መሰረት ተስፉ (Meserettesfu4@gmail.com)
ሁላችንም እንደምናውቀው ህወሓቶች ትግል ሲጀምሩ ትግራይን ከኢትዮጵያ በመነጠል “ታላቅ ሃገር” እንመሰርታለን የሚል ስትራቴጅ ነድፈው ነው። ይህን መሰረት አድርገውም አደረጃጀቶቻቸውን ሲያጠናክሩና አባላቶቻቸውን ሲገነቡ ቆይተዋል። በዚህ መሰረትም በ1982 ዓ.ም አከባቢ ትግራይ በቁጥጥራቸው ስር መሆኗን በተረዱ ጊዜ አብዛኛዎቹ የህወሓት አባላት በጅምላ እየፈረሱ ወደየቤተሰቦቻቸው መሄዳቸው ይታወቃል። እኔ በተወለድኩበት አከባቢ ከነበሩ አንዳንድ ወጣት (በነሱ አጠራር ማንጁስ ተብለው ከሚታወቁ) የህወሓት ተዋጊ ጓደኞቻችን ውስጥ እንኳ ከዚህ በኋላ ታግላችሁ ራሳችሁን ከደርግ ነፃ አውጡ ብለው በምስጢር ተሰናብተውን የሄዱ እንዳሉ አስታውሳለሁ።
ኋላ ላይ ግን አመራሮቹ ባካሄዱት ግምገማ ደርግ ስልጣን ላይ እሳክለ ድረስ ሰላማዊ የሆነች “ታላቋን” ትግራይን መገንባት አይቻልም የሚል ድምዳሜ ላይ በመድረሳቸው ምክንያት በመላ ትግራይ ህዝባዊ ኮንፈረንሶች፣ ውይይቶችና ስብሰባዎች እንዲካሄዱ ካደረጉ በኋላ ትግሉ በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ወደ መሃል ሃገር እንዲገባ ተደረገ። ለዚህ የተመረጠው መጓጓዣ ደግሞ በአቻነት ላይ ያልተመሰረተው ኢህዴግ የተሰኘው ግንባር እንደነበር ለአብዛኞቻችን ግልፅ ይመስለኛል። ትግሉ በዚህ መልክ እንደ አዲስ ተጠናክሮ ወደመሃል ሃገር ከገባ በኋላ ነው ደርግ ከስልጣን የተወገደው።
በዚህ ሂደት ህወሓቶች የመረጡት የትግል ስልት ደግሞ አማራውን ትምክህተኛ፣ ገዥ፣ ጨቋኝ፣ ጨፍላቂ፣ ነፍጠኛ፣ ቢሮክራት እና የደርግ እርዝራዥ እንደሆነ አድረገው በመስበክ የውጭዎቹን ወዳጆቻቸውን ጨምሮ ሌሎች እንዲጠራጠሩትና እንዲጠሉት ማድረግን ነበር። ይህ ስልት ያሰቡትን ያህል ባይሆንም ፍላጎታቸውን በጥቂቱም ቢሆን አሳክቶላቸዋል ማለት ይቻላል። ምክንያቱም እነሱና የእነሱን አሻራ የተከተሉት የኦነግ ፅንፈኞች በበተኑት የጥላቻ ዘር የተነሳ አማራው በማነቱ ምክንያት ሲፈናቀል፣ ሲጨፈጨፍና ንብረቱ ሲወድም መመልከት እየተለመደ መጥቷል። አንዳንዴም ዛፍ ቆርጠሃል በሚል ተራ ምክንያት ጭምር ለአመታት ከኖረበት ቀየው ተፈናቅሎ ቤት አልባ እንዲሆን የተደረጉባቸውን አጋጣሚዎችም አስተውለናል።
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ከኦነጎች ጋር ተጣምረው “በህዝቦች መካከል የነበረ የተዛባ ግንኙነት” የሚል ሃረግ ህገመንግስቱ ውስጥ በመሰንቀር የአማራን ህዝብ ተቋማዊ በሆነ መንገድ ለመድፈቅ ያልሄዱበት መንገድና ያልተጓዙት እርቀት አልነበረም። ይህን ስሁት ትርክት በመጠቀም በማንነት ላይ የተመሰረተ የቁጩ የፌዴራል ስርዓት አቋቁመው ብሄር ብሄረሰቦችን ከፋፍለው