እልቂትና ተዝካር     (ከአሁንገና ዓለማየሁ) 

January 23, 2021

የጉዞ ፍታቱ ምንኛ ረዘመ

ስንቱ እያለቀ ነው ሰዉ እንደቆዘመ

እድርተኛው ሁሉ ስለሟች ሲያወራ

ስንቱ ተቀጠፈ በሌላኛው ሥፍራ።

የሕወሃት ቀብር ድንኳን ሳይነሳ

ስንቱ ባለእስትንፋስ ተደረገ ሬሳ።

የጉዞ ፍታቱን ያረጉት ልቃቂት

ሊደብቁ ነው ወይ የቋሚውን እልቂት?

ግርም ያረገኛል ሰሞነኛው ዜና

ድባጤ ላይ ታርዶ ሰማንያ ሰው ሞተ

በገበሬ ሞቶ ተገኘ ተከሥተ

ቡለን ላይ ሶስት መቶ ገበሬ ታረደ

ስዩም መስፍን ሸሸ ጉልበቱ እየራደ

መቶ ሰው ተገድሎ አደረ ማንዱራ

ሌላ አዲስ መቃብር ተገኘ ማይካድራ

ጉበቱ ተበላ ሕጻኑ ልጅ ታርዶ

አቦይ ስብሐት መጣ ከገደል ሰርጥ ወርዶ

ጉባ ላይ ሃምሳዎች በጉምዝ ታረዱ

ፓሊሶች እጅ ገባ ተማርኮ ዓባይ ወልዱ

የጉሙዝ ሚሊሻ ዚገም ተሻገረ

ጄኔራል እንትና እንትን ተናገረ

ሕወሃት ከሞተች ከወርም በኋላ

የሕዳሴው ግድብ በሰው ደም ሲሞላ

የሰው እልቂት ሳይሆን ዜናው ሌላ ሌላ።

(ጉባ፣ ድባጤ፣ ማንዱራ፣ ቡለን፣ ዚገም ከጳጉሜ እስከ ጥር ዘር ተኮር ጭፍጨፋ

 የተደረገባቸው የመተክል (ጎጃም) አካባቢዎች ናቸው)

 

አሻድሊ ታድለህ

ሁሉንም ያስቻለህ

ምን ዓይነት ጌታ አለህ?

አንገት በገጀራ ታስቀነጥሳለህ

ከሽሜ ጋር ሸገር ኬኩን ትቆርሳለህ

ጓሮህ ከዝናሽ ጋር ሪባን ትቆርጣለህ።

አሻድሊ ባለቀን!

ፈላጭ ቆራጭ ማለት ከዚህ በላይ የታል

ያሻውን በጅምላ መቃብር ይከታል

ሲሻው ሸገር መጥቶ ጣፋጭ ኬክ ይቆርሳል

ቡለን ተመልሶ የሰው ደም ያፈሳል

ሪባን ይቆርጥና

ከቀዳሚ እመቤት ፎቶ አብሮ ይነሳል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

በጠንካራ መሰረት ላይ እንድንቆም – ይርጉ እንዳይላሉ

Next Story

ፓርላማ፣ ለመተከሉ ጨለማ፤ ሻማ ወይስ ሌላ ድራማ? (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

Go toTop