የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ሰብሳቢ የሆኑት መስፍን አርአያ (ፕሮፌሰር ) መንግስት በኮሚሽኑ አሰራር ውስጥ ጣልቃ የሚገባ ከሆነ ከኃላፊነታቸው እንደሚለቁ አሳሰቡ

February 23, 2022

ዋና ሰብሳቢው መስፍን አርአያ የግል ማሳሳቢያቸውን የተናገሩት ሀገራዊ ምክክሩን ለሚመራው ኮሚሽን ሰሞኑን የተሾሙት ኮሚሽነሮች ዛሬ የካቲት 16 ቀን 2014 ዓም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ የስራ ትውውቅ ፕሮግራም ባደረጉበት ወቅት እንደሆነ ምክር ቤቱ በማህበራዊ ድረ ገጹ ካሰራጨው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

ይህንን ኃላፊነት የሰጣቸው የኢትዮጵያ ህዞብ በመሆኑ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው በኃላፊነት መንፈስ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን የተናገሩት የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፤ ከሚዲያውና ሌሎች አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ መናገራቸውንም ዘገባው አስረድቷል፡፡

አክለው ባደረጉት ንግግርም የአስፈፃሚው አካል ወይም የመንግሥት ጣልቃ-ገብነት እንደማይኖር እምነታቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

ነገር ግን በኮሚሽኑ አሰራር ውስጥ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የሚኖር ከሆነ ኃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው እንደሚለቁ ማሳሰባቸውን ምክር ቤቱ ያወጣው መረጃ ይገልጻል።

በስራ ትውውቅ ፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ኮሚሽኑ ሥራውን በገለልተኝነት በመሥራት የተሰጠውን ህዝባዊ ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ተመሳሳይ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

ፖለቲካ ከአገር በላይ ስላልሆነ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት የተሰጠውን ኃላፊነት ገለልተኛ በመሆን ታሪካዊ ሥራ ሰርቶ ማለፍ እንደሚገባው አፈ ጉባኤ ታገሰ ማስገንዘባቸውን መረጃው አመላክቷል።

በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አንድ አካል መሆናቸውን ጠቁመው፤ የምክክሩ ባለቤት ህዝቡ ስለሆነ ትክክለኛ ውሳኔ የሚጠበቀው ከህዝቡ መሆኑን አፈ ጉባኤው እንደገለጹ መረጃው ይገልጻል።

በተጨማሪም ኮሚሽኑ እቅድ አውጥቶ ወደ ሥራ እንዲገባ አስፈላጊው የሰው ኃይል፣ ቢሮ እና ግብኣቶች ሊሟሉለት ስለሚገባ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር አስፈለጊው በጀት እንደሚመደብ አፈጉባኤው ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ለሚያከናውነው ሀገራዊ ምክክር ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተሞክሮዎችን በማካተት እና በሕዝቡ መካከል ብዙ የባህል ትስስሮች ስላሉ እድሉን ለሕዝቡ በመስጠት እንዲሁም በማወያየት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ የኮሚሽኑ አባላት አበክረው እንደሚሰሩ በትውውቅ ፕሮግራሙ ወቅት መናገራቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል።

#ሪፖርተር

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ልዑክ ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ውይይት ማድረጉ ታውቋል።

Next Story

ሀገራዊ ምክክር የጥንሰሳ ምዕራፍ መጠናቀቅን አስመልክቶ – ከኢዜማ ሀገራዊ ምክክር ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

Go toTop