እውን የሚነግሩን ወይም የሚያስነብቡን መሬት ላይ ስላለው እውነታ ነው ወይስ …? – ጠገናው ጎሹ

February 6, 2022

ጠገናው ጎሹ

“ግድፈቶችን በውስጣዊ ሥርዓት በማረምና አንድነታችንን በመጠበቅ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ኢዜማዊ ማህተማችን ማሳረፋችን እንቀጥላለን” የፓርቲው ብሄራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ (2/3/22) ።

ይህንን መግለጫ እንደ አንድ የኢትዮጵያ ፖለቲካና ፖለቲከኞች የውድቀት አዙሪትን እንደሚከታተልና እንደሚያሳስበው የአገሬ ሰው በጥሞና አነበብኩት። የሚያሳዝን እንጅ የሚያስገርም ሆኖ ግን አላገኘሁትም። ለምን? ቢባል እነዚህ የኢዜማ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ሞት የሞቱት እና የሞራል ዝቅጠት ውስጥ የተዘፈቁት ለተረኛ የኢህአዴግ አንጃ ቡድን (ብልፅግና ተብየ) ታማኝ አገልጋይነት (አሽከርነት) እራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ እለት የመሆኑ እውነታ ግልፅና ግልፅ ነውና።

መከረኛው የአገሬ ህዝብ በሥልጣነ መንበር ላይ ለዘመናት በተፈራረቁና አሁንም በዚያው እጅግ አስከፊ በሆነ ምህዋር ላይ መሽከራቸውን በቀጠሉ ሸፍጠኛ፣ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኛ ገዥ ቡድኖች እና ግብረ በላዎቻቸው ምክንያት  በድንቁርና፣ በፍፁም የድህነት አኗኗር (መኖር ከተባለ) ፣በበሽታ ፣  በአስከፊ ፖለቲካ ወለድ አረመኔያዊ ግድያና በቁም ሰቆቃ (በቁም ሞት) ፣ ወዘተ አዙሪት ውስጥ እንዲቀጥል የመደረጉን ግዙፍና መሪር እውነት ለማስተባበል መሞከር የለየለት የፖለቲካ አስተሳሰብ ስንኩልነት እና የሞራል ውድቀት ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

በመጀመሪያ ስለ “የተፎካካሪ ፓርቲ” ተብየው ኢዜማ ስንነጋገር የምንነጋገረው በውስጡ ካሉ አመራር ተብየዎች ፣ አባላት እና ደጋፊዎች ለይተን ወይም ነጥለን አይደለም። የየትኛውንም የፖለቲካ ወይም ሌላ አይነት ቡድን (ድርጅት) ጥንካሬ ወይም ደካማነት በአመራር ላይ ከተሰየሙ ግለሰቦች ፣ አባላት እና ደጋፊዎች ነጥሎ ማየት ከቶ አይቻልም።  አንዳንድ ግለሰቦችን በስም እየጠቀስን ወይም በደምሳሳው  እገሌ ቅን አሳቢ፧ እገሌ ነገር አዋቂ፣ እገሌ ዲስኩር አዋቂ፣ እገሌ የተማረ ፣ እገሌ ዶ/ር ወይም ፕሮፌሰር ፣ እገሌ የህዝብ ተቆርቋሪ፣ እገሌ ግብረገባዊ፣ እገሌ ግሩም ተንታኝ፣ እገሌ ሰላምና ፍቅር ሰባኪ፣ እገሌ ብልፅግና ናፋቂ፣ ወዘተ  ከማለት እና ለሌሎችን ደግሞ ተቃራኒ የሆነ የባህሪ ስያሜ በመስጠት  የሚደረግ የድርጅት እይታ በእራሱ ወይ የለየለት ድንቁርና ወይንም የአድርባይነት ደዌ ነው።

የትኛውም ሥርዓት ወይም ድርጅት የግለሰቦች ስብስብ እንደመሆኑ መጠን እና የግለሰቦች በጎ ወይም አፍራሽ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ የእይታችን ትኩረት መሆን ያለበት ግን ድርጅቱ ወይም ሥርዓቱ እንደ ድርጅት ወይም እንደ ሥርዓት ምን አደረገና ምን እያደረገ ነው? በሚል ፈታኝ ጥያቄ ላይ እንጅ ይህ ወይም ያ ግለሰብ እና እነዚህ ወይም እነዚያ ግለሰቦች በሚል እጅግ ቁንፅልና አሳሳች እይታ ላይ መሆን የለበትም። ለዚህ ነው “በኢዜማ ውስጥ እኮ ጥቂት እውነተኛለውጥ እንዲመጣ የሚፈልጉና የሚሠሩ ግለሰቦች አሉና … “ የሚለው ማስተዛዘኛ አይነት አመለካከት ጨርሶ ወንዝ የማያሻግረው።

