ኢትዮጵያ ጠልነቱን በተግባር ያሳየው አሸባሪው ህወሃት በደሴ ሙዚየም ሊተኩ የማይችሉ ቅርሶችን አውድሟል፣ ዘርፏል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እንወዳለን ያለበትን እኩይ ህልሙን ለማሳካት ያልወጣው ዳገት፣ ያልወረደው ቁልቁለት፣ ያልፈጸመው ኢሰብአዊ ድርጊት፣ ያልሰራው ወንጀል የለም።
በወረራ በገባበት አካባቢ ሁሉ ንጹሀንን ገድሏል፣ ሴት ደፍሯል፣ ሀብትና ንብረት ዘርፏል፣ የተረፈውን ከጥቅም ውጭ አድርጎ አውድሟል።
የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያ እሱ እንዳለው በአንድ ጀምበር ትጠፋ ይመስል የትውልድ መገንቢያ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የጤና ተቋማትን፣ ኢትዮጵያ ትናንት እንዲህ ነበረች ብለው የሚያስረዱበትን ቅርስ እያወደመ አጥፍቷል።
ከመልካምነት ይልቅ ክፋት፣ ከልማት ይልቅ ጥፋት፣ ከመስራት ይልቅ ማፍረስ የሚቀናቸው የሽብር ቡድኑ የጥፋት እጆች እድሜ ጠገቡን የደሴ ሙዚየም በማውደም ወደ ነበርነት ቀይረውታል።
የደሴ ሙዚየም አስጎብኝ ወጣት ፍሰሀ ፈለቀ እንዳለው ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዓመት በላይ ያስቆጠሩ የአርኪኦሎጂ ግኝቶችን ጨምሮ ውድ የሆኑ የታሪክ ቅርሶችን የያዘ ሙዚየም ነው።
ሙዚየሙ የታሪክ፣ የአርኪኦሎጂ፣ ኢትኖግራፊክ መሳሪያዎች ያሉበት ኢትዮጵያዊ ማንነትን የሚገልጹ በተለይ የወሎን ማህበረሰብ ሁነት የሚያንጸባርቁ ቅርሶች እንደነበሩበት ገልጿል።
ይሁን እንጂ ታሪክን በማጥፋት ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳው ሀይል የጥፋት በትሩን በደሴ ሙዚየም ላይ አሳርፏል ብሏል።
ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በ1941 ዓ.ም ከእንግሊዟ ንግስት ኤልዛቤጥ በስጦታ የተበረከተላቸው ከብር የተሰራ ሻሞላ/ሰይፍ እንዲሁም በአድዋ ጦርነት ወቅት ዳግማዊ አፄ ሚኒልክ ይጠቀሙበት የነበረው የጦር ሜዳ መነጽር እንዲሁም ሌሎች ውድ ቅርሶች ተዘርፈዋል፣ የቀሩት ጥቅም እንዳይሰጡ ተደርገው ወድመዋል ብሏል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ሰይድ አራጋው የሽብር ቡድኑ የኢትዮጵያን የማንነት መገለጫ የሆኑ ቅርሶችን በማውደም ኢትዮጵያ ጠልነቱን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።
በደሴ ሙዚየም ለትውልድ ታሪክ የምናስተላልፍባቸው በገንዘብ የማይተኩ ውድ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ተዘርፈዋል፣ የማይንቀሳቀሱት ከጥቅም ውጭ ሆነዋል ብለዋል።
አሸባሪው ህወሓት ቅርሶቹን ከደበቀበት ቦታ መመለስ ካልተቻለ ሊተኩ አይችሉም ብለዋል።
“ለኢትዮጵያ ፍቅር ለጃንሆይ ክብር” በሚል ከእንግሊዝ ንግስት የተበረከተው ሰይፍ፣ ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ አድዋ ላይ የተዋጉበት የጦር ጎራዴ፣ አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ያጠፉበት የሚመስል ሽጉጥ ሊተኩ የማይችሉ ቅርሶች ናቸው ብለዋል።
ሌላው የውድመትና ዘረፋ ኢላማ የሆነው በ1938 ዓ.ም የተመሰረተው የአስፋውወሰን ኃይለስላሴ ቤተ መንግስት የነበረውና ደሴ የሚገኘው የመርሆ ቤተ መንግስት ነው።
የመርሆ ቤተ መንግስት አስጎብኚ አቶ መስፍን ሞላ ታሪክን የሚገልጹ ቅርሶች፣ ሰነዶችና ሌሎች ማስረጃዎች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ገልጸዋል።
“እኔ በአፄ ኃይለስላሴም በደርግም ኖሬያለሁ እንደዚህ አይነት አስከፊ ውድመት አይቼ አላውቅም” የሚሉት አቶ መስፍን ጎብኝዎች ሊያውቋቸው የሚገቡ ቅርሶች በሙሉ መዘረፋቸውን ገልጸዋል።
የንጉስ ሚካኤል ቤተ መንግስት አስተዳዳሪ አቶ መጂድ ኢማም ቤተ መንግስቱ 1875 ዓ.ም የተሰራ የወሎን ህዝብ ታሪክ የሚያንጸባርቅ የታሪክ ማስረጃና ሀብት ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ ቤተ መንግስቱ በየጊዜው እድሳት ስለሚያስፈልገው ለእድሳት የተገዙ ከአምስት ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ሀብት በቡድኑ አማካኝነት ዘረፋና ውድመት ተፈጽሞባቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የቤተ መንግስቱን በርና መስኮት በመሰባበር ታሪካዊ ይዘቱን እንዲያጣ አድርገውታል ብለዋል።
_ አካባቢህን ጠብቅ፣
_ ወደ ግንባር ዝመት፣
_ መከላከያን ደግፍ።
ታህሳስ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ)