አትሰቀል ይቅር !! እና ተጠየቅ ልጠየቅ !! (አሥራደው ከፈረንሳይ)

April 21, 2022

በገባለት ቃሉ – አባትህ ለእኛ አባት፤
አንተ ለኛ ሞተህ – ልንድን ከሃጢያት፤
እኛን አድናለሁ – ብለህ ከመከራ፤
መስቀል ተሸክመህ – አትውጣ ተራራ::

በጨካኞች ጅራፍ – አይገረፍ ጀርባህ፤
ምስማር አይቸንከር – በጅና በግሮችህ፤
በጦር አይወጋ – አይበሳ ጎንህ፤
አትጠጣ ፍጹም – የሃሞት መራራ፤
አድናለሁ ብለህ – እኛን ከመከራ፤
መከራህ አይብዛ – መከራችን ላይቀር፤
ተንገላተህ አትሙት – አትሰቀል! ይቅር::

ተከባብሮ መኖር – አብሮ መብላት ቀርቶ፤
ጥላቻ፤ ጭካኔ – መከራ በርክቶ፤
ወንድማማችነት – ፍቅር መተባበር፤
አንድነት፤ ነፃነት – ፍጹም ጠፍተው ካገር፤
መቻቻል፤ ደግነት- ከሃገር ተሰደው፤
ግፍ በደል በርክቶ – ሞልቶ ፈሶ ጽዋው፤
ሰው ሆነን ሰው ካልሆን – ተፈጥረን ባምሳልህ፤
ከሰማየ ሰማይ – ወርደህ ከዙፋንህ፤
አፈር ለባሽ ገላ – ከንቱ ሥጋ ለብሰህ፤
አትሰቀል በቃ! – እኛን ላድን ብለህ ::

ይልቅስ ከሰሙህ_ እንዲህ ምከራቸው………!
እንደዚህ በላቸው_ ስልጣን ላዋስካቸው…. !
ስልጣን ተገን አርጎ – ቀምቶ የበላ፤
ለሥጋው አድልቶ – ወገኑን ያጉላላ፤
ዘረኝነት አርሶ – ቂም በቀል የዘራ፤
የሚያበዛ ትዕቢት – ሰው የሚያስፈራራ፤

ውሸት ያመረተ – በደል የከመረ፤
በግፍ የገደለ – ወህኒ ቤት ያጎረ፤
ጥላቻን አንግሶ – ፍቅርን ያኮሰሰ፤
ወንድሙን የገፋ – በደል ያነገሰ፤
ቁጣዬን አብዝቶ – መከራውን ያጭዳል፤
ሕዝቤን አታጉላሉ – ከንግዲህ ይበቃል !
ብለህ ንገራቸው………!
ስልጣን ላዋስካቸው……… !
ልቦና ቢገዙ_ ድንገት ቢመለሱ_ ወደ ሕሊናቸው ::

ግን !
የሕዝብህን ጩኸት – እየሰማ ጆሮህ፤
ስቃይ መከራውን – እያየኸው ባ’ይንህ
ሲካድ ሰብዕናው – ፈጥረኸው ባምሳልህ፤
ዝምታህ ከበዛ – ከዘገየ ፍርድህ፤
ኤሎሄ ! ኤሎሄ ! ላማ ሰበቅታኒ – ላ’ባትህ ልናገር፤
ቁም ስቅልህ ይብቃ!_ እኛ አልዳንምና – አትሰቀል ይቅር!!
ተጠየቅ ልጠየቅ !
( አሥራደው ከፈረንሳይ )

« በአገር በሃይማኖት፤ በሚስት የለም ዋዛ !
በአሞሌ አይለወጥ፤ በአራጣ አይገዛ !! »
ብሎ የዘመተው ፤
በአድዋ በማይጨው ፤
ለአገር ለነፃነት ሕይወቱን የሰዋው ፤
ለኛ ሲል የሞተው ፤

ድንበር ያስከበረ – ባጥንቱ ቸንክሮ ፤
ባ’ንድነት ያሰረ – በጅማቱ አክርሮ ፤
ቆዳው ተፈቅፍቆ – ብራና ተሌጦ ፤
ታሪኩ የተጣፈ – በደም ተበጥብጦ ፤
ሰንደቅ የሰቀለው – ባጥንቱ ሰክቶ፤
በሥጋ ወ ደሙ – በቃል ኪዳን ጠንቶ ፤
ለሰጠን አደራ – ለቃል ኪዳናችን ፤
ዛሬ ቢጠይቀን፤
ምንድነው መልሳችን ?!

በአሞሌ ለሸጥነው – ለነፃነታችን ፤
ለተቸበቸበው – ለባዕድ መሬታችን ፤
ለተሸራረፈው – ያገር ድንበራችን ፤
ለተሸረሸረው – ጥኑው ዕምነታቸን ፤
ለ’ኛ ሲል የሞተው ፤
በአድዋ በማይጨው ፤
ዛሬ ቢጠይቀን ፤
ምንድነው መልሳችን ?!
ለቃል ኪዳናችን – መፍረስ ወይ መጠበቅ ፤
መልሳችን ምንድነው ?_ ተጠየቅ ልጠየቅ ?!

ቢጠይቅ ታሪኩን ፤
ቢያነሳ አደራውን ፤
በደም የተጣፈ – ያ’ባት ኑዛዜውን ፤
ምንድነው መልሳችን ?!
ለሰጡን አደራ – ማረጋገጫችን ፤
ለ’ኛነት መግለጫ – የ’ኛነት ቃላችን ?!
ለቃል ኪዳናችን – መፍረስ ወይ መጠበቅ ፤
መልሳችን ምንድነው ?_  ተጠየቅ ልጠየቅ ?!

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የፋኖ ሦስተኛ ተገዳዳሪ ኃይል ሆኖ መውጣት፣ ለመላ ኢትዮጵያ አንድነት ኃይሎች ታላቅ የምሥራች ነው

Next Story

በአርባ ምንጭ የባልደራስ አመራሮች እገታን በተመለከተ የፓርቲው ድርጅታዊ መግለጫ

Go toTop