የምናወራው ስለ ግለሰቦች ቅን ወይም የተወላገደ ባህሪና አካሄድ ሳይሆን ግለሰቦቹ እንደ ቡድን ወይም እንደ ሥርዓት አባልነታቸው አነሳሱና አካሄዱ ከራሱ አልፎ የህዝብን የእውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ሥርዓት ፍለጋ ተጋድሎ የሚያጨናግፍ (የሚያመክን) አስተሳሰብና ቁመና የተጠናወተውን ቡድናቸውን ወይም ፓርቲያቸውን በወቅቱና በአግባቡ ለማስተካከል ምን ያህል ጥረዋልአሁንስ ምን እያደረጉ ነው? ከሚል መሠረታዊ ጥያቄ አንፃር ባለመሆኑ ከክስተቶች የትኩሳት መጠን ጋር ከፍና ዝቅ ከሚል እጅግ አስቀያሜ የፖለቲካ አዙሪት ለመውጣት ከቶ አልተቻለንም።

በሌላ አገላለፅ የትክክለኛና እውነተኛ የፓርቲ ፖለቲካ (genuine and appropriate party politics) ለውጥ ሃዲዱን በመሳት ለእራሳቸው “ብልፅግና” የሚል እጅግ አሳሳች (highly deceptive) ስያሜ በመስጠት  የቤተ መንግሥት ፖለቲካውን በተረኝነት ከተቆጣጠሩት ሸፍጠኛ ፣ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ የኢህአዴግ አንጃ (faction) ቡድኖች ጋር ያልተቀደሰ (unholy) ጋብቻ በመፈፀም እነ አብይን (“የለውጥ ሃዋርያትን”)  መቶ በመቶ (ከራሱና ከእራሱ ፓርቲ ተብየ) በላይ እንደሚያምናቸው ያለምንም ሃፍረት (እንዲያውም በኩራት ) የነገረንን ኢዜማን ከላይ በተገለፀው አጭር  የፖለቲካ ድርሰት ለመሸፋፈን መሞከር ከስህተት ያለመማር እጅግ አስቀያሜ የፖለቲካ አስተሳሰብ ደዌ ነው። መሬት ላይ ከሆነውና እየሆነ ካለው ግዙፍና መሪር ሃቅ ጋርም እንኳን ለማጣጣም ለማስመሰለም ፈፅሞ አይቻልም።

የግንቦት ሰባት መሪዎች በመሆን ቅጥፈት በተሞላበት (እጅግ አሳሳች) ዲስኩር በየአደባባዩና በየአዳራሹ ሲያስጨበጭቡን ቆይተው ሥርዓት ባልተለወጠበት ወይም እንዲለወጥ የሚያስችል የፖለቲካ ሃይል በሌለበት የኢህዴግ አንጃ  (“የለውጥ ሃይል”) ተለጣፊዎች በመሆን የመከረኛውን ህዝብ የመከራና የውርደት እድሜ እንዲራዘም ማድረጋቸውን ለመረዳት ቅንና ሚዛኑዊ ህሊና ብቻ በቂ ነው።  አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቸግር በቅን ልቦና እና በጠንካራ ድርጅታዊ ይዘትና ቁመና የመታገል እንጅ መሪ እና ሊቀ መንበር የሚል የአደረጃት እርከን (ዝባ ዝንኬ)  መፍጠር ያለመቻል ጉዳይ  ይመስል “ኢዜማችን ልዩ ነው” ሲሉን ህሊናቸውን ጨርሶ አይጎረብጣቸውም።

የሚያስነብቡን  የፖለቲካ ድርሰታቸውን ዘመኑን የዋጀ፣ ወቅቱን ያገናዘበ፣ የአገርንና የህዝብን ጥቅም ያስቀደመ ፣ ወዘተ በሚል ቅድመ ሃሳብ  (መንደርደሪያ) ለማንቆለጳጰስ ሲሞክሩ ይሉኝታ የሚባል የህሊና ዳኝነት ጨርሶ የላቸውም።

