ፋኖነት ዛሬ በእኛ ዘመን የተፈጠረ ሳይሆን አባቶቻችን ኢትዮጵያን እንደ ሃገር አሁን ባለችበት ደረጃ ጸንታ እንድትቆይ ያደረገ የጋራ የጀግንነት መጠሪያ የወል ስም ነዉ። ፋኖ ማለት ማንነት /Sentiment/ ነው። ፋኖ ማለት በዘመናት መለዋወጥ የማይደበዝዝ ፤ በስርዓት መቀያየር የማይሸረሸር የነፃነት አርማ ነው ።
ፋኖ አገር ተወረረች በተባለ ጊዜ ሁሉ መደበኛ ስራውን ወደ ጎን በመተው “እምቢ ለሃገሬ” ብሎ ህይወቱን የሚገብር በሰላም ግዜ አራሽ ፤ በጭንቅ ጊዜ ተኳሽ ነው ። ይህ የ”እምቢ ለባርነት” የትግል አርማ የሆነው ፋኖ ከትግል መልስ አርሶአደሩ የሚያርስ፣ ነጋዴው የሚነግድና ምሁሩ ወደ መደበኛ ስራው የሚመለስ ሃይል ነው።
ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያ የእናት ሃገር ጥሪ ባስተላለፈችበት ወቅት ጥሪውን ሳያቅማማ ተቀብሎ ከሌሎች ህዝባዊ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት ህይወቱን መስዋዕት እስከማድረግ በደረሰ ቁርጠኝነት ሃገር ለማዳን ተሟል ። ይህንን እንኳን እኛ ተግባሩን ያስተባበርን አካላት ይቅርና ለማንም ያልተሰወረ ሃቅ ነዉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር ፋኖን መሳሪያ ለማስወረድና እንዳይደራጅ እቅድ እንዳለው ተደርጎ በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው መረጃ ስህተት መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። ፋኖ ትጥቅ ያውርድ የሚል እንደ ክልል መመሪያ ያልወጣ መሆኑ እየታወቀ አንድ ዞን ተነጥሎ መመሪያ ያወጣል ብሎ ማሰብስ እንዴት ይቻላል ? ምስራቅ ጎጃም ዞን ከአማራ ክልል ዞኖች አንዱ እንደመሆኑ መጠን ከክልሉ ህግ እና አሰራር ያፈነገጠ ተግባር እንደማንሰራ በድጋሚ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።
ነገርግን ከዚህ የተዛባ መረጃ እና የጠላት ወሬ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በሞጣ ከተማ በተከሰተው ችግር የተከፈለውን የህይወት መስዋዕትነት ስሰማ ጥልቅ ሃዘን ተሰምቶኛል።
ይህንን የካቲት 27 / 2014 ዓም በሞጣ ከተማ የተከሰተውን እና የ 5 ወንድሞቻችንን ህይወት መቀጠፍ የሰማሁት ከክልሉ ዉጭ ለቅድመ ጉባኤ ለመሳተፍ በሄድሁበት ወቅት ነበር ። በድርጊቱም ሆነ የተከፈለዉን የህይወት መስዋዕትነት ስሰማ በእጅጉ አዝኛለሁ።
በመሆኑም ሞጣ እና አካባቢው ላይ የተከሰተውን ግጭትና የግጭቱን ምክንያት ከስር መሰረቱ በመመርመር የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር አጥፊዎችን በህግ አግባብ የሚያጣራ እና ለህግ የሚያቀርብ መሆኑን እየገለፅሁ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን እመኛለሁ።
አቶ አብርሃም አያሌው
የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