አገር ከገጠማት አደጋ ለመታደግ የጋራ ምክክሩ እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ መፍትሄ መሆኑን የአብን የፖለቲካ ጉዳዮች ሃላፊና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ አመለከቱ።
አቶ ክርስቲያን በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት አስተያየት፣ አገሪቱ በይደር በመጡት ችግሮችና የተለያየ ፍላጎቶች፣ አመላካከቶችና ዋልታ ረገጥ ጥያቄ ባላቸው የፖለቲካ ሃይሎች ተወጥራ አገረ መንግሥቱና የአገሪቱ ህልውና ጥያቄ ውስጥ ከገባ ውሎ አድሯል። የተለያዩ አመለካከቶችና ጥያቄዎችም እንደ ውበት ተቆጥረው ለውይይት በር ከፋች መሆን ሲገባቸው አልፈው ለዜጎች ሞትና ሰቃይ እንዲሁም የጦርነት መነሻ ሆነዋል።
አመለካከቶቻችንና ጥያቄዎቻችን ወደ ውይይት ቢመጡ ኖሮ ይሄ ሁሉ የሰው ሕይወት መጥፋትና ንብረት ወድመት ባልተከሰተ ነበር ያሉት አቶ ክርስቲያን፣ ነገር ግን አገሪቱን ለመታደግ ሊደረግ የታቀደው ምክክር ሚናው የላቀ ቢሆንም “ኢትዮጵያ በመቃብሬ ላይ ነው፤ ሲኦልም ቢሆን ወርጄ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ” ከሚል አሸባሪ ቡድን ጋር ግን ፈጽሞ መካሄድ እንደሌለበት ጠቁመዋል።
ብሔራዊ ምክክሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቅቡልነት ያለው ጉዳይ ከመሆኑም በላይ በምክክሩ የሚነሱ ሃሳቦች ለአገሪቱ መጻዒ እድል ወሳኝ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ለዘላቂ መተማመንና መከባበር በብሄራዊ ምክክሩ በይቅርታ የሚታለፉ ጉዳዮች በይቅርታ በማለፍ በይቅርታ የማይታለፉ ጉዳዮችን ደግሞ ተበዳዮች የሚካሱበትና በዳዮች በፍትህ ሽግግር የሚዳኙበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል።
በምክክሩ ለዘመናት የዘለቁ ችግሮች የተሟላ እልባት ያገኛሉ ማለት ሳይሆን በዋናነት ለአገረ መንግሥቱ ለህልውና አደጋ የሆኑ፣ የሕዝቡ አብሮነት፣ ሰላምና አንድነት ጥያቄ ውስጥ ያስገቡ ጉዳዮች የትኩረት አጀንዳ እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ከሁሉም በላይ የምክክሩን አቅጣጫ ለማሳትና ወዳልተፈለገ መንገድ ለመምራት የሚፈልጉ ወገኖች አካሄዳቸውን ማስተካከል እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።
በተለይ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ ወድመትን ያስከተለ፣ የአገር መከላከያን በመውጋት ክህደት የፈጸመ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ከፍተኛ ማህበራዊ ምስቅልቅልን ከፈጠረው አሸባሪው የትህነግ ቡድን ጋር መመካከር ከዚህ በኋላ ለአገሪቱ የሚያመጣው ፋይዳ እንደሌለ ያስገነዘቡት ኃላፊው፣ እንደ ሕዝብ ግን የትግራይ ሕዝብ በብሔራዊ ምክክሩ ሊሳተፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
መንግሥት ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት በሚል ሃሳብ አንዴ በይቅርታ አንዴ፤ በምህረት ፤ሌላ ጊዜ ደግሞ ክስ በማቋረጥ በማለት እርስ በእርሱ የሚጣረስ መግለጫ በማውጣት የሽብር ቡድኑ አባላት ከእስር ቤት ማስለቀቁ እንደ ፓርቲያቸው ተቀባይነት የሌለው ውሳኔ መሆኑን የተናገሩት አቶ ክርስቲያን፣ ጉዳዩ ዳግም እንዲፈተሽ ከመንግሥት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ቀጣይ ምክክር እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።
ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ጥር 8 ቀን 2013 ዓ.ም