ሁለቱ የኢህአዴግ አንጃዎች (ህወሃት እና ብልፅግና ተብየው) በሥልጣን የበላይነት ሽኩቻ ምክንያት በፈጠሩት ውዥንብርና ጦርነት በመከረኛው ህዝብ ላይ ታይቶ የማይታወቅ ሰቆቃና እልቂት ሲደርስበት እንኳንስ በድርጊት ትርጉም ባለው የቃል ወይም የወረቀት ላይ  መግለጫ የመሞገትና የማውገዝ ወኔው ሳይኖራቸው አሁን ደግሞ እንዲህ ዓይነት  ድርሰታቸውን ከምር እንወስድላቸው ዘንድ ጫጭረው (ፅፈው) ሲለጥፉልን እናንተ እነማን ናችሁ?  በሎ መጠየቅ ተገቢ ብቻ ሳይሆን በእጅጉ አስፈላጊ ነው።

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን እነዚህ የኢዜማ መሪዎች የአስከፊ ተለጣፊነት (አሽከርነት) ልክፍተኞች ከሆኑት እና የአማራን ማህበረሰብ በተለይ እና የኢትዮጵያ ህዝብ በአጠቃላይ ከመከራና ከውርደት ሥርዓት እንዳይላቀቅ ካደረጉት ብአዴናዊያን ፣ እና እጅግ አሳፋሪ በሆነ አኳኋን ፖለቲካን  እስከ ሚኒስተርነትና የተከበሩ የፓርላማ አባልነት ለሚደርስ  የጥቅም ወይም የፍርፋሪ ማስገኛ ወይም መልቀሚያ ካደረጉት አብን ተብየዎች በምን ትለያላችሁ? ተብለው ቢጠየቁ ከዚያው ከለመደማቸው የቅጥፈት ዲስኩር የተሻለ መልስ አይኖራቸውም።

“በሁለንተናው የተሟላለት ድርጅት መሪዎች ስለሆን ዲሲፕሊን በሚጥሱት ላይ ተገቢውን እርምትና ሌላም እርምጃ እንውስዳለን” ሲሉን ስለ የትኛው እውነተኛና ገንቢ ዲሲፕሊናችሁ ነው የምታወሩት? ግዙፍና መሪር መስዋእትነት በተከፈለበት የመሠረታዊ  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ጅማሮ ላይ የበረዶ ውሃ ቸልሶ ከሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ ተረኛ የኢህአዴግ አንጃ (ብልፅግና ተብየ) ጋር በፖለቲካ አመንዝራነት ከመተሻሸት የከፋ (የባሰ) የበጎ ዲሲፕሊን ፣ ራእይ፣ መርህ፣ ዓላማና ግብ ዝቅጠት (ውድቀት) አለ እንዴብለን በግልፅና በቀጥታ መጠየቅ የግድ ነው

አዎ! ከእንዲህ አይነት እጅግ ወራዳና አዋራጅ የፖለቲካ አስተሳሰብና የሞራል ድህነት በአሸናፊነት መውጣት ካለብን እስከዚህ ድረስ ነው መነጋገር ያለብን። ኢዜማ ተብየውን በእጅ መንሻነት (በሥጦታ መልክ) አስረክበው የሚኒስትርነት ሹመት ሲቸራቸው ህሊናቸውን ሳይጠይቁና አይናቸውን ሳያሹ በመቀበል የሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ ተረኛ ኢህአዴጋያን/ብልፅግናዊያን ፖሊሲና ፕሮግራም አስፈፃሚ በሆኑ ኢዜማዊያን የፖለቲካ ጨዋታ  ዴሞክራሲያዊት  ኢትዮጵያ እውን ትሆናለች ብሎ መጠበቅ ወይም የለየለት ድንቁርና ወይም የምን አገባኝነት ደዌ ወይንም የአስከፊ አድርባይነት (ልክክስክስነት) ልክፍት ነው  ።

በእንዲህ አይነት እጅግ ግልፅና ግልፅ የወረደና አዋራጅ የአሽከርነት (የተለጣፊነት) ፖለቲካ አረንቋ (disgraceful political quagmire) ውስጥ ተዘፍቆ “ልዩነቶችን በዴሞክራሲያዊ ወይይት እየፈታን እና እንደ አለት እየጠነከርን እንቀጥላለን” የሚለውን የወረቀት ላይ ድርሰት በመሬት ላይ ከሆነውና እየሆነ ካለው ግዙፍና መሪር እውነታ ጋር እንኳን ማጣጣም ማመሳሰልም ጨርሶ አይቻልምና የሚሻለው ሃቁን ተጋፍጦ እራስን ከተዘፈቁበት ክፉ አዙሪት ለማውጣት እጥፍ ድርብ ጥረት ማድረግ ነው!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

መኪና አሳዳጅ ውሾች! – በሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

Next Story

ፖለቲካ የማስተዳደር ጥበብ እንጂ ቁማር አይደለም – ከንገሤ አሊ

Go toTop