ደርግ ሥልጣን የያዘው በወታደሮች ደሞዝ ይጨመርልን ተቃውሞ በተቀጣጠለ ነውጥ ነበር። ባለጊዜዎቹ ወታደሩን አልሰሙትም።ደሞዝ አልጨምርልህም ያሉት ወታደር እነሱንም ሀገርንም ገደል ጨምሮ ሄዷል። ወታደሩ መግደያ መሳሪያ የታጠቀ ስለነበር። ሐኪሞቹ ግን የታጠቁት መፈወሻ እውቀት ነው። የነሱ ዐመጽ ደግሞ ሀገርን የሚፈውስ ያድርግልን። (በነገራችን ላይ በተማሪ ረብሻ ጊዜ እንኳን በመጨረሻ ነው የሕክምና ተማሪዎች አመጹን የሚቀላቀሉት። የትምህርታቸው ባሕርይ ፋታ የሚሰጥ ባለመሆኑ። ቅኝታቸውም ሁከትን የማምጣት ሳይሆን አካላዊና አእምሯዊ ሰላምን የማስፈን ስለሆነ። ሐኪሞች አመጹ ማለት የሥርዐቱ ተስፋ ተሟጧል፣ አደጋው እውነትም የህልውና ሆኗል የሚለውን ያረጋግጣል።)
ወደ ደሞዙ ጉዳይ ስንመለስ የወታደር ደሞዝ እኛ ሕፃናት ሳለን በዚያ በደርግ ዘመን መቶ ሃያ ብር ነበር። እንግዲህ የማውቀውን የአዲስ አበባን ዋጋ እየጠቀስኩ ላነጻጽር። ኩንታል ጤፍ ሃያ ብር ስለነበር አንድ ወታደር ዘና ብሎ በአንድ ወር ደሞዙ ብቻ አምስት ኩንታል ጤፍ መግዛት ይችል ነበር። አንድ በግም ወደ ሃያ ብር ገደማ ነበር። ስለዚህ አንድ ወታደር ካሰኘው በአንድ ወር ደሞዙ አምስት በግ መግዛት ይችል ነበር። ዛሬ አንድ በግ ስንት ነው? አሥር ሺህ ብር (ዝቅተኛው ዋጋ)። የአንድ ሐኪም ደሞዝም አሥር ሺህ ብር። ይህ ማለት የመንግሥቱ ኀይለማርያም ዘመን የወታደር ደሞዝ ከአቢይ አህመድ አሊ ዘመን የሐኪም ደሞዝ ጋር ሲተያይ የቀደመው በአምስት እጥፍ ይበልጥ ነበር ማለት ነው። ልዩነቱ ምንድነው? ሁለቱም ኦሮሞ፣ ሁለቱም ኮሎኔል፣ ሁለቱም ሌሎች ያደራጁትን አመጽ ጠልፈው ሥልጣን ላይ የወጡ መሪዎች ናቸው። ሁለቱም በአፍ ኢትዮጵያ ትቅደም እያሉ ኢትዮጵያውያንን የጨፈጨፉ፣ ኢትዮጵያን ያወደሙ፣ ያፈረሱ ናቸው።ሁለቱም ከሰባተኛ ወይም ከስምንተኛ ክፍል ወደ ውትድርና የገቡ ናቸው። መንግሥቱ ኃይለማርያም የተማረን ሰው ቢጠላም ትምህርትን ግን ይወዳል። ልጁን ሳይቀር ትምህርት ነው ያላት። አቢይ የተማረ ሰውንም ትምህርትንም ነው መሰል የሚጠላው። መንግሥቱ ሐኪም ይወዳል፣ ለሕክምና ትምህርትም ትልቅ ግምት አለው። ልጆቹም ሐኪሞች ነው የሆኑት ይባላል። አቢይ ግን ሐኪም ይጠላል። ፕሮፌሰር አሥራትን እያስታወሱት ይሆን? የአቢይ የሥጋ ልጆቹም ባይሆኑ የመንፈስ ልጆቹ ሃኪሞች ሳይሆኑ አጋቾች ነው የሆኑት።
