ካሁን በፊት የአማራ ክልል የሰማዕታት ሀውልት በሚል ይጠራ የነበረው “የአማራ ህዝብ ዝክረ ታሪክ ማዕከል” በሚል ተቀየረ

February 16, 2022

በዝክረ ታሪክ ማዕከሉ ውስጥ የአማራን ህዝብ ታሪክ፣ ባህልና ስነ ልቦና የማይገልፁ የኪነ- ሀውልት ስራዎችን በመቀየር እና በማሻሻል የአማራ ህዝብን ሥነ ልቦና፣ ታሪክ፣ ባህል እና ማንነት በሚወክሉ የኪነ ሀውልት ስራዎች እንዲተኩ ተደርገው ዛሬ በይፋ ተመርቀዋል።

በምርቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ም/ቤት አፈ ጉባኤ ክብርት ፋንቱ ተስፋዬ፣ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ፣ የአማል ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጌታቸው ጀንበር እና ሌሎች የክልል እንዲሁም የዞን ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

በዝክረ ታሪኩ ውስጥ የተከናወኑ ተግባራትን እና የማዕከሉን ስያሜ ጭምር ለመቀየር ለምን እንዳስፈለገ የአማራ ህዝብ ዝክረ ታሪክ ማዕከል ሀላፊ የሆኑት አቶ አዲስ በየነ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ማዕከሉ ከስያሜው ጀምሮ መሰረታዊ ችግር ነበረበት ያሉት ሀላፊው መሳሪያ ዘቅዝቆ የሚተክዝ ኪነ ቅርስ፣ ያለ አግባብ የተቀመጠ የመሳሪያ ካርታ፣ የሙዝዬም አደረጃጀቱ ከ1973 – 1983 ባለው ታሪክ ብቻ የተቀመጠ በመሆኑ፣ ቀድሞ በነበረው ስያሜና ኪነ ሀውልቶች ላይ የበርካታ ህዝብ ቅሬታ በመኖሩ፣ የአማራን ህዝብ ታሪክ እና ስነ ልቦና በትክክል ባለመግለፁ፣ ሰፊ ቦታ ይዞ ባለመልማቱና ለህዝብ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ ባለመሆኑ እንዲሁም በልዩ ልዩ ምክንያቶች ስያሜው እና ኪነ ሀውልቶች እንዲሁም ኪነ ቅርሶች እንዲቀየሩ ተደርጓል ብለዋል።

የዝክረ ታሪክ የማዕከል ሀላፊው አያይዘውም ወደ ትግበራ ከመግባታችን በፊት በተገቢው መንገድ ጥናት በማድረግ እና ከህዝቡ ግብዓት በመውሰድ ወደ ስራ መግባታቸውን በመግለፅ ነፍጥ ዘቅዝቆ የተቀመጠውን ሀውልት በአማራ ልዩ ሀይል የመተካት ስራ፣ የግቢ አጥር እና የአንበሳ ሀውልት ስራ፣ የሙዝየም አደረጃጀት ስራ፣ የስዕል እና ቅርፃቅርፅ ስራ፣ የላይ በራሪ አገልግሎት እንዲሁም አጠቃላይ ግቢውን የማስዋብ እና ለህዝብ አገልግሎት ክፍት የማድረግ ስራ እየተስራ ነው ብለዋል።

“የወታደራዊ ኪነ ቅርሱ ትርጉም የአማራን ህዝብ ጀግንነት፣ ለጠላት አይበገሬነትና ለሀገር መፅናት ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን የሚገልፅ ነው” ያሉት ሀላፊው ማዕከሉ የአማራን ህዝብ ታሪክ በትክክል የሚወክል እና የስነ ልቦና ከፍታውን በሚያሳይ መንገድ ስራ ተሰርቷል ሲሉ ገልፀዋል።

የአማራ ህዝብ በሀገረ መንግሥት ምስረታ ረጅም ታሪክ ያለው ህዝብ መሆኑን የገለፁት ሀላፊው በጎጃም፣ በጎንደር፣ በሸዋና በወሎ አካባቢዎች የተለያዩ ነገስታት ቤተ መንግስቶች መኖራቸው ይህንን ያረጋግጣል ሲሉም ነው ጨምረው የገለፁት።

ዝክረ ማዕከሉን ለማሻሻል እና የአማራን ህዝብ ታሪክ እንዲሁም የስነ ልቦና ከፍታ በሚያሳይ ደረጃ እንዲቀየር ልዩ ድጋፍ ላደረጉ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ እና አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ዘርና ኃይማኖት ተኮር ጭፍጨፋ በቃ NOMORE# የምንለው መቼ ነው? | Hiber Radio Special Program Feb 16, 2022

Next Story

ሕወሓት ላይ እጁን እየጠቆመ የሕወሓትን ፖሊሲ የሚያስፈጽመው ደመቀ መኮንን እና ቡድኑ ለስልጣን ሽኩቻ

Go toTop