ሽፈራው ሽጉጤ ዲፕሎማቶችን የማሰልጠን ኃላፊነት በምክትል ዳይሬክተርነት ሊመሩ ነው

February 19, 2022

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያን አዳዲስ ዲፕሎማቶች የሚያሰለጥነውን በውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት ስር የተዋቀረ ዘርፍ፤ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በምክትል ዳይሬክተርነት ሊመሩ ነው። ሽፈራው ከሶስት ሳምንታት ገደማ በፊት የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት የስልጠና ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንደተሾሙ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከተቋሙ አረጋግጣለች።

ያለፉትን ሶስት ገደማ አመታት በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ሽፈራው፤ በምክትል ዳይሬክተርነት “ከተሾሙ በኋላ ወደ ተቋሙ አልፎ አልፎ ይመጡ” እንደነበር የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጌታሰው አዳነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አዲሱ ተሿሚ ከኢንስቲትዩቱ አመራሮች ጋር በይፋ ትውውቅ ያደረጉት ግን ከትላንት በስቲያ ረቡዕ የካቲት 9፤ 2014 እንደነበር አቶ ጌታሰው ገልጸዋል።

የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩትን በዳይሬክተርነት የሚመሩት፤ የቀድሞው የአማራ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዮሐንስ ቧያለው ናቸው። የቀድሞው የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር በከር ሻሌም የተቋሙ ምክትል ዳይሬክተር ሆነው ለአንድ ዓመት ሰርተዋል።

ዶ/ር በከር ባለፈው መስከረም ወር ከተካሄደው የመንግስት ምስረታ በኋላ በስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው በመሾማቸው ሌላ የስራ ኃላፊ ተክተዋቸዋል። ከባለፈው ጥር ወር መጀመሪያ ጀምሮ የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ሆነው እየሰሩ ያሉት አቶ ጃፋር በድሩ ናቸው።

የሽፈራው ሽጉጤ ወደ ኢንስቲትዩቱ ተሾመው መምጣት ተቋሙ ሁለት ምክትል ዳይሬክተሮች እንዲኖሩት ያደርጉታል። የኢንስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተርም፤ ሽፈራው የተሾሙበት ኃላፊነት ከዚህ ቀደም ከዚህ በፊት በተቋሙ ያልነበረ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “የኢንስቲትዩቱ ህንጻ እድሳት ላይ ስለሆነ፤ ምክትል ዳይሬክተሩ በጊዜያዊነት ቢሯቸው የሚሆነው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው” ሲሉም አክለዋል።የስትራቴጂ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት የተሰኘ መጠሪያውን ወደ የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት በቅርቡ የቀየረው ይህ ተቋም ተጠሪነቱ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው። አቶ ሽፈራው በምክትል ዳይሬክተርነት የሚመሩት የስልጠና ዘርፍ በኢንስቲትዩቱ እንዲካተት የተደረገው፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር የነበረ ሌላ ተቋም ከኢንስቲትዩቱ ጋር እንዲዋድ በመደረጉ ነው። የተዋሃደው ተቋም የኢትዮጵያን አዳዲስ ዲፕሎማቶች የማሰልጠን ኃላፊነት ያለበት፤ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ነው።

የፌደራል አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን ባለፈው መስከረም ወር የወጣው አዋጅ፤ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት መብት እና ግዴታዎችን ወደ የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት እንዲተላለፍ አድርጓል። የተዋሃዱት የሁለቱ ኢንስቲትዩቶች ኃላፊዎች የስራ ርክክብ ያደረጉት ትላንት ሐሙስ የካቲት 10፤ 2014 ነው። አዲሱ ተሿሚ አቶ ሽፈራው በዚሁ የርክክብ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተዋል።

የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩትን በምክትል ዳይሬክተርነት የመምራት ኃላፊነት የተረከቡት አቶ ሽፈራው፤ ለረዥም አመታት በተለያዩ ቁልፍ የስልጣን እርከኖች እየተሾሙ የሰሩ ፖለቲከኛ ናቸው። አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በሚያዝያ 2010 የመጀመሪያ ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ፤ ሽፈራው ሽጉጤ የግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስትር ሆነው ተሹመው ነበር። ሆኖም በዚህ ኃላፊነታቸው ከሁለት ወራት በላይ ሳይቆዩ በአምባሳደርነት ተሹመው ወደ ደቡብ ኮሪያ አቅንተዋል።

 

ሽፈራው የግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ለቀድሞው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሊቀ-መንበርነት በተደረገው ምርጫ ተወዳድረው ከተሸነፉ በኋላ ነው። በምርጫው ሽፈራው ከደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) አብይ አህመድ ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ)፣ ደመቀ መኮንን ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እንዲሁም ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ተወዳድረው ነበር።

በደቡብ ክልል ፕሬዝዳንትነት እና በደኢህዴን ሊቀ-መንበርነት ኃይለማርያም ደሳለኝን የተኩት ሽፈራው፤ በኢህአዴግ ተመሳሳዩን ማሳካት ሳይሰምርላቸው ቀርቷል። በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ሕዝባዊ ተቃውሞዎች እጅግ ባየሉበትና በገዢው ፓርቲ ላይ ከፍተኛ ጫና ባሳደሩባቸው አመታት፤ አቶ ሽፈራው የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ነበሩ።

በሰኔ 2005 ከአቶ ደመቀ መኮንን በተረከቡት የትምህርት ሚኒስትርነት የኃላፊነት ቦታም፤ ሽፈራው ፈታኝ ጊዜን አሳልፈዋል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቃውሞ በበረታበት በ2008 ዓ.ም. የብሔራዊ ፈተና ተሰርቆ ሲወጣ አቶ ሽፈራው የትምህርት ሚኒስትር ነበሩ።

ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በስልጣን ላይ ባሉበት ወቅት፤ ሽፈራው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ ሆነው ሰርተዋል። ሽፈራው ወደ ፌደራል መንግስት የስልጣን እርከን እስከተዘዋወሩበት ጊዜ ድረስ የደቡብ ክልልን በርዕሰ መስተዳድርነት መርተዋል።

(ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

aklog birara 1
Previous Story

“ከሽብርተኛው” ትህነግ ጋር ድርድር በምን ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ይደረጋል? –  አክሎግ ቢራራ (ዶር)

Next Story

የካቲት 12 በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ስፍራ ያለዉ ዕለት ነዉ

Go toTop