ለማንኛውም የዛሬን የሐኪም ደሞዝ ከደርግ ጅማሮ ዘመን ተራ ወታደር (ሐኪም አላልኩም) ደሞዝ ጋር ለማስተካከል ቢያንስ አምስት እጥፍ ጭማሪ ይፈልጋል። በሌላ አነጋገር የአንድ የደርግ ወታደር ደሞዝ ለአምስት ሃኪሞች ተካፍሎ እየተሰጣቸው ነው። ወይም 5 የአቢይ አህመድ አሊ ደሞዝተኛ ሐኪሞች ደሞዛቸውን ተቀብለው ለአንድ ሰው ቢሰጡት ያ ድምርምር ደሞዝ ከደርግ ወታደር ደሞዝ ጋር እኩል ይሆናል። የመግዛት አቅሙን ነው እያነጻጸርን ያለነው።
ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ በሐኪሞች ተቃውሞ ዙሪያ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ዝምታ አስገርሞኝ ነው። ምናልባት የዝምታው መንስኤ አሥር ሺህ ብር ደሞዝ አነሰን የሚለውን ካለመረዳት የመነጨ ይሆን? ብዬ እንዳስብም ስላደርገኝ ነው። በስደት ያለው ኢትዮጵያዊ ከፊሉ በኅያለሥላሴ፣ አብዛኛው በደርግና በወያኔ የመጀመሪያ አመታት የተሰደደ ስለሆነ አሥር ሺህ ብር የሚለውን የደሞዝ መጠን አሁናዊ ትርጉም በደንብ አይረዳው ይሆናል። አንድ ሺህ ብር የሚንስቴር ደሞዝ ስለነበረ ድሮ። ከስደተኛው ውስጥ እጅግ ብዙ ለቤተሰብ ገንዘብ የሚልክና የኑሮ ውድነት እንዳለ የሚያውቅ ቢኖርም በቦታው ላይ ስለማይገኝ የኑሮ ውድነቱ አጥንቱ ድረስ ዘልቆ አይሰማው ይሆናል ብዬ አሰብኩ። ስለዚህ እስኪ ጥቂት ንጽጽር አድርገን እንየው የሚል ሃሳብ መጣልኝ።
በደርግ መጀመሪያ አካባቢ አንድየአባቴ ጓደኛ ሐኪም የስድስት መቶ ብር ደሞዝተኛ ነበር። ከነሰርቪሱ ስምንት ክፍል ያለውና ባለ ግቢ የሆነ የተንጣለለ ቪላ በመቶ አምሳ ብር ተከራይቶ ይኖር ነበር። ያን ጊዜ እንዳልኳችሁ አንደኛ ደረጃ የአዳ ማኛ ኩንታል ጤፍ ሰላሣ ብር (ተራው ደግሞ ሃያ ብር) ይገዛ ነበር። በግ ደግሞ ሃያ ብር፣ በጣም ትልቁ ሰላሳ ብር ይገዛ ነበር። የሃያ ብር በግ ሃያ ሺህ ከገባ የኑሮው ውድነት በቀጥታ ንጽጽር መቶ እጥፍ ነው ያደገው።
በወያኔ መጀመሪያ አካባቢ ደግሞ ተከራይቼ በምኖርበት ግቢ አንድ ጎረቤቴ የዳግማዊ ሚኒልክ ሐኪም ጸዳ ያለ ትልቅ ክፍል በመቶ ብር ተከራይቶ ይኖር ነበር። ደሞዙ ወደ ስምንት መቶ ብር ገደማ ሲሆን ተቆራርጦ ሰባት መቶ ምናምን ብር ያገኝ ነበር። ከቤታችን በቅርበት ካለው የሾላ ገበያ እኔ ነኝ ያለ በግ በመቶ አምሳ ብር ይገዛ ነበር። በአንድ ሰባተኛ ደሞዙ ቤት መከራየት በአንድ አምስተኛ ደሞዙ በግ መግዛት ይችል ነበር። የዛሬውን ሐኪም ደሞዝ ከዚህ ከወያኔ ጅማሮ ዘመን ሐኪም ደሞዝ ጋር ለማስተካከል ከአምስት እስከ ሰባት ጊዜ ማባዛት ያስፈልጋል። ደሞዝ አሥር ሺህ ብር፤ ቤት ኪራይ አሥር ሺህ ብር ነው የዛሬው ተመን። ስለዚህ የዛሬው የሃኪም ደሞዝ መነሻ ሰባ ሺህ ብር ቢደረግ ከወያኔ ጅማሮ ዘመን የሀኪም ደሞዝ ጋር ይስተካከላል ማለት ነው።
ኢትዮጵያ ለማይመላለስ ስደተኛ የኑሮውን ውድነት ለማገናዘብ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ፍጹም ባይተዋርነትን የሚፈጥር፣ ጣልያን ሀገር እንደመሄድ ያለ ሁሉንም ነገር እንዲዞርብህ የሚያደርግ ነው – ቆይተህ ቆይተህ አገርህ ስትመለስ የሚሰማህ ስሜት። እንደዛሬው የከተማው ፈረሳ ሳይጨመርበት በዋጋው ንረት እና በሌላው ብቻ ማለቴ ነው። ይሄንን የምለው አሥርና ሃያ አመት ሀገሩ ላልተመለሰ ሰው አይደለም። ሁለትና ሦስት አመት እንጂ። ያኛውማ እሱ ሞቶ ከሙታን ጋላክሲ ተመልሶ ቋንቋውን ሳይቀር የማያውቀው አንድ ባእድ ፕላኔት ላይ እንደወደቀ ሆኖ ሊሰማው ይችላል ብዬ እገምታለሁ።
ይሄ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበቱ ነገር እዚያው ኢትዮጵያም ተቀምጠህ ሊያዞርብህ ይችላል። እኔን ገጥሞኛል። በዘመነ ወያኔ ሻይ የምጠጣበት የወሎ ሰፈር ካፌ አጠገብ የፍራፍሬ ሱቅ ነበር።
አንድ ቀን ከካፌው ስወጣ ሁለት ኪሎ ብርቱካን ገዛሁና ሄድኩ። አራት አራት ብር ነበር በኪሎ። ሌላ ጊዜ ከአንድ ወር ገደማ በኋላ ቦሌ ጉዳይ ነበረኝና ስመለስ እዚያች ካፌ ቁጭ ብዬ ስነሳ አሁንም ብርቱካን ልገዛ ፈለግኩ። ዛሬ ግን አንድ ኪሎ ብቻ ነው የፈለግኩት። አሥር ብር ስሰጠው ሁለት ብር ብቻ መለሰልኝ። አንድ ኪሎ ብርቱካን ብቻ እኮ ነው የገዛሁህ አልኩት። አዎ ጨምሯል። ኪሎ ስምንት ብር ነው አለኝ። ዞረብኝ ብል አታምኑኝም። ጮህኩም። አምሳ ሳንቲም ቢጨምርም ይገርመኝ ነበር እንኳን እጥፍ ሆኖ። በአንድ ወር!
