ከቦጋለ አበበ
«የማይቻል ነገር የለምና ሙኒክን አሸንፈን ወደ ሩብ ፍፃሜ እናልፋለን»ይህ አስተያየት በሻምፒዮንስ ሊግ ብቸኛው የእንግሊዝ ተስፋ የነበረው ክለብ አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር ነው።ቬንገር ከትናንት በስቲያ ከጨዋታው በፊት የሰጡት ይህ አስተያየት እንግሊዛውያን በሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ክለባቸውን የሚያዩበትን ተስፋ የሰጠ ቃልኪዳን ሆኖ ነበር።
ቬንገር በሜዳቸው ኢሚሬትስ በጀርመኑ ክለብ ባየር ሙኒክ ሦስት ለአንድ በሆነ ውጤት ከተሸነፉ በኋላ የሰጡት ተስፋ ሰጪ አስተያየት በደርሶ መልስ ጨዋታው ከባድ የሚመስለውን ጨዋታ ውጤት ለመቀልበስ ምናልባትም ተዓምር ይፈጥሩ ይሆናል የሚያሰኝ ነው።
ለስምንት ዓመታት የዘለቀ የዋንጫ ድርቅ የመታቸው መድፈኞቹ በዚሁ ምክንያት በርካታ ኮከብ ተጫዋቾቻቸውን አጥተዋል። ለተጫዋቾች ዳጎስ ያለ ገንዘብ አውጥተው ዋንጫዎችን ከመሰብሰብ ይልቅ የክለቡን የገንዘብ አቅም ወደ ማጎልበት ያዘነበሉት ቬንገርም በክለቡ ደጋፊዎች ጠንካራ ተቃውሞ ባይገጥማቸውም ተስፋ የተቆረጠባቸው ይመስላል።
በዚህ የውድድር ዓመት በእንግሊዝ ሊጎች ከሦስቱም ዋንጫዎች በጊዜ የተሰናበቱት መድፈኞቹ ብቸኛ ተስፋቸው የነበረውን የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫም ተሰናብተው ባዶ እጃቸውን ወደ ኢሚሬትስ መመለሳቸው እውን ሆኗል።
መደፈኞቹ ከትናንት በስቲያ የራሳቸውንም ታሪክ ቀይረው የእንግሊዝ ክለቦች ከረጅም ዓመታት በኋላ ከሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ፉክክር እንዳይርቁ ያደርጋሉ ተብሎ የተጣ ለባቸውን እምነት ማሳካት አልቻሉም።
ቬንገር ከባየር ሙኒክ ጋር የሚያደርጉትን የደርሶ መልስ ጨዋታ በድል ተወጥተው በሜዳቸው የደረሰባቸውን ሽንፈት እንደሚቀለብሱ ተስፋ ቢያደርጉም በጨዋታው የመድፈኞቹ ወጣ ገባ ያለ አቋም የአሰልጣኙን ቃል ሊያስጠብቅ አልተቻለውም።
ከመድፈኞቹ የደርሶ መልስ ጨዋታ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በሻምፒዮንስ ሊጉ ፍልሚያ የጣሊያኑን ኤሲ ሚላን ክለብ ተዓምር በሚመስል ጨዋታ ዓለምን አስደምመው ያሸነፉት የካታሎን ጀግኖች ባርሴሎናዎች «ኳስ ድቡልቡል ናት፤በዘጠና ደቂቃ ውስጥ የሚፈጠረው አይታወቅም»የሚባለውን አባባል እውነተኛነት አረጋግጠዋል።
በዚህም ምክንያት ይመስላል ቬንገር በሜዳቸው ሦስት ለአንድ ተሸንፈው ከሜዳቸው ውጪ በተሻለ የግብ ክፍያ አሸንፈው የእንግሊዝ ክለቦች እ.ኤ.አ ከ1996 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ተስፋ የተጣለባቸው።
በእርግጥም ቬንገር የባርሴሎናን ተዓምረኛ ጨዋታ ካዩ በኋላ የባየር ሙኒክን ውጤት ቀልብሰው በሻምፒዮንስ ሊግ የሚኖራቸው ቆይታ እንደሚራዘም ተስፋ ሰንቀው ነበር።መድፈኞቹ የአሰልጣኛቸው ተስፋ ፍሬ አልባ እንዳይሆን በጨዋታው ጥረት አድርገው ሁለት ለባዶ በሆነ ውጤት አሸንፈዋል፤ውጤቱ በሻምፒዮንስ ሊጉ ወደ ቀጣይ ዙር ባያሳልፋ ቸውም።
ቬንገር አርሰናል ብቻ ሳይሆን የእንግሊዝ ክለቦች ከብዙ ዓመታት በኋላ በሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ተፋላሚ ባለመሆናቸው የእንግሊዝ ክለቦች ዞር ብለው አቋማቸውን እንዲፈትሹ ትናንት ከቢቢሲ ስፖርት ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