ለመግዛት ሲጠቀሙበት እንደነበረ ገሃድ የወጣ ጉዳይ ነው። እንዲያውም ሁኔታዎችን በደንብ ላጤነ ሰው ህወሃቶች ያቋቋሙት እውነተኛ ፌዴራላዊ ስርዓት ሳይሆን አህዳዊ ነው ወደሚል ድምዳሜ መድረሱ የሚቀር አይመስለኝም። ምክኒያቱም ፌዴራል ስርዓቱን አቋቁመዋል የሚባሉት ክልሎች የራሳቸው ነፃነት የሌላቸው፤ ይልቁንም በልምድ ማካፈል ሰበብ በህወሃት ካድሬዎች የሚዘወሩና የሚሾሩ እንደነበሩ ይታወቃል።
ለምሳሌ ሶሎሞን ፂሞ ኦሮሚያ፤ ቢተው በላይ ደግሞ ደቡብ ላይ የህወሃት ፍላጎት አስፈፃሚዎች እንደነበሩ በታሪክ ተመዝግቦ ያለፈ ሃቅ ነው። አዲስ አበባ እና ድሬዳዋም ቢሆኑ እንደየቅደም ተከተላቸው ተስፋ ማሪያምና ፍሰሃ ዘሪሁንን የመሳሰሉ የህወሃት ከፍተኛ ካድሬዎች የሚያሸከረክሯቸው የፌዴራል ተቋማት ነበሩ። ሶማሊ ክልልም የህወሃት ጄኔራሎችና ሌሎች ሲቪል ካድሬዎቻቸው ኮንትሮባንድን ጨምሮ ምን ምን ያደርጉ እንደነበር በስፋት ይገለፅ ስለነበር እዚህ ላይ መድገሙ አስፈላጊ ሆኖ አልታየኝም። ሌሎቹ ክልሎችም በህወሃት ቅኝ ተገዝተው ነበር ቢባል ማጋነን የሚሆን አይመስለኝም።
በዚያ ላይ (አሁንም እጆች ቀይረው ችግሮቹ እየቀጠሉ እንዳሉ የሚያሳዩ ምልክቶች ቢኖሩም) ህወሓቶች “በዘመናቸው” መከላከያውን፣ ፖሊሱንና ደህንነቱን ጨምሮ ሁሉንም የፌዴራል ተቋማት ጠቅልለው ይዘዋቸው እንደነበር (እንደሚባለው የማስታወስ ችግር ከሌለብን በስተቀር) ልንዘነጋው የምንችለው ጉዳይ አይደለም። ፖሊሲዎች፣ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ሲወጡ እንኳ የነሱን ጥቅሞች ለማስከበር የታለሙ እንደነበሩ ለብዙዎቻችን የተደበቀ አልነበረም።
በነዚህና በሌሎች ምክንያቶች የህወሃቶች የግፍ ፅዋ ሞልቶ በመፍሰሱ ህዝቡ አሻፈረኝ አለ። ይህን የህዝብ ትግል እንደ ግብዓት በመጠቀም ደግሞ ኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ ሃይሎች ህወሓቶችን ገፍተው መጣል እንደቻሉ እናስታውሳለን። በዚህ ውስጣዊ ትግል ወቅት ብአዴንና ኦህዴድ ተጣምረው ያደረጉት አስተዋፅዖ ቀላል ግምት የሚሰጠው ባይሆንም በተለይ ብአዴን ውስጥ የነበሩ የተወሰኑ አመራሮች ለህወሓቶች የጉሮሮ ላይ አጥንት ሆነውባቸው እንደነበር ሁኔታውን የሚያውቁ ሰዎች የሚመሰክሩት ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ ነብሱ በሰላም ትረፍና ባንድ ወቅት ከዶ/ር አምባቸው ጋር ተገናኝተን ስናወራ “ገድላችን ገበያ ላይ አውጥተን አልቸረቸርነውም እንጅ እንደኛ (እንደ ብአዴኖች ማለቱ ነው) ህወሃትን የታገለና የተጋፈጠ ማንም ሃይል የለም” ያለኝን አስታውሳለሁ። ለዚህም ነው ህወሓቶች ብዙውን ጊዜ ደኢህዴንንና ኦህዴድን ሳይሆን ብአዴንን ነጥለው ሲያብጠለጥሉት የሚሰሙት።
