እንዴት ያለ ሥልጣን የዓለም ንጉስ
በሰላምታ ምክንያት አገር የሚወርስ፡፡
ፖሊስ የማይፈራ ዳኛ የማያቀው
የማይዳሰሰው የማይታየው
ስንቱን ባለሙያ በየቤቱ አስቀረው፡፡
ምርጡ ጥበበኛ ላገር መከታው
ከምድር እስከጠፈር ተመራማሪው
ዛሬስ እያቃዠ ጉንፋን ድል ነሣው፡፡
ቅጠል በጣሽና ቀማሚም ጠይቆ
ሁሉን ተመራምሮ ሌተቀን ተራቆ
ያዳም ልጅ ተረታ ፍጡር መሆኑ ታውቆ፤
የሰው ልጅ ተጨንቆ ሰላምን ለማግኘት
ሲበር በሰማይ ሲዳክር በመሬት
ሚሳየል አልሠራ ሮኬት ሆነ ጀት
በትንፋሽ ተረታ አወይ ሰውነት፡፡
ዳርዊንና ማልተስ እንደተነበዩት
እንግዲህ መፎከር የለም ማቅራራት፤
ኮሮና ነገሠ እስኪወርድ ምህረት
ወሸባ ወሸባ እንዲየው በርቀት፡፡
ሕዝበ አሕዛብ ሁሉ ወንዱም ሆነ ሴቱ
መዘመሩ ናፍቆት በየአውደምህረቱ
ፌስቡክና ቫይቨር ጠምዶ በየፊቱ
ድምፅና ምስልን ባጀው በየቤቱ፡፡
የእግር ኳሱ ቡድን ጋጋታ የለመደው
የቅርጫት ኳስ ቡድን ዋካታ የናፈቀው
የስፖርቱ ቤተሰብ ወጣት ሽማግሌው
በመስኮት ላይ ቀረ አጀብ እያማረው፡፡
ሰው ወዳጅ ዘመዱን ሲያገኝ እንዳያቅፈው
ከንፈር ጉንጭን አይቶ ቀርቦም እንዳይስመው
እግር ፓርክ ወስዶት እንዳያዝናናው
እጅ ሥራ ሠርቶ እንዳይኖር በምንዳው
ንጉሡ ኮሮና ሁሉን ከለከለው፡፡
ያዳም ልጅ የሔዋን አይሁድ ክርስትያን
ቡድሒስቱ እስላሙ አረማውያን
መድሐኒት መጥቶለት ሁሉን የሚያድን
በውሀ መታጠብ ጠፍቶት መቀደስን
ሁሉንም ለማግኘት ተማምኖ ገንዘብን
ልብ መግዛት አጥቶ የሚያዘልቀውን
ውሀን በመዘንጋት ተሠረቀ ነፍሱን፡፡
እንደአውድማ በሬ እሚታሠር አፉ
አንዱ በሌላው ሥር አለአግባብ ማለፉ
የፈጸመው ጥፋት ተቆጥሮበት ግፉ
ሰውም ተሸበበ አወይ ዘመን ክፉ፡፡
በቅንጦት የመጣ በአስረሽ ምቺው
ሕግ እየተሻረ አያስቆጣ ምነው፤
ግን በሌላው ስህተት ተጎዳ ብዙ ሰው፡፡
ዓለም ትልቅ መስላ የማይደርሱባት
ዛሬማ አየናት ትንሽ ጎጆ ናት
በመንካት በትንፋሽ የተዳረሱባት
እንግዲህ ሰው ባየው ምርምር ውጤት
ዓለምን የሚያድን በፈዋሽነት
እውነትን ላወቀ እሱስ ነው መድሐኒት፡፡
እንግዲህ ተረኛው ምንም አይታወቅ፣
መዘንጋቱ ቀርቶ ይሻላል መጠንቀቅ፡፡