በእንግሊዝ ማራኪ የጨዋታ ፍልስፍና በመከተል ወደር ያልተገኘላቸው ቬንገር እንግሊዝ በዓለም ተወዳጅ የሆነው ፕሪሚየር ሊግ ያላት አገር እንደመሆኗ መጠን በሻምፒዮንስ ሊግ እስከ መጨረሻ የሚጓዝ ክለብ ማጣቷ ለአገሪቱ እግር ኳስ አሳፋሪ እንደሆነ አስረድተዋል።
«እንግሊዝ በሻምፒዮንስ ሊጉ የሩብ ፍፃሜ ፍልሚያ የሚወክላት ክለብ ማጣቷ ለአገሪቱ ክለቦች የማንቂያ ደውል ሊሆን ይገባል፤ጉዳዩ ለአገሪቱ እግር ኳስ አሳዛኝ የሚባል ነው»በማለትም ቬንገር ቁጭታቸውን ገልፀዋል።
እንግሊዝ ሁለቱን የአንድ ከተማ ተቀናቃኞች ማንቸስተር ዩናይትድና ሲቲን፤ የአምናው የሻምፒዮንስ ሊግ ባለድል ቼልሲንና አርሰናልን የመሳሰሉ ክለቦችን ታቅፋ በሻምፒንስ ሊግ ቢያንስ የሩብ ፈፃሜ ተፋላሚ የሚሆን ከለብ ማጣቷ በእርግጥም ክለቦቹ ራሳቸውን ዞር ብለው እንዲመለከቱ ሊያደርግ እንደሚገባ የስፖርት ቤተሰቡ ጠንካራ እምነት አለው።
ቬንገርም ከጨዋታው በኋላ የሰጡት አስተያየት በርካታ ወገኖችን ያስማማ ሆኗል። «ዩናይትድ፤ ሲቲና ቼልሲን የመሳሰሉ ክለቦች እያሉ እንግሊዝ እንደዚህ አይነት ታሪክ ያሰተናገደችው ከብዙ ዓመታት በኋላ ነው፤ይህን ታሪክ ለመቀየር ጉዳዩን አፅንኦት ሰጥተን ልንመለከተው ይገባል»በማለት ቬንገር የሰጡት አስተያየት በእንግሊዛውያን ተቀባይነት ይኖረዋል።
ቬንገር በዘንድሮው የውድድር ዓመት ቁርጣቸውን ቢያውቁም በቀጣዩ ዓመት የክለባቸውንም ይሁን አሁን የተበላሸውን የእንግሊዝ እግር ኳስ ገፅታ ለመቀየር መነሳሳታቸውንና ለዚህም የማይከፍሉት መሰዋዕትነት እንደማይኖር ተናግረዋል።
«በእርግጠኝነት መናገር የምችለው በቀጣይ ዓመት ይህን ታሪክ ለመለወጥ መስጠት ያለብኝን ሁሉ እንደምሰጥ ነው፤ወጣቶቹ ተጫዋቾቼ ይህን ለማሳካት እንደሚጥሩም እርግጠኛ ነኝ»በማለት አስተያየት የሰጡት ቬንገር ዘንድሮ በፕሪሚየር ሊጉን አራተኛ ሆነው ለማጠናቀቅ አጣብቂኝ ውስጥ ቢሆኑም ተጫዋቾቻቸው ጠንካራ ስራ ሰርተው በቀጣይ ዓመት ሻምፒዮንስ ሊግ ተፋላሚ እንደሚሆኑ ተስፋ አድርገዋል።
አርሰናልን ከሻምፒዮንስ ሊጉ በደርሶ መልስ ጨዋታ ያሰናበተው የባየር ሙኒኩ አሰልጣኝ ጁፕ ሄንክስ የእንግሊዝ ክለቦች በዓለም ጠንካራ ከሚባሉት ግንባር ቀደም እንደመሆናቸው መጠን በሻምፒዮንስ ሊግ የሚያሳዩት አቋም ጠንካራ መሆን እንደሚገባው ገልፀዋል።
በዚህ ዓመት የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ከእንግሊዝ ማንቸስተር ዩናይትድና ሲቲ፤አርሰናል እንዲሁም ቼልሲ ተካፋይ የነበሩ ቢሆኑም አሁን ከጨዋታው ውጪ ናቸው።
የአምናው የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ማንቸስተር ሲቲ በሻምፒዮንስ ሊጉ በምድብ አራት ከጀርመኑ ቦሩሲያ ዶርት ሙንድ፤አያክስ አምስተርዳምና ከስፔኑ ሪያል ማድሪድ ጋር ተደልድሎ ከምድቡ የመጨረሻ ደረጃን ይዞ ከውድድር ውጪ ሆኗል።
ማንቸስተር ዩናይትድ በበኩሉ የምድብ ጨዋታውን በድል ከፈፀመ በኋላ አስራ ስድስት ውስጥ ገብቶ በሪያል ማድሪድ በደርሶ መልስ ውጤት ሦስት ለሁለት ተሸንፎ ሻምፒዮንስ ሊጉን ተሰናብቷል።
በምድብ አምስት ተደልድለው የነበሩት የአምና የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ባለቤቶቹ ቼልሲዎች በምድባቸው ሦስተኛ ሆነው በማጠናቀቃቸው በጊዜ ከውድድር ውጭ ሆነዋል።ቼልሲ በሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ ዋንጫ አንስቶ በቀጣይ ዓመት ከምድቡ ማለፍ ያልቻለ ክለብ ሆኗል።