በዚህም አለ በዚያ ህወሓቶች ኢትዮጵያን በግዛት ከፋፍለው ለመግዛት ወጥነውት የነበረው የሃያ ሰባት አመታት ሙከራ መጨናገፉን ሁላችንም እናውቃለን። ባለፉት ሶስት አመታትም እንዲሁ “ፌዴራሊስት ናቸው” የሚሏቸውን ቡድኖች ጋልበው ኢትዮጵያን እንደገና ከፋፍለው ለመግዛት ጥረት ቢያደርጉም ብዙ ርቀት ሊያስከኬዳቸው አልቻለም። ይህን ሁሉ ሙከራ አድርገው አልሳካ ሲላቸው ደግሞ ወደ መጀመሪያው ውጥናቸው በመመለስ ያለ የሌለ ሃይላቸውን ተጠቅመው በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በማድረስ “ታላቋን ትግራይን” ለመመስረት የሞት ሽረት ጥረት ቢያደርጉም አሁንም እቅዳቸው አልሰመረም።
በቅርቡ ደግሞ አጠቃላይ ጉዟቸውን ገምግመው ይመስላል በጀኔራል ፃድቃን፣ በጌታቸው ረዳ፣ በሌሎች ጄኔራሎቻቸውና በሁሉም የሚዲያ ሰዎቻቸው አማካኝነት “አማራ ልሂቃን” የሚል አዲስ የሚመስል ግን የነበረ አጀንዳ ይዘው ወደ መድረክ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ህወሃቶች ለፖለቲካ ፍጆታ ሲሉ “የአማራ ልሂቃን” ይበሉ እንጅ ትኩረታቸው የአማራን ህዝብ በመበቀል አድርገው ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደሆነ ከሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ለመረዳት የሚከብድ አይመስለኝም። ምክንያቱም ከዚህ በፊትም “ትግላችን ከትምክህተኞች፣ ከጨፍላቂዎችና ከአህዳውያን ጋር ነው” ይሉ የነበረ ቢሆንም እነዚህን ተቀጥላ ስሞች እየለጠፉ ሲያሰቃዩት የነበረው ግን ይህንኑ መከረኛ የአማራ ህዝብ ነው። የህወሓቶች ትኩረት አማራ ህዝብ ላይ ከሆኑባቸው ምክንያቶች ውስጥ ደግሞ የተወሰኑት የሚከተሉት ናቸው።
- ከፋፍሎ የመግዛት ሙከራቸውን በዋነናነት ያከሸፈው የአማራ ህዝብ ነው ብለው ስለሚያስቡ፣
- የአማራን ህዝብ በማብጠልጠልና የተለያዩ ስሞችን በመለጠፍ ከሌሎች ወንድምና እህቶቹ ጋር አናክሰው፤ ከተሳካላቸው ኢትዮጵያንም ማዳከምና ማፍረስ ይቻላል ብለው ስለሚያምኑ፣ እና፤
- የአማራን ህዝብ ከሌሎች ጋር በማናከስ ኢትዮጵያ እንድትፈርስ ካደረጉ በኋላ ከአማራ መሬት የሚበቃቸውን ዘርፈው ታላቋን ትግራይን በተደላደለ ሁኔታ ለመመስረት ይቻላል የሚል ቅዠት ስላላቸው ነው ብየ እገምታለሁ።
ጠቅለል ለማድረግ ያህል ተሳካላቸውም አልተሳካላቸውም ህወሃቶች ሂሳብ የምናወራርደው “ከአማራ ልሂቃን” ጋር ነው እያሉ በየጉራንጉሩ ሲደነፉ አንተን ወደውህ ከመሰለህ አውቀህም ሆነ ሳታውቀው በሴራ ፖለቲካቸው ተጠልፈህ አገር ለማፍረስ እየተባበርካቸው እንደሆነ ተገንዘብና ከእንቅልፍህ ነቅተህ ሴራቸውን ለማክሸፍ የምትችለውን ሁሉ አስተዋፅዖ አበርክት።
ቸር እንሰንብት!!!