማራ ህዝብ ከሌሎቹ ወንድም ህዝቦች ጋር ያለውን ጠንካራ ግንኙነት የበለጠ ከማጠናከር በዘለለ ልዩነትን እና ጥርጣሬን የሚሰብኩ ጦማሮችም ይሁኑ ይህንን ከሚያጠናክሩ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መጠንቀቅ፣ መራቅና መቆጠብ እጅጉን ያስፈልጋል። እያንዳንዱ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሁሉ በዚህ ሀገር ላይ የሚኖረውን አዎንታዊና አሉታዊ ጎኖች ቀድሞ የሚመዝን የተፅእኖዎችን ትርፍና ከኪሳራ የሚያሰላ ሊሆን ይገባል።
በዚህም ኢትዮጵያዉያን በጋራ ተስማምተው ሊታገሉ ከሆነ የሚታገሏቸው ፀረ ኢትዮጵያዊያንን እና ፀረ አብሮነትን ሊሆን ይገባል።
“የአማራና የኦሮሞን ህዝብ ጠንካራ ግንኙነት በመነጠል ኢትዮጵያን ማዳከም ይቻላል” ብለው ለሚያምኑና ለዚህም ለሚቆምሩ ፀረ ኢትዮጵያ ሀይሎች የአማራ ህዝብ ችግር ለኦሮሞው ህመሙ፤ የኦሮሞ ህዝብ ችግር ለአማራው ህመሙ ሆኖ ውስጡ ድረስ ዘልቆ የሚሰማው መሆኑንና በማንም በየትም አይነት ተፅእኖ ከኖረበት የጋራ እና ጠንካራ መስተጋብር የሚነጥላቸው አንዳች ሀይል አለመኖሩን በሚገባ ማሳየት አለብን።
በተለይም በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች የሚኖሩ ልሂቃኖች፣ የሚዲያ ባለሞያዎች እና ጦማሪያን ይህንን ፖለቲካዊ ግቡቡነት በመፍጠር ረገድ ጉልህ ድርሻ ሊጫወቱ ይገባል።
‹‹ሀገር እንዲኖራቸዉ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዉን ከአማራ ህዝብ ጋር ይሰለፉ ዘንድ የትግል አካሄዳችንን እንፈትሽ!››
በየሺዋስ አንበርብር