ይህ በአንድ ወር ሳይሆን በአንድ ትውልድ ውስጥ የሚጠበቅ ጭማሪ ነው። ይሄንን አስደንጋጭ ጭማሪ እዚያው አጠገብ የሚገኝ መድኃኒት ቤት ገብቼ ለሠራተኞቹ ባወራላቸው የተገረመ ሰው አልነበረም። አለመገረማቸው ገረመኝ። በአመቱ ኢትዮጵያ ተመለስኩና ጥቁር አንበሳ የታመመ ሰው ልንጠይቅ ስንገባ ልጄን ሁለት ኪሎ ብርቱካን ግዢ ብዬ መቶ ብር ሰጠኋት። በሽተኛውን ጠይቀን ስንወጣ መልሱን ልታረሳሺ ነው እንዴ? ብዬ ስጠይቃት። የምን መልስ? ኪሎው አምሳ ብር ነው አትለኝም! በፍጹም ስላላመንኳት ተመልሼ ባለፍራፍሬ ቤቱን ሄጄ ጠየቅኩት። አምሳ ብር ነው ግን ደንበኛ ስለሆኑ አርባ ስምንት አደርግሎታለሁ አለኛ! የምን ደምበኛ? እንግዲህ ያ የማወራችሁ ጊዜም ዛሬ ላይ ተቁሞ ወደ ኋላ ሲታሰብ የድንጋይ ዳቦ ዘመን ነው የሚመስለው። ዛሬ አንድ ዳቦ አሥር ብር ፣ አንድ እንቁላል ሃያ ብር እየተሸጠ ባለበት። ኪሎ ብርቱካን ስንት ይሆን?
እዚህ ላይ ዳቦ በብር አርባ፣ እንቁላል በብር ሃያ ይገዛበት የነበረውን የልጅነታችንን “በዝባዥና ጨቋኝ” ሥርዐት እንድትናፍቁ አይደለም። ያውም ይሄ ኑሮው ውድ ነው በሚባለው በአዲስ አበባ የነበረው ዋጋ ነው። የክፍለ ሀገሩንማ አታንሱት። እርግጥ ብዙ ሰው በዚያ ዘመን የኖረ ሳይቀር ይህንን ለማመን ይቸገራል። የገዛ የእድሜ እኩዮቻችን እንኳን እየተገረሙ ነው የሚሰሙት። የነገሮች ርካሽነት ዋጋቸውን እንዳታስበውም ሊያደረግ ስለሚችል በዚያ ዘመን ዋጋ ላይ ትኩረት አልነበራቸው ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ገበያ ሄዶ የማይገዛ ሰው የነገሮችን ዋጋ ሊያስተውለው ስለማይችልም ይሆናል። የዳቦና የእንቁላሉ፣ የበጉ ዋጋ ተጽፎ ያነበብኩት፣ ሲወራ የሰማሁት ሳይሆን ራሴ የገዛሁበት ወይም ሲገዛ ያየሁበት ዋጋ ነው።
እንቁላል በብር ሃያ የገዛሁባት ቀን
አንድ ቅዳሜ እንቁላል ግዛ ተብዬ ገበያ ስላክ የተሰማኝ ደስታ አይረሳኝም። የእጅ ማስገቢያ ያላት ቄንጠኛ የላስቲክ ከረጢት ነበረች። እሷን ያዝኩና ወደ ገበያ ሮጥኩ። አንድ ሦስት ሻጮችን ጠይቄ ዋጋቸው ተመሳሳይ ሲሆን መጀመሪያ የጠየቅኩት ሰውዬ ጋር ሄጄ እንቁላሌን መረጥኩ። ሲደረግ እንዳየሁት በጸሐይ ብርሃን አያየሁ ከረጢቴ ውስጥ ሃያ እንቁላሎች ጨመርኩና የተሰጠችኝን አንድ ብሬን ከፍዬ በሄድኩበት ሳይሆን በሌላ መንገድ ወደ ቤቴ ስመለስ ወፍጮ ቤቱ ጋራ የሚቀፍ ነገር አየሁና ቆምኩ። አንድ ወጣት ቦይ ውስጥ የገባች አንድ አህያ አጠና በሚያክል ዱላ ይደበድባል። ዱላውን እንዴት አድርጎ እንደሚሰነዝረው ለሚያይ ይሰቀጥጣል። ዞር ዞር ብዬ ሳይ ተው የሚለው ሰው ቀርቶ በቁም ነገር የሚያየው የለም። አላፊው አግዳሚው ግን ብዙ ነው።