ቴድሮስ አድኃኖም ለቀጣይ ዙር ብቸኛ ተወዳዳሪ ብቸኛ እጩ የዓለም ጤና ድርጅት በመግለጫው ዐስታውቋል

October 29, 2021

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊው ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ለቀጣይ ዙር ብቸኛ ተወዳዳሪ መሆናቸውን ዛሬ ዐስታወቀ። ዶ/ር ቴድሮስ በማመልከቻ ጽሑፋቸው ኮቪድ-19 ወረርሺኝ፦ «ዓለምን ማንኮታኮቱን» ገልጠው በሁለተኛ ዙር የሥልጣን ዘመናቸው ዓለማችንን ለመሰል ወረርሺኝ «የምር ዝግጁ» መሆኗን ማረጋገጥ ፍላጎታቸው መሆኑን ጠቁመዋል ሲል የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) ዘግቧል። ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም የዓለም የጤን ድርጅት ዋና ኃላፊ ሆነው የተመረጡት በጎርጎሪዮሱ 2017 ነበር። የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመናቸውም ባለፈው ነሐሴ ወር ውስጥ ነው የተገባደደው። «መስከረም 13 ቀን፣ 2014 ዓም በነበረው ቀነ-ገደብ በአባል ሃገራት የቀረበው እጩ አንድ ብቻ ነበር፤ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ገብረእየሱስ» ሲል የዓለም ጤና ድርጅት በመግለጫው ዐስታውቋል፤ በ28 ሃገራት እጩ ሆነው መቅረባቸውንም ዓለም አቀፉ ድርጅት ይፋ አድርጓል።

ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተያያዘ በርካታ ኢትዮጵያውያን ዶ/ር ቴድሮስ እጃቸው አለበት ሲሉ ይከሳሉ። በቅርቡ ይፋ በሆነ የድምፅ ቅጂ ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ኃላፊ የነበሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊዎች፦ የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የተመድ ኃላፊ እንዲነሱ ግፊት እያደረጉ ነው ሲሉም በቃለ ምልልሱ ተደምጧል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በኢትዮጵያ የዓለም የፍልሰተኞች ጉዳይ ድርጅት (IOM) ዋና ኃላፊ ማውሪን አቺንግ ከሌላ የተመድ ባለሥልጣን ጋር በመሆን ስለ ኢትዮጵያ በስፋት በመዘገብ ከሚታወቀው ካናዳዊው ደራሲና ጸሐፊ ጄፍ ፒርስ ጋር ያደረጉት ረዘም ያለ ቃለ ምልልስ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ሰሞኑን ሲንሸራሸር ቆይቷል።

ዶ/ር ቴድሮስ ኮቪድ-19 ወረርሺኝ ዓለምን ባዳረሰበት ወቅት ይበልጥ ታውቀዋል። የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊው ለቻይና ያደላሉ የወረርሺኙን መነሻ በማድበስበስም «የቤጂንግ አሻንጉሊት ናቸው» በሚል ሀገራቸው ከዓለም አቀፉ ድርጅት እንድትወጣ አዘው ነበር። የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ውስጥ የኤቦላ ተሐዋሲን እንዲዋጉ የላኳቸው ሠራተኞቻቸው አስገድዶ መድፈር እና የወሲብ ጥቃት ፈጽመዋል የሚል ዘገባ መውጣቱም ለብርቱ ሒስ ዳርጓቸዋል። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2018 እስከ 2020 ድረስ ባሉት ጊዜያት 21 የዓለም ጤና ድርጅት ሠራተኞች የአስገድዶ መድፈር እና የወሲብ ጥቃት መፈጸማቸው እንደተገለጠ የፈረንሳይ የዜና አገልግሎት (AFP) ዘግቧል። ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖምን የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ዋና ኃላፊ ሆነው ዳግም እንዲመረጡ የእጩነት ድጋፍ ከሰጡ ሃገራት መካከል 38 የአውሮጳ ሃገራት ይገኙበታል። ከአፍሪቃ ኬንያ እና ሩዋንዳ ድጋፋቸውን ሠጥተዋቸዋል።

DW

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ከፋሺስት የከፋ… ዘጋቢ ፊልም

244520714 4918606008166713 6887600739069403657 n
Next Story

የመጠሪያ ለዉጥ ለዉጥ ወይስ ለመገላበጥ ? – ማላጂ

Go toTop