በሶማሌ ክልል አብዛኞቹ ዞኖች የተከሰተው ድርቅ አርብቶ አደሩ እንደ ዓይኑ ብሌን የሚጠብቃቸው እና የሚሳሳላቸውን እንስሳቱን በመንጥቅ ህልውናን እየፈተነ ይገኛል። በክልሉ የተከሰተው ድርቅ ጉዳት ካስከተለባቸው ዞኖች አንዱ በሆነው የሸበሌ ዞን ስር ባሉ አካባቢዎች በመገኘት በርካታ እንስሳት የሞቱበትን አስከፊውን ሁኔታ ተመልክተናል።
ድርቅ አዲስ ክስተት አይደለም የሚሉት በሸበሌ ዞን ሀዳዌ እና ገቢአስ በተባሉ አካባቢዎች ከሚኖሩ አዛውንቶች መካከል አቶ ኑህ እና አቶ አብዱላሂ ከዚህ በፊት በቀያቸው ድርቅ ሲያጋጥም ሌላው ቢቀር ወደ ተሻሉት አጎራባች አካባቢዎች በመሄድ የእንስሳቶቻቸውን ህይወት ያቆዩ እንደነበር ጠቅሰው አሁን ግን የተሻለ ቦታ መጥፋቱን በማንሳት የዘንድሮ የከፋ መሆኑን ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።
እስካሁን የሰው ህይወት አላለፈበትም ያሉት ድርቅ ምናልባትም እንዲሁ የቀጠለ እንደሆን ለህብረተሰቡ ህልውናም ፈታኝ ይሆናል የሚል ስጋት እንዳላቸው በመግለፅ ሁሉም ወገን የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ድርቁ በፈተናቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ለተረፉ ጥቂት እንስሳቶቻቸው የሚሆን መኖ ፣ ለህብረተሰቡ የሚያገለግል የምግብ ድጋፍ እና ውሀ መንግስትም ይሁን መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ሁሉ በርብርብ እንዲያቀርቡላቸው የሚጠይቋቸው ሶስት መሰረታዊ ነገሮች እንደሆኑም ገልፀዋል።
የቪዲዮ ዘገባ፦ መሳይ ተክሉ
DW