አላስችል አለኝና ለምንድነው እንደዚህ የምትመታት አልኩት? እንስሳት በጣም ነበር የምወደው። ምናገባህ አለኝና የበለጠ ተናዶ በሃይል ሲሰነዝር እሷን ሳታትና የተጫነችውን እንጨት ሲመታው ምን እንደሆነ አላውቅም የሆነ ጉማጅ ተፈናጥሮ እንቁላል የያዝኩበትን ላስቲክ መታው። ላስቲኩን ስከፍተው እንቁላሎቹ ውሃ ሆነዋል። ክፈለኝ አልኩና ተንጠለጠልኩበት። መነጨቀኝና እኔንም በዱላ ሊነርተኝ ሲቃጣ ገበያተኛው በቁጣ ምንድነው ምንድነው ብለው አስጣሉኝ። ሰዉ ከበበን። መታህ እንዴ? ምን ሆነህ ነው የምታለቅሰው አሉኝ። ተልኬ መጥቼ የብር እንቁላል ገዝቼ ወደ ቤቴ ስሄድ ይሄ ሰውዬ መያዣውን በዱላ መታና ውሃ አደርገው ብዬ ላስቲኩን ከፍቼ አሳየኋቸው። አራት አህዮች ጭኖ ሶሶቱን ወፍጮ ቤቱ ጋር አራግፎ ካንደኛዋ ጋር ሲጣላ የነበረው ወጣት ክፈል ቢባል አውቄ አልመታሁትም፤ አልከፍልም አለ። አንቀው ያዙት። ይሄ ልጅ ቤተሰቦቹ ይገድሉታል። ቁማር የተጫወተበት፣ ብስኩት የበላበት ነው የሚመስላቸው። ስጠውና ገዝቶ ይግባ አሉት። እንባው ኮለል ብሎ እየወረደ ከኪሱ አንድ ብር አውጥቶ ሰጣቸውና ሰጡኝ። ምንም ተናድጄ የነበረ ቢሆን አስጣዮቼን አመስግኜ እንቁላሉን ገዝቼ ወደ ቤት እየሄድኩ ወጣቱ አሳዘነኝና እኔም ትንሽ አለቀስኩ። የአንድ አህያ ጭነት እንጨት ያን ጊዜ ሰባ አምስት ሳንቲም ነበር። የሆኖ ሆኖ ያቺ ቀን እንቁላል በብር ሃያ የገዛሁባት የመጀመሪያም የመጨረሻም ቀን ሆነች። አልረሳትም። ቆይቶ ሌላ ጊዜ ገበያ ስላክ እንቁላል በብር አሥራ ስድስት ሆኖ ጠበቀኝ።
በነገራችን ላይ በዚያ ዘመን አህያ በከፍተኛ ጭካኔ ሲቀጠቀጥ ተው የሚል ባይኖርም አንድ ሰው ግን አላግባብ ሲበደል ዝም ብሎ የሚያይ አልነበረም፤ ማኅበረሰቡ። ዛሬ ግን ሰው በጎዳና ቢቀጠቀጥ ቀርቶ ቢገደል ያገባኛል የሚል የለም። ሃኪሞች ራበን ብለው ጎዳና ወጥተዋል፣ መንግሥትም ያስራል፣ ይቀጠቅጣል። ሕዝቡ ግን ምናገባኝ ብሎ ጭጭ!
“እኔ ምናገባኝ” የሚባለው ሐረግ
እሱ ነው ሀገሬን ያረዳት እንደበግ
ብሏል ኑረዲን ኢሳ
አዎ ምናገባኝ ብሎ አፍን ለጉሞ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ሀገርን ያጠፋል። ተዉ “ያገባናል!” በሉ። “ያገባናል” እንበል