![](https://amharic.thehabesha.com/wp-content/uploads/2022/03/Abiy-7.jpg)
እንደ ጊዜው መክፋት
እንደ ግፉ መስፋት
እንደ አገሩ ክስመት
እንደ አገሬው ጥመት
እንደ ሰው ጭካኔ እንደ ልቡ ፍሬ
ተዐምር ነው መትረፍሽ ተዐምር ነው መኖሬ።
.
የበጎ ሰው ሀሳብ ሲካድ ዕለት በዕለት
ጉድጓድ ተምሶለት
ስብዕና ሲቀበር
በዚህ ምድር መኖር አያስመኝም ነበር።
.
ምድር ሳር ቅጠሉ በስጋት ተሞልቶ
የማለዳው ሰማይ እንደ አንቀልባ ቀልቶ
ታረደ
ነደደ
ከዘብጥያ ወጥቶ ዘብጥያ ወረደ
የሚል ዜና ብቻ አየሩን ሲሞላው
ሰው በገዛ ጥላው በረግጎ ሲሸበር
በዚህ ምድር መኖር አያስመኝም ነበር።
.
አዎ
ለጊዜውም ቢሆን ግፍ ያደነዝዛል
በደል ያስተክዛል
ጊዜም ጠብን ሽሮ ወደፊት ይጓዛል
በልብ ሰሌዳ ላይ ቂም ይደበዝዛል።
በነገ ያመነ፣
ልጁን ቀብሮ መጥቶ ሚስቱን ያስረግዛል።
ይቅርታና ምህረት
ፍቅርና ህብረት
ከግፍ ጋር ፍልሚያቸው ሲሆን የሞት ሽረት
ዳገት ይወጣሉ በእንጥፍጣፊ አቅም
የመኖር ፍላጎት፣
ዘመም ይላል እንጂ ተገርስሶ አይወድቅም።
(በእውቀቱ ስዩም – አዳምኤል፣ ገጽ 34)