የጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ መልዕክት ከሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት

ግፍ ከበዛበት ወህኒ የአክብሮት ስላምታየ ይድረሳችሁ!

እነሆ ለሁለተኛ ጊዜ ለአፍታ ያህል እድሉን አግኝቸ ወህኒ የመውረዴን እውነታ ላስረዳችሁ ግድ አለኝ ። ዛሬ አስረግጨ የምነግራችሁ ወህኒ የመውረዴ ምክንያት ሚስጥር ግምሽ እድሜየን ህግና ስርአቷን አክበሬ የኖርኩባትን የሳውዲት አረቢያን ህግ ተላልፊ አይደለም ! የስደተኛው ጉዳይ ያገባኛል በሚል የማቀርበው መረጃ ቅበላየ የማይመቻቸው ፣ ያመማቸው ከተሰረሰውና እየተሰራ ካለው ከእገታው ጀርባ ስለመኖራቸው አልጠራጠርም ። … ዛሬ በዚህ ዙሪያ ብዙ አልልም!

አላወቁትም እንጅ ክፉዎች ጠቅመውኛል ፣ ያላየሁትን እንዳይ አድርገውኛል። መንገዱ የከፋ ቢሆንም በወሰዱኝ መንገድ ተመርቸ እሰማው የነበረውን የወገኖቸ የወህኒ የከፋ ኑሮና ህመም ፣ በተቆርቋሪ ጠያቂ ማጣት ፣ በፍትህ መነፈግ እይሆኑ ያሉትን ከመስማት ማየት ማመን ነውና በአካል ማየት ችያለሁ !

ከመታሰሬ ጥቂት ቀናት በፊት በግፍ ለተደበደበው፣ ሁለት አይኑን ላጣውና ” አይሆኑ ከሚሆን ቢሞት ይሻላል “ተብሎ የፎቶ መረጃው ሳይቀር በእጀ የገባውን ወጣት ምንዱብ የወህኒ ህይወትን ተጨባጭ ታሪክ ከአይን እማኞች ቃርሜያለሁ! እሱም ያለው ከታሰርኩበት የቅርብ ርቀት ነው ። … አትጠራጠሩ አገኘውም ይሆናል !

በዚህ የጭንቅ ሰአት ከእኔና ከቤተሰቦቸ ጎን ሆናችሁ አለኝታችሁን ለገለጻችሁልን ምስጋናየ ከፍ ያለ ነው ! ዛሬ ወደ ዝርዝር ጉዳዩ አንገባም ። በላይ በመላ አለም የምትገኙ ወገኖቸ ያሳያችሁኝ ድጋፍና መቆርቆር ከጨለማው ቤት ደርሶኝ ጽናት አጎናጽፎኝ ሰንብቷል። ይህም በአረብ ሃገር ስደተኛ ዙሪያ ሳቀርነው ለነበረው መረጃ ያገኘሁት ክብርና ሞገስ ሆኖ መከራውን አስረስቶኛል: ) ምስጋናየ አይለያችሁ!

ወገኖቸ ወዳጆች ፣ ዛሬ ሰላም መሆኔን ብቻ ተረዱ ብየ እንጅ በሰፊው ስለሚሆነው አቅም በፈቀደ መጠን እናወራለን ! ዝምታው ከናፈቅኳቸው ልጆቸ ፣ ከቤተሰቦቸና ከእናንተ ጋር የሚያደርሰው መንገድ ውል እንዲይዝ የሚደረገው ሙከራ ውል እንዲይዝ የሚተጉ ወገኖችን ሂደት ላለማደናቀፍ ብቻ ለመረጋጋት ሲባል ብቻ ነው !

በጨለመው የሳውዲ ወህኒም ይነጋል ፣ በንጋቱ ጮራ ታግዘን የምናወጋው የማለዳ ወግ ናፍቆኛል: ) ይህን ለማድረግ የሚከፈለውን ሁሉ ለመክፈል ደግሞ ልቤ ብርቱ ነው …

ሰላም ለሁላችሁ !

ነቢዩ ሲራክ
ከአንዱ የሳውዲ ወህኒ ቤት

Previous Story

Health: ሰዎች ለፍቅረኞቻቸው ታማኝ የማይሆኑበት ምስጢር

Next Story

አሉላ፣ የዮሐንስ፣ የጎበና እና የምኒሊክ ትውልድ! (ግርማ ሞገስ)